1 ሳሙኤል 26:7-11
1 ሳሙኤል 26:7-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዳዊትና አቢሳም ወደ ሕዝቡ በሌሊት መጡ፤ እነሆም፥ ሳኦል በድንኳን ውስጥ ተኝቶ ነበር፤ ጦሩም በራስጌው አጠገብ በምድር ተተክሎ ነበር፤ አቤኔርና ሕዝቡም በዙሪያው ተኝተው ነበር። አቢሳም ዳዊትን፥ “ዛሬ እግዚአብሔር ጠላትህን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ አሁንም እኔ በጦር አንድ ጊዜ ከምድር ጋር ላጣብቀው፤ ሁለተኛም አልደግመውም” አለው። ዳዊትም አቢሳን፥ “እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጁን የሚዘረጋ ንጹሕ አይሆንምና አትግደለው” አለው። ደግሞም ዳዊት አለው፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር ካልገደለው፥ ወይም ቀኑ ደርሶ ካልሞተ፥ ወይም ወደ ጦርነት ወርዶ ካልሞተ እኔ አልገድለውም። እግዚአብሔርም በቀባው ላይ እጄን እዘረጋ ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው፤ አሁንም በራሱ አጠገብ ያለውን ጦርና የውኃውን መንቀል ይዘህ እንሂድ፤” አለው።
1 ሳሙኤል 26:7-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ ዳዊትና አቢሳ በሌሊት ሰራዊቱ ወዳለበት ሄዱ። እነሆ፤ ሳኦል በሰፈሩ ውስጥ ተኝቶ ጦሩም ራስጌው አጠገብ በመሬት ላይ ተተክሎ ነበር፤ አበኔርና ወታደሮቹም በዙሪያው ተኝተው ነበር። አቢሳም ዳዊትን፣ “ዛሬ እግዚአብሔር ጠላትህን በእጅህ ላይ ጥሎታል፤ አሁንም እኔ አንድ ጊዜ በጦር ወግቼ ከመሬት ጋራ ላጣብቀው፤ መድገምም አያስፈልገኝም” አለው። ዳዊት ግን አቢሳን እንዲህ አለው፤ “አትግደለው! እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጁን አንሥቶ ከበደል ነጻ የሚሆን ማን ነው? ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር ራሱ ይቀሥፈዋል፤ ወይም ቀኑ ደርሶ ይሞታል፤ ወይም በጦርነት ይሞታል። እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን ከማንሣት እግዚአብሔር ይጠብቀኝ! ነገር ግን በራስጌው አጠገብ ያለውን ጦርና የውሃ መያዣውን ያዝና እንሂድ።”
1 ሳሙኤል 26:7-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዳዊትና አቢሳም ወደ ሕዝቡ በሌሊት መጡ፥ እነሆም፥ ሳኦል ጦሩ በራሱ አጠገብ በምድር ተተክሎ በሰፈሩ ውስጥ ተኝቶ ነበር። አበኔርና ሕዝቡም በዙሪያው ተኝተው ነበር። አቢሳም ዳዊትን፦ ዛሬ እግዚአብሔር ጠላትህን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶታል፥ አሁንም እኔ በጦር አንድ ጊዜ ከምድር ጋር ላጣብቀው፥ ሁለተኛም አያዳግምም አለው። ዳዊትም አቢሳን፦ እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጁን የሚዘረጋ ንጹሕ አይሆንምና አትግደለው አለው። ደግሞም ዳዊት፦ ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር ይመታዋል፥ ወይም ቀኑ ደርሶ ይሞታል፥ ወይም ወደ ሰልፍ ወርዶ ይገደላል፥ እኔ ግን እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን እዘረጋ ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው፥ አሁንም በራሱ አጠገብ ያለውን ጦርና የውኃውን መንቀል ይዘህ እንሂድ አለ።
1 ሳሙኤል 26:7-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህም በዚያው ምሽት ዳዊትና አቢሳን ወደ ሳኦል ሰፈር ገቡ፤ ሳኦልንም በሰፈሩ መካከል ተኝቶ አገኙት፤ ጦሩም በራስጌው በኩል መሬት ላይ ተተክሎ ነበር፤ አበኔርና ወታደሮቹም በዙሪያው ተኝተዋል፤ አቢሳም ዳዊትን “እግዚአብሔር በዛሬው ምሽት ጠላትህን በእጅህ ጥሎልሃል፤ ስለዚህ አሁን የገዛ ጦሩን አንሥቼ ልውጋውና ከመሬት ጋር ላጣብቀው፤ አንድ ምት ብቻ ስለሚበቃው ድጋሚ አያስፈልገውም!” አለው። ዳዊት ግን አቢሳን፦ “ልትገድለው አይገባህም! ቀብቶ ያነገሠውን ንጉሥ የሚጐዱ ሰዎችን እግዚአብሔር ራሱ ይቀጣል፤ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምልልሃለሁ፤ እግዚአብሔር ራሱ ሳኦልን ይገድለዋል፤ የሚሞትበት ጊዜ ደርሶ፥ አለበለዚያም በጦርነት መሞቱ አይቀርም፤ እግዚአብሔር ቀብቶ ባነገሠው ንጉሥ ላይ ጒዳት የማድረስ ተግባርስ ከእኔ ይራቅ! ይልቅስ ጦሩንና ውሃ መቅጃውን ይዘንበት እንሂድ” አለው።
1 ሳሙኤል 26:7-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለዚህም በዚያው ምሽት ዳዊትና አቢሳን ወደ ሳኦል ሰፈር ገቡ፤ ሳኦልንም በሰፈሩ መካከል ተኝቶ አገኙት፤ ጦሩም በራስጌው በኩል መሬት ላይ ተተክሎ ነበር፤ አበኔርና ወታደሮቹም በዙሪያው ተኝተዋል፤፥ አቢሳም ዳዊትን፥ “ዛሬ እግዚአብሔር ጠላትህን በእጅህ ላይ ጥሎታል፤ አሁንም እኔ አንድ ጊዜ በጦር ወግቼ ከመሬት ጋር ላጣብቀው፤ መድገምም አያስፈልገኝም” አለው። ዳዊት ግን አቢሳን እንዲህ አለው፤ “አትግደለው! ጌታ በቀባው ላይ እጁን አንሥቶ ከበደል ነጻ የሚሆን ማን ነው? ሕያው ጌታ አለ፥ ጌታ ራሱ ይቀሥፈዋል፤ ወይም የመሞቻው ቀን ይመጣል፤ ወይም በጦርነት ይሞታል፤ ይጠፋልም። ጌታ በቀባው ላይ እጄን ከማንሣት ጌታ ይጠብቀኝ! ነገር ግን በራስጌው አጠገብ ያለውን ጦርና የውሃ መያዣውን ያዝና እንሂድ።”