1 ሳሙኤል 17:1-51
1 ሳሙኤል 17:1-51 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ፍልስጥኤማውያንም ጭፍሮቻቸውን ለጦርነት ሰበሰቡ፤ ራሳቸውም በይሁዳ በሰኮት ተሰበሰቡ፤ በሰኮትና በዓዜቃ መካከል በኤፌርሜም ሰፈሩ። ሳኦልና የእስራኤል ሰዎችም ተሰበሰቡ፤ በኤላ ሸለቆም ሰፈሩ፤ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ሊዋጉ ተሰለፉ። ፍልስጥኤማውያንም በአንድ ወገን በተራራ ላይ ቆመው ነበር፥ እስራኤልም በሌላው ወገን በተራራ ላይ ቆመው ነበር፤ በመካከላቸውም ሸለቆ ነበረ። ከፍልስጥኤማውያንም ሰፈር የጌት ሰው ጎልያድ፥ ቁመቱም ስድስት ክንድ ከስንዝር የሆነ፥ ኀይለኛ ሰው መጣ። በራሱም የናስ ቍር ደፍቶ ነበር፤ ጥሩርም ለብሶ ነበር፤ የጥሩሩም ሚዛን አምስት ሺህ ሰቅል ናስና ብረት ነበረ። በእግሮቹም ላይ የናስ ገምባሌ ነበረ፤ የናስም ጭሬ በትከሻው ላይ ነበረ። የጦሩም የቦ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ ነበረ፤ የጦሩም ሚዛን ስድስት መቶ ሰቅል ብረት ነበረ፤ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር። እርሱም ቆሞ ወደ እስራኤል ጭፍሮች ጮኸ፥ “ከእኛ ጋር ትዋጉ ዘንድ ለምን ወጣችሁ? እኔ ፍልስጥኤማዊ አይደለሁምን? እናንተስ የሳኦል አገልጋዮች ዕብራውያን አይደላችሁምን? ከእናንተ አንድ ሰው ምረጡ፤ ወደ እኔም ይውረድ፤ ከእኔም ጋር ሊዋጋ ቢችል ቢገድለኝም፥ ባሪያዎች እንሆናችኋለን፤ እኔ ግን ባሸንፈው፥ ብገድለውም፥ እናንተ ባሪያዎች ትሆኑናላችሁ፤ ለእኛም ትገዛላችሁ” አለ። ፍልስጥኤማዊውም፥ “ዛሬ የእስራኤልን ጭፍሮች ተገዳደርኋቸው፤ አንድ ሰው ስጡኝ ሁለታችንም ለብቻችን እንዋጋ አልኋቸው” አለ። ሳኦልና እስራኤልም ሁሉ ይህን የፍልስጥኤማዊውን ቃል በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፤ ደነገጡም። ዳዊትም የዚያ የኤፍራታዊው ሰው ልጅ ነበረ፤ ያም ሰው ከቤተ ልሔም ይሁዳ ስሙም እሴይ ነበረ፤ ስምንት ልጆችም ነበሩት፤ እሴይም በሳኦል ዘመን በዕድሜ አርጅቶ ሸምግሎም ነበር። የእሴይም ሦስቱ ታላላቆች ልጆቹ ሳኦልን ተከትለው ወደ ሰልፉ ሄደው ነበር፤ ወደ ሰልፉም የሄዱት የሦስቱ ልጆች ስም ይህ ነበረ፤ ታላቁ ኤልያብ፥ ሁለተኛውም አሚናዳብ፥ ሦስተኛውም ሣማዕ ነበረ። ዳዊትም የሁሉ ታናሽ ነበረ፤ ሦስቱም ታላላቆቹ ሳኦልን ተከትለው ነበር። ዳዊትም የአባቱን በጎች ለመጠበቅ ከሳኦል ዘንድ ወደ ቤተ ልሔም ይመላለስ ነበር። ፍልስጥኤማዊውም ጥዋትና ማታ እየመጣ አርባ ቀን ይቆም ነበር። እሴይም ልጁን ዳዊትን እንዲህ አለው፥ “ከዚህ በሶ አንድ የኢፍ መስፈሪያ እነዚህንም ዐሥር እንጀራዎች ለወንድሞችህ ውሰድ፤ ወደ ሰፈሩም ፈጥነህ ሂድና ለወንድሞችህ ስጣቸው፤ ይህንም ዐሥሩን አይብ ወደ ሻለቃው ውሰደው፤ የወንድሞችህንም ደኅንነት ጠይቅ፤ ወሬአቸውንም አምጣልኝ።” ሳኦልና የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ከፍልስጥኤማውያን ጋር እየተዋጉ በኤላ ሸለቆ ነበሩ። ዳዊትም ማልዶ ተነሣ፤ በጎቹንም ለጠባቂ ተወ፤ እሴይም ያዘዘውን ይዞ ሄደ፤ ጭፍራውም ተሰልፎ ሲወጣ፥ ለሰልፍም ሲጮኽ በሰረገሎች ወደ ተከበበው ሰፈር መጣ። የእስራኤልና የፍልስጥኤማውያን ሠራዊትም ፊት ለፊት ተሰላልፈው ነበር። ዳዊትም ዕቃውን በዕቃ ጠባቂው እጅ አኖረው፤ ወደሚዋጉበትም ሮጦ ሄደ፤ የወንድሞቹንም ደኅንነት ጠየቀ። እርሱም ሲነጋገራቸው፥ እነሆ፥ ጎልያድ የተባለ ያ አርበኛ ፍልስጥኤማዊ የጌት ሰው ከፍልስጥኤማውያን ጭፍራ መካከል ወጣ፤ ቀድሞ የተናገረውንም ቃል ተናገረ፤ ዳዊትም ሰማ። የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ሰውዬውን ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው ከፊቱ ሸሹ። የእስራኤልም ሰዎች፥ “ይህን የወጣውን ሰው አያችሁትን? በእውነት እስራኤልን ሊገዳደር ወጣ፤ የሚገድለውንም ሰው ንጉሡ እጅግ ባለጠጋ ያደርገዋል፤ ልጁንም ይድርለታል፤ ያባቱንም ቤተ ሰብ በእስራኤል ዘንድ ከግብር ነጻ ያወጣቸዋል” አሉ። ዳዊትም በአጠገቡ ለቆሙት ሰዎች፦ ይህን ፍልስጥኤማዊ ለሚገድል፥ ከእስራኤልም ተግዳሮትን ለሚያርቅ ሰው በውኑ ይህ ይደረግለታል? የሕያው አምላክን ጭፍሮች የሚገዳደር ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ ማን ነው?” ብሎ ተናገራቸው። ሕዝቡም፥ “ለሚገድለው ሰው እንዲህ ይደረግለታል” ብለው እንደ ቀድሞው መለሱለት። ታላቅ ወንድሙም ኤልያብ ከሰዎች ጋር ሲነጋገር ሰማ፤ ኤልያብም በዳዊት ላይ እጅግ ተቈጣ፥ “ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂቶች በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውሃቸው? እኔ ኵራትህንና የልብህን ክፋት አውቃለሁና ሰልፉን ለማየት መጥተሃል” አለው። ዳዊትም፥ “እኔ ምን አደረግሁ? ይህ ታላቅ ነገር አይደለምን?” አለ። ዳዊትም ከእርሱ ወደ ሌላ ሰው ዘወር አለ፤ እንደዚህም ያለ ነገር ተናገረ፤ ሕዝቡም እንደ ቀድሞው ያለ ነገር መለሱለት። ዳዊትም የተናገረው ቃል ተሰማ፤ ለሳኦልም ነገሩት፤ ወደ እርሱም ወሰደው። ዳዊትም ሳኦልን፥ “ስለ እርሱ የማንም ልብ አይውደቅ፤ እኔ ባሪያህ ሄጄ ያን ፍልስጥኤማዊ እወጋዋለሁ” አለው። ሳኦልም ዳዊትን፥ “አንተ ገና ብላቴና ነህና፥ እርሱም ከብላቴንነቱ ጀምሮ ጦረኛ ነውና ይህን ፍልስጥኤማዊ ለመውጋት ትሄድ ዘንድ አትችልም” አለው። ዳዊትም ሳኦልን አለው፥ “እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳ ወይም ድብ ይመጣ ነበር፤ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር። በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር። ከአፉም አስጥለው ነበር፤ በተነሣብኝም ጊዜ ጕሮሮውን አንቄ እመታውና እገድለው ነበር። እኔ ባሪያህ አንበሳና ድብ ገደልሁ፤ ይህም ያልተገረዘው ፍልስጥኤማዊ ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። እንግዲህ እገድለው ዘንድ፥ ከእስራኤልም ተግዳሮትን አስወግድ ዘንድ ዛሬ አልሄድምን? የሕያው አምላክ ጭፍሮችን ይገዳደር ዘንድ ይህ ቈላፍ ምንድን ነው?” ዳዊትም፥ “ከአንበሳና ከድብ እጅ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል” አለ። ሳኦልም ዳዊትን፥ “ሂድ፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን” አለው። ሳኦልም ለዳዊት ጥሩር አለበሰው፤ በራሱም ላይ የናስ ቍር ደፋለት። ዳዊትንም ሰይፉን በልብሱ ላይ አስታጠቀው፤ ዳዊትም አንድና ሁለት ጊዜ ሲራመድ ደከመ። ዳዊትም ሳኦልን፥ “አለመድሁምና በዚህ መሄድ አልችልም” አለው። ከላዩም አወለቁለት። ዳዊትም በትሩን በእጁ ያዘ፤ ከወንዝም አምስት ድብልብል ድንጋዮችን መረጠ፤ በእረኛ ኮሮጆውም በኪሱ ከተታቸው፤ ወንጭፍም በእጁ ነበረ፤ ወደ ፍልስጥኤማዊውም ቀረበ። ፍልስጥኤማዊውም መጥቶ ወደ ዳዊት ቀረበ፤ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር። ጎልያድም ዳዊትን ትኩር ብሎ አየው፤ ቀይ ብላቴና፥ መልኩም ያማረ ነበረና ናቀው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፥ “በትርና ድንጋይ ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን?” አለው። ዳዊትም፥ “የለም ከውሻ ትከፋለህ” አለው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን በአምላኮቹ ረገመው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፥ “ወደ እኔ ና፤ ሥጋህንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት እሰጣቸዋለሁ” አለው። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊዉን አለው፥ “አንተ ሰይፍና ጦር፥ ጋሻም ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እመታህማለሁ፤ ራስህንም ከአንተ እቈርጠዋለሁ፤ ሬሳህንና የፍልስጥኤማውያንንም ሠራዊት ሬሶች ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ዛሬ እሰጣለሁ። ምድር ሁሉ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር እንዳለ ያውቃሉ፤ ይህም ጉባኤ ሁሉ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን እንዳይደለ ያውቃል። ሰልፉ ለእግዚአብሔር ነውና፤ እግዚአብሔርም እናንተን በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።” ፍልስጥኤማዊውም ተነሥቶ ዳዊትን ሊገናኘው በቀረበ ጊዜ ዳዊት ፍልስጥኤማዊዉን ሊገናኘው ወደ ሰልፉ ሮጠ። ዳዊትም እጁን ወደ ኮሮጆው አግብቶ አንድ ድንጋይ ወሰደ፤ ወነጨፈውም፤ ፍልስጥኤማዊውንም ግንባሩን መታው፤ ድንጋዩም ጥሩሩን ዘልቆ በግንባሩ ተቀረቀረ፤ እርሱም በምድር ላይ በፊቱ ተደፋ። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን በወንጭፍና በድንጋይ አሸነፈው፤ ፍልስጥኤማዊውንም መትቶ ገደለ ፤ በዳዊትም እጅ ሰይፍ አልነበረም። ዳዊትም ሮጦ በፍልስጥኤማዊው ላይ ቆመ፤ ሰይፉንም ይዞ ከሰገባው መዘዘው፤ ገደለውም፤ ራሱንም ቈረጠው። ፍልስጥኤማውያንም ዋናቸው እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ ሸሹ።
1 ሳሙኤል 17:1-51 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ፍልስጥኤማውያን ሰራዊታቸውን ለጦርነት አሰባስበው፣ በይሁዳ ምድር በሦኮን ላይ አከማቹ፤ እነርሱም በሰኰትና በዓዜቃ መካከል ባለው በኤፌሰደሚም ሰፈሩ። ሳኦልና እስራኤላውያን ተሰብስበው፣ በኤላ ሸለቆ ሰፈሩ፤ ፍልስጥኤማውያንንም ለመግጠም ቦታ ቦታቸውን ያዙ። ሸለቆ በመካከላቸው ሆኖ ፍልስጥኤማውያን አንዱን ኰረብታ እስራኤላውያን ደግሞ፣ ሌላውን ኰረብታ ያዙ። ከጋት የመጣ ቁመቱ ከዘጠኝ ጫማ በላይ የሆነ፣ ጎልያድ የተባለ አንድ ጀግና ከፍልስጥኤማውያን ሰፈር ወጣ። እርሱም ከናስ የተሠራ የራስ ቍር ደፍቶ፣ ክብደቱ ዐምስት ሺሕ ሰቅል የሆነ የናስ ጥሩር ለብሶ ነበር። በእግሮቹ ላይ የናስ ገምባሌ አድርጎ፣ በጫንቃው ላይ ደግሞ የናስ ጭሬ ይዞ ነበር። የጦሩም ዘንግ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የወፈረ፣ የጦሩም ብረት ስድስት መቶ ሰቅል ያህል የሚመዝን ነበር፤ ጋሻ ጃግሬውም ከፊት ከፊቱ ይሄድ ነበር። ጎልያድ ቆሞ ለተሰለፈው የእስራኤል ሰራዊት እንዲህ ሲል ጮኾ ተናገረ፤ “ለውጊያ ተሰልፋችሁ መውጣታችሁ ስለ ምንድን ነው? እኔ ፍልስጥኤማዊ፣ እናንተም የሳኦል አገልጋዮች አይደላችሁምን? አንድ ሰው ምረጡና እኔ ወደ አለሁበት ይውረድ፤ ከእኔ ጋራ ሊዋጋና ሊገድለኝ ከቻለ፣ እኛ ባሪያዎቻችሁ እንሆናለን፤ እኔ ባሸንፈውና ብገድለው ግን እናንተ ባሪያዎቻችን ትሆናላችሁ፤ ትገዙልናላችሁ።” ከዚያም ፍልስጥኤማዊው፣ “ዛሬ የእስራኤልን ሰራዊት እገዳደራለሁ፤ እንዋጋ ዘንድ ሰው ስጡኝ” አለ። ሳኦልና እስራኤላውያን ሁሉ የፍልስጥኤማዊውን ቃል በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፤ ደነገጡም። ዳዊት በይሁዳ የቤተ ልሔሙ ሰው የኤፍራታዊው የእሴይ ልጅ ነበር። እሴይ ስምንት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ በሳኦልም ዘመን ያረጀና ዕድሜው የገፋ ሰው ነበር። ሦስቱ የእሴይ ታላላቅ ልጆች ሳኦልን ተከትለው ወደ ጦርነት ሄደው ነበር፤ እነርሱም ታላቁ ኤልያብ፣ ሁለተኛው አሚናዳብ፣ ሦስተኛውም ሣማ ይባላሉ፤ ዳዊት የሁሉም ታናሽ ነበር። ሦስቱ ታላላቅ ወንድሞቹ ሳኦልን ተከትለው ሄዱ፤ ዳዊት ግን የአባቱን በጎች ለመጠበቅ ከሳኦል ዘንድ ወደ ቤተ ልሔም ይመላለስ ነበር። ፍልስጥኤማዊውም አርባ ቀን ሙሉ ጧትና ማታ ፊት ለፊት ብቅ እያለ ቆሞ ይታያቸው ነበር። በዚህ ጊዜ እሴይ ልጁን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ይህን የተጠበሰ ኤፋ እህል፤ ዐሥር ኪሎ የተጠበሰ እሸትና ዐሥር እንጀራ ለወንድሞችህ ይዘህ ወዳሉበት የጦር ሰፈር በቶሎ ድረስ። ይህንም ዐሥር የአይብ ጥፍጥፍ ለክፍል አዛዣቸው ዐብረህ ውሰድ፤ ወንድሞችህም እንዴት እንደ ሆኑ አይተህ፣ ደኅንነታቸውን የሚያረጋግጥ ምልክት ከእነርሱ ዘንድ አምጣልኝ። እነርሱ ከሳኦልና ከእስራኤል ሰዎች ሁሉ ጋራ ሆነው በኤላ ሸለቆ ከፍልስጥኤማውያን ጋራ እየተዋጉ ናቸው።” ዳዊት በማለዳ በጎቹን ለጠባቂ ትቶ፣ እሴይ እንዳዘዘው ዕቃውን ይዞ ጕዞ ጀመረ። ልክ ሰራዊቱ እየፎከረ ለውጊያ ቦታ ቦታውን ለመያዝ በሚወጣበት ጊዜ ከጦሩ ሰፈር ደረሰ። እስራኤልና ፍልስጥኤማውያን ቦታ ቦታቸውን ይዘው ፊት ለፊት ተፋጠው ይጠባበቁ ነበር። ዳዊት ዕቃውን ከስንቅ ጠባቂው ዘንድ አስቀምጦ ወደ ጦሩ ግንባር ሮጠ፤ ወንድሞቹንም አግኝቶ ደኅንነታቸውን ጠየቀ። ከእነርሱም ጋራ በሚነጋገርበት ጊዜ፣ ከጋት የመጣው ፍልስጥኤማዊው ጀግና ጎልያድ ከሰልፉ መካከል ወጥቶ እንደ ለመደው ሲደነፋ፤ ዳዊት ሰማ። እስራኤላውያንም ሰውየውን ባዩት ጊዜ ሁሉም በታላቅ ፍርሀት ከፊቱ ሸሹ። እስራኤላውያንም እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው በየቀኑ እየመጣ እስራኤልን እንደሚገዳደር ታያላችሁ? ይህን ሰው ለሚገድል፣ ንጉሡ ብዙ ሀብት ይሰጠዋል፤ ሴት ልጁን ይድርለታል፣ የአባቱንም ቤት በእስራኤል ዘንድ ከግብር ነጻ ያደርገዋል” ይባባሉ ነበር። ዳዊት በአጠገቡ የቆሙትን ሰዎች፣ “ለመሆኑ ይህን ፍልስጥኤማዊ ገድሎ እንዲህ ያለውን ውርደት ከእስራኤል ለሚያስወግድ ሰው ምን ይደረግለታል? ደግሞስ የሕያው እግዚአብሔርን ሰራዊት ይገዳደር ዘንድ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እርሱ ማነው?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም፣ “ለሚገድለው ሰው የሚደረግለትማ ይህ ነው” ሲሉ አስቀድመው ያሉትን ደግመው ነገሩት። ታላቅ ወንድሙ ኤልያብ፣ ዳዊት ከሰዎች ጋራ ሲነጋገር በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጥቶ፣ “ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂት በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውሃቸው? ትዕቢትህንና የልብህን ክፋት ዐውቃለሁ፤ የመጣኸው ጦርነቱን ለማየት ብቻ ነው” አለው። ዳዊትም፣ “ታዲያ ምን አደረግሁ? መጠየቅ እንኳ አልችልም?” አለ። ከዚያም ወደ ሌላ ሰው ዘወር ብሎ፣ ያንኑ ጥያቄ ጠየቀ፤ ሰዎቹም እንደ ቀድሞው መለሱለት፤ ዳዊት የተናገረው ነገር ወደ ሳኦል ጆሮ ደረሰ፤ ሳኦልም ልኮ አስጠራው። ዳዊትም ሳኦልን፣ “ከዚህ ፍልስጥኤማዊ የተነሣ የማንም ሰው ልብ አይሸበር፤ ባሪያህ ሄዶ ይዋጋዋል” አለው። ሳኦልም መልሶ “አንተ ገና አንድ ፍሬ ልጅ ነህ፣ ሰውየው ግን ከልጅነቱ ጀምሮ ውጊያ የተለማመደ ስለ ሆነ፣ ወጥተህ ይህን ፍልስጥኤማዊ ልትገጥመው አትችልም” አለው። ዳዊት ግን ሳኦልን እንዲህ አለው፣ “አገልጋይህ የአባቱን በጎች በሚጠብቅበት ጊዜ፤ አንበሳ ወይም ድብ መጥቶ ከመንጋው አንድ በግ ነጥቆ ሲሄድ፣ ተከትዬ በመሄድ እመታውና ከአፉ አስጥል ነበር፤ ፊቱን ወደ እኔ በሚያዞርበትም ጊዜ ጕረሮውን ይዤ በመምታት እገድለው ነበር። ባሪያህ አንበሳውንም ድቡንም ገድሏል፤ ይህም ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ የሕያው እግዚአብሔርን ሰራዊት ተገዳድሯልና መጨረሻው ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። ከአንበሳ መዳፍና ከድብ መንጋጋ ያዳነኝ እግዚአብሔር አሁንም ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያድነኛል።” ሳኦልም፣ “ሂድ፤ እግዚአብሔር ካንተ ጋራ ይሁን” አለው። ከዚያም ሳኦል ለዳዊት የገዛ ራሱን የጦር ልብስ አለበሰው፤ ጥሩር አጠለቀለት፤ ከናስ የተሠራ ቍርም ደፋለት። ዳዊትም ይህን ዐይነት ልብስ ለብሶ ስለማያውቅ፣ ሰይፉን በጦር ልብሱ ላይ ታጥቆ ለመራመድ ሞከረ። እርሱም ሳኦልን፣ “ያልተለማመድሁት ስለ ሆነ እንደዚህ ሆኜ መራመድ አልችልም” አለው። ስለዚህ ሁሉንም አወለቀው። ከዚያም በትሩን በእጁ ያዘ፤ ዐምስት ድቡልቡል ድንጋዮች ከወንዝ መርጦ በእረኛ ኰረጆው ከጨመረ በኋላ፣ ወንጭፉን በእጁ ይዞ፣ ወደ ፍልስጥኤማዊው ቀረበ። ፍልስጥኤማዊውም፣ ጋሻ ጃግሬውን እፊት እፊቱ በማስቀደም፣ ወደ ዳዊት እየቀረበ መጣ። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን ትኵር ብሎ ሲያየው፣ ደም ግባት ያለው፣ መልከ መልካምና አንድ ፍሬ ልጅ ነበር፤ ስለዚህ ናቀው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፣ “በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን?” አለው፤ በአማልክቱም ስም ረገመው። ፍልስጥኤማዊውም፣ “እስኪ ወደኔ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞሮችና፣ ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን እንዲህ አለው፤ “አንተ ሰይፍ፣ ጦርና ጭሬ ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን አንተ በተገዳደርኸው የእስራኤል ሰራዊት ጌታ በሆነው፣ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እኔ መትቼ እጥልሃለሁ፤ ራስህንም እቈርጠዋለሁ። በዚህች ዕለት የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ሬሣ ለሰማይ አሞሮችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ፣ ዓለምም ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ መኖሩን ያውቃል። እዚህ የተሰበሰቡትም ሁሉ፣ እግዚአብሔር የሚያድነው በሰይፍ ወይም በጦር እንዳልሆነ ያውቃሉ፤ ሰልፉ የእግዚአብሔር ስለ ሆነም ሁላችሁን በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።” ፍልስጥኤማዊው ሊመታው በቀረበ ጊዜ፣ ዳዊትም ሊገጥመው ወደ ውጊያው ሜዳ በፍጥነት ሮጠ። እጁንም ወደ ኰረጆው በመስደድ አንድ ድንጋይ አውጥቶ ወነጨፈው፤ ፍልስጥኤማዊውንም ግንባሩ ላይ መታው። ድንጋዩም ግንባሩ ውስጥ ገብቶ ተቀረቀረ፤ ፍልስጥኤማዊውም በግምባሩ ተደፋ። በዚህ ሁኔታ ዳዊት በወንጭፍና በድንጋይ ብቻ ፍልስጥኤማዊውን አሸነፈው፤ በእጁም ሰይፍ ሳይዝ ፍልስጥኤማዊውን መታው፤ ገደለውም። ዳዊት ሮጦ በላዩ ላይ ቆመ፤ ከዚያም የፍልስጥኤማዊውን ሰይፍ ከሰገባው መዝዞ አወጣው፤ እርሱንም ከገደለው በኋላ ራሱን በሰይፍ ቈረጠው። ፍልስጥኤማውያንም ጀግናቸው መሞቱን ባዩ ጊዜ ሸሹ።
1 ሳሙኤል 17:1-51 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ፍልስጥኤማውያንም ጭፍሮቻቸውን በይሁዳ ባለው በሰኮት አከማቹ፥ በሰኮትና በዓዜቃ መካከል በአርፌስደሚም ሰፈሩ። ሳኦልና የእስራኤል ሰዎች ተከማቹ፥ በዔላ ሸለቆም ሰፈሩ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ሊዋጉ ተሰለፉ። ፍልስጥኤማውያንም በአንድ ወገን በተራራ ላይ ቆመው ነበር፥ እስራኤልም በሌላው ወገን በተራራ ላይ ቆመው ነበር፥ በመካከላቸውም ሸለቆ ነበረ። ከፍልስጥኤማውያንም ሰፈር የጌት ሰው ጎልያድ፥ ቁመቱም ስድስት ክንድ ከስንዝር የሆነ፥ ዋነኛ ጀግና መጣ። በራሱም የናስ ቁር ደፍቶ ነበር፥ ጥሩርም ለብሶ ነበር፥ የጥሩሩም ሚዛን አምስት ሺህ ሰቅል ናስ ነበረ። በእግሮቹም ላይ የናስ ገምባሌ ነበረ፥ የናስም ጭሬ በትከሻው ላይ ነበረ። የጦሩም የቦ እንደ ሸማኔ መጠቅልያ ነበረ፥ የጦሩም ሚዛን ስድስት መቶ ሰቅል ብረት ነበረ፥ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር። እርሱም ቆሞ ወደ እስራኤል ጭፍሮች ጮኸ፦ ለሰልፍ ትሠሩ ዘንድ ለምን ወጣችሁ? እኔ ፍልስጥኤማዊ፥ እናንተም የሳኦል ባሪያዎች አይደላችሁምን? ለእናንተ አንድ ሰው ምረጡ፥ ወደ እኔም ይውረድ፥ ከእኔም ጋር ሊዋጋ ቢችል ቢገድለኝም፥ ባሪያዎች እንሆናችኋለን፥ እኔ ግን ባሸንፈው ብገድለውም፥ እናንተ ባሪያዎች ትሆኑናላችሁ፥ ለእኛም ትገዛላችሁ አለ። ፍልስጥኤማዊውም፦ ዛሬ የእስራኤልን ጭፎሮች ተገዳደርኋቸው፥ እንዋጋ ዘንድ አንድ ሰው ስጡኝ አለ። ሳኦልና እስራኤልም ሁሉ እንዲህ የሚላቸውን የፍልስጥኤማዊውን ቃል በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፥ ደነገጡም። ዳዊትም የዚያ የኤፍራታዊው ሰው ልጅ ነበረ፥ ያም ሰው ከቤተ ልሔም ይሁዳ ስሙም እሴይ ነበረ፥ ስምንትም ልጆች ነበሩት፥ በሳኦልም ዘመን በዕድሜ አርጅቶ ሸምግሎም ነበር። የእሴይም ሦስቱ ታላላቆች ልጆቹ ሳኦልን ተከትለው ወደ ሰልፉ ሄደው ነበር፥ ወደ ሰልፉም የሄዱት የሦስቱ ልጆቹ ስም ይህ ነበረ፥ ታላቁ ኤልያብ ሁለተኛውም አሚናዳብ ሦስተኛውም ሣማ ነበረ። ዳዊት የሁሉ ታናሽ ነበረ፥ ሦስቱም ታላላቆች ሳኦልን ተከትለው ነበር። ዳዊትም የአባቱን በጎች ለመጠበቅ ከሳኦል ዘንድ ወደ ቤተ ልሔም ይመላለስ ነበር። ፍልስጥኤማዊውም ጥዋትና ማታ ይቀርብ፥ አርባ ቀንም ይታይ ነበር። እሴይም ልጁን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ ከዚህ ከተጠበሰው እሸት አንድ የኢፍ መስፈሪያ እነዚህንም አሥር እንጀራዎች ለወንድሞችህ ውሰድ፥ ወደ ሰፈሩም ወደ ወንድሞችህ ፈጥነህ አድርሳቸው፥ ይህንም አሥሩን አይብ ወደ ሻለቃው ውሰደው፥ የወንድሞችህንም ደኅንነት ጠይቅ፥ ወሬአቸውንም አምጣልኝ። ሳኦልና እነርሱ የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ከፍልስጥኤማውያን ጋር እየተዋጉ በዔላ ሸለቆ ነበሩ። ዳዊትም ማልዶ ተነሣ፥ በጎቹንም ለጠባቂ ተወ፥ እሴይም ያዘዘውን ይዞ ሄደ፥ ጭፍራውም ተሰልፎ ሲወጣ ለሰልፍም ሲጮኽ በሰረገሎች ወደ ተከበበው ሰፈር መጣ። እስራኤልና ፍልስጥኤማውያን ፊት ለፊት ተሰላልፈው ነበረ። ዳዊትም ዕቃውን በዕቃ ጠባቂው እጅ አኖረው፥ ወደ ሠራዊቱም ሮጠ፥ የወንድሞቹንም ደኅንነት ጠየቀ። እርሱም ሲነጋገራቸው፥ እነሆ፥ ጎልያድ የተባለው ያ ዋነኛ ጀግና ፍልስጥኤማዊ የጌት ሰው ከፍልስጥኤማውያን ጭፍራ መካከል ወጣ፥ የተናገረውንም ቃል ተናገረ፥ ዳዊትም ሰማ። የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ሰውዮውን ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው ከእርሱ ሸሹ። የእስራኤልም ሰዎች፦ ይህን የወጣውን ሰው አያችሁትን? በእውነት እስራኤልን ሊገዳደር ወጣ፥ የሚገድለውንም ሰው ንጉሡ እጅግ ባለጠጋ ያደርገዋል፥ ልጁንም ይድርለታል፥ ያባቱንም ቤተ ሰብ በእስራኤል ዘንድ ከግብር ነጻ ያወጣቸዋል አሉ። ዳዊትም በአጠገቡ ለቆሙት ሰዎች፦ ይህን ፍልስጥኤማዊ ለሚገድል፥ ከእስራኤልም ተግዳሮትን ለሚያርቅ ሰው ምን ይደረግለታል? የሕያውን አምላክ ጭፍሮች የሚገዳደር ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ ማን ነው? ብሎ ተናገራቸው። ሕዝቡም፦ ለሚገድለው ሰው እንዲህ ይደረግለታል ብለው እንደ ቀድሞው መለሱለት። ታላቅ ወንድሙም ኤልያብ ከሰዎች ጋር ሲነጋገር ሰማ፥ የኤልያብም ቁጣ በዳዊት ላይ ነድዶ፦ ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂቶች በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውሃቸው? እኔ ኩራትህንና የልብህን ክፋት አውቃለሁና ሰልፉን ለማየት መጥተሃል አለው። ዳዊትም፦ እኔ ምን አደረግሁ? ይህ ታላቅ ነገር አይደለምን? አለ። ዳዊትም ከእርሱ ወደ ሌላ ሰው ዘወር አለ፥ እንደዚህም ያለ ነገር ተናገረ፥ ሕዝቡም እንደ ቀድሞው ያለ ነገር መለሱለት። ዳዊትም የተናገረው ቃል ተሰማ፥ ለሳኦልም ነገሩት፥ ወደ እርሱም አስጠራው። ዳዊትም ሳኦልን፦ ስለ እርሱ የማንም ልብ አይውደቅ፥ እኔ ባሪያህ ሄጄ ያንን ፍልስጥኤማዊ እወጋዋለሁ አለው። ሳኦልም ዳዊትን፦ አንተ ገና ብላቴና ነህና፥ እርሱም ከብላቴንነቱ ጀምሮ ጦረኛ ነውና ይህን ፍልስጥኤማዊ ለመውጋት ትሄድ ዘንድ አትችልም አለው። ዳዊትም ሳኦልን አለው፦ እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳና ድብ ይመጣ ነበር፥ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር። በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር፥ ከአፉም አስጥለው ነበር፥ በተነሣብኝም ጊዜ ጉሮሮውን ይዤ እመታውና እገድለው ነበር። እኔ ባሪያህ አንበሳና ድብ መታሁ፥ ይህም ያልተገረዘው ፍልስጥኤማዊ የሕያውን አምላክ ጭፍሮች ተገዳድሮአልና ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። ዳዊትም፦ ከአንበሳና ከድብ እጅ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል አለ። ሳኦልም ዳዊትን፦ ሂድ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል አለው። ሳኦልም ዳዊትን የገዛ ራሱን ልብስ አለበሰው፥ በራሱም ላይ የናስ ቁር ደፋለት፥ ጥሩርም አለበሰው። ዳዊትም ሰይፉን በልብሱ ላይ ታጠቀ፥ ገናም አልፈተነውምና መሄድ ሞከረ። ዳዊትም ሳኦልን፦ አልፈተንሁትምና እንዲህ ብዬ መሄድ አልችልም አለው። ዳዊትም አወለቀ። በትሩንም በእጁ ወሰደ፥ ከወንዝም አምስት ድብልብል ድንጋዮችን መረጠ፥ በእረኛ ኮረጆውም በኪሱ ከተታቸው፥ ወንጭፍም በእጁ ነበረ፥ ወደ ፍልስጥኤማዊውም ቀረበ። ፍልስጥኤማዊውም መጥቶ ወደ ዳዊት ቀረበ፥ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር። ጎልያድም ዳዊትን ትኩር ብሎ አየው፥ ቀይ ብላቴና መልኩም ያማረ ነበረና ናቀው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፦ በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን? አለው። ፍልስጥኤማዊውም በአምላኮቹ ስም ዳዊትን ረገመው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፦ ወደ እኔ ና፥ ሥጋህንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ አለው። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን አለው፦ አንተ ሰይፍና ጦር ጭሬም ይዘህ ትመጣብኛለህ፥ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፥ እመታህማለሁ፥ ራስህንም ከአንተ አነሣዋለሁ፥ የፍልስጥኤማውያንንም ሠራዊት ሬሶች ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ዛሬ እሰጣለሁ። ይኸውም ምድር ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ እንዳለ ታውቅ ዘንድ፥ ይህም ጉባኤ ሁሉ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን እንዳይደል ያውቅ ዘንድ ነው። ሰልፉ ለእግዚአብሔር ነውና፥ እናንተንም በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል። ፍልስጥኤማዊውም ተነሥቶ ዳዊትን ሊገናኘው በቀረበ ጊዜ ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ሊገናኘው ወደ ሰልፉ ሮጠ። ዳዊትም እጁን ወደ ኮረጆው አግብቶ አንድ ድንጋይ ወሰደ፥ ወነጨፈውም፥ ፍልስጥኤማዊውንም ግምባሩን መታ፥ ድንጋዩም በግምባሩ ተቀረቀረ፥ እርሱም በምድር ላይ በፊቱ ተደፋ። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን በወንጭፍና በድንጋይ አሸነፈው፥ ፍልስጥኤማዊውንም መትቶ ገደለ፥ በዳዊትም እጅ ሰይፍ አልነበረም። ዳዊትም ሮጦ በፍልስጥኤማዊው ላይ ቆመ፥ ሰይፉንም ይዞ ከሰገባው መዘዘው፥ ገደለውም፥ ራሱንም ቆረጠው። ፍልስጥኤማውያንም ዋናቸው እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ ሸሹ።
1 ሳሙኤል 17:1-51 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ፍልስጥኤማውያን ሶኮ ተብላ በምትጠራው በይሁዳ ለጦርነት ተሰለፉ፤ እነርሱም በሶኮና በዐዜቃ መካከል ኤፌስዳሚም ተብሎ በሚጠራው ቦታ ሰፍረው ነበር። ሳኦልና እስራኤላውያንም ፍልስጥኤማውያንን ለመውጋት በተዘጋጁበት በኤላ ሸለቆ ተሰብስበው መሸጉ። በመካከላቸው አንድ ሸለቆ ሲኖር በአንድ በኩል ባለው ኮረብታ ፍልስጥኤማውያን፥ በሌላ በኩል ባለው ኮረብታ እስራኤላውያን ተሰልፈው ነበር። ከጋት ከተማ የመጣ፥ ጎልያድ ተብሎ የሚጠራ አንድ ግዙፍ ሰው፥ ከፍልስጥኤማውያን ሰፈር ወጥቶ እስራኤላውያንን መፈታተን ጀመረ፤ የዚያም ሰው ቁመት ሦስት ሜትር ያኽል ነበር፤ ከነሐስ የተሠራና ክብደቱ ኀምሳ ሰባት ኪሎ የሚሆን ጥሩርና ከነሐስ የተሠራ የራስ ቊር ነበረው። እግሮቹም ከነሐስ በተሠራ ገንባሌ የተሸፈኑ ነበሩ፤ ከነሐስ የተሠራ ጦርም በትከሻው ነበር፤ የጦሩ ዘንግ ውፍረቱ የሸማኔ መጠቅለያ ያኽል ነበር፤ የጦሩም ብረት ክብደቱ ሰባት ኪሎ ያኽል ነበር፤ ጋሻውንም ጋሻጃግሬው ተሸክሞለት በፊት በፊቱ ይሄድ ነበር። ጎልያድ ተነሥቶ በመቆም በእስራኤል ሠራዊት ላይ እንዲህ እያለ ይደነፋባቸው ጀመር፦ “አሁን በዚያ ቦታ ለጦርነት የተሰለፋችሁት ከቶ ምን ልታደርጉ ነው? እኔ ፍልስጥኤማዊ ነኝ፤ እናንተ ደግሞ የሳኦል ባሪያዎች ናችሁ፤ እንግዲህ ከእኔ ጋር የሚዋጋ አንድ ሰው ከወታደሮቻችሁ መካከል ምረጡና ወደ እኔ መጥቶ ይግጠመኝ። እርሱ እኔን አሸንፎ ከገደለኝ፥ እኛ የእናንተ ባሪያዎች ሆነን እንገዛላችኋለን፤ ነገር ግን እኔ አሸንፌ ከገደልኩት፥ እናንተ የእኛ ባርያዎች ሆናችሁ ትገዙልናላችሁ። እነሆ እኔ ዛሬ በዚህ የእስራኤልን ሠራዊት እፈታተናለሁ! ከእኔ ጋር የሚዋጋ አንድ ሰው ስጡኝ!” አለ። ሳኦልና ወታደሮቹም የፍልስጥኤማዊውን ቃል በሰሙ ጊዜ በፍርሃት ተንቀጠቀጡ። ዳዊት በይሁዳ በምትገኘው በቤተልሔም የሚኖር የኤፍራታዊው የእሴይ ልጅ ነበር፤ እሴይ ስምንት ልጆች ያሉት ሲሆን ሳኦል በነገሠበት ዘመን በዕድሜ የገፋ ሽማግሌ ሰው ነበር። ሦስቱ ታላላቅ ልጆቹም ከሳኦል ጋር ወደ ጦርነት ዘምተው ነበር፤ እነርሱም በኲሩ ኤሊአብ፥ ሁለተኛው አሚናዳብ፥ ሦስተኛውም ሻማ ተብለው ይጠሩ ነበር። ዳዊት የሁሉ ታናሽ ሲሆን፥ ሦስት ታላላቅ ወንድሞቹ ሳኦልን ተከትለው ነበር። ዳዊት በየጊዜው ከሳኦል ዘንድ እየተመላለሰ በቤተልሔም የአባቱን በጎች ይጠብቅ ነበር። ፍልስጥኤማዊውም ለአርባ ቀኖች በፊታቸው እየመጣ ቆሞ ይፎክር ነበር። አንድ ቀን እሴይ ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ዐሥር ኪሎ የተጠበሰ እሸትና ዐሥር የዳቦ ሙልሙል ያዝ፤ ፈጥነህም በመሄድ በጦር ሰፈር ለሚገኙት ወንድሞችህ አድርስላቸው። እነዚህንም ዐሥር የአይብ ጥፍጥፎች ለሻለቃው የጦር አዛዥ ስጠው፤ ወንድሞችህም እንዴት እንዳሉ በዐይንህ አይተህ የደኅንነታቸውን መረጃ አምጣልኝ። ንጉሥ ሳኦል፥ ወንድሞችህና መላው እስራኤላውያን በኤላ ሸለቆ ከፍልስጥኤማውያን ጋር በመዋጋት ላይ ናቸው።” ዳዊትም በማግስቱ ማልዶ ተነሣ፤ በጎቹን ለሌላ እረኛ በመተው እሴይ ባዘዘው መሠረት የተዘጋጀውን ምግብ ይዞ ሄደ፤ እስራኤላውያን ጦርነት ለመግጠም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በሚደነፉበት ጊዜ ዳዊት ወደ ጦሩ ሰፈር ደረሰ። የፍልስጥኤማውያን ሠራዊትና የእስራኤላውያን ሠራዊት ቦታ ቦታቸውን ይዘው በጦሩ ግንባር ፊት ለፊት በመተያየት ላይ ነበሩ። ዳዊትም የያዘውን ምግብ ለስንቅ ጠባቂው ትቶ ወደ ጦሩ ግንባር እየሮጠ ወደ ወንድሞቹ ሄደ፤ ስለ ደኅንነታቸውም ጠየቃቸው። ዳዊትም ከወንድሞቹ ጋር በመነጋገር ላይ ሳለ እነሆ፥ ጎልያድ የተባለው ግዙፍ ፍልስጥኤማዊ የጋት ሰው ከዚያ በፊት ያደርገው እንደ ነበር ወደፊት በማምራት በእስራኤላውያን ላይ መፎከሩን ቀጠለ፤ ዳዊትም የእርሱን ድንፋታ ሰማ። እስራኤላውያንም ጎልያድን ባዩ ጊዜ በታላቅ ፍርሀት ሸሹ። እስራኤላውያንም እርስ በርሳቸውም እንዲህ ይባባሉ ነበር፤ “ይህ በየቀኑ እስራኤልን ለመፈታተን የሚወጣውን ሰው ታያላችሁን? ንጉሥ ሳኦል እርሱን ለሚገድልለት ሰው ብዙ ሀብት ለመስጠት ቃል ገብቶአል፤ ሴት ልጁንም እንደሚድርለትና የአባቱም ቤተሰብ ከግብር ነጻ እንደሚያደርግለት ተናግሮአል።” ዳዊትም በአጠገቡ የቆሙትን ሰዎች “ይህን ፍልስጥኤማዊ ገድሎ እስራኤልን ከዚህ አሳፋሪ ውርደት ለሚያድን ሰው ምን ይደረግለታል? ኧረ ለመሆኑ የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት የሚፈታተን ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ ማን ነው?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም ጎልያድን ለሚገድል ሰው ምን እንደሚደረግለት ነገሩት። የዳዊት ታላቅ ወንድም ኤሊአብም ዳዊት ከሰዎቹ ጋር ሲነጋገር ሰማ፤ እርሱም በዳዊት ላይ በጣም ተቈጥቶ “እዚህ ምን ትሠራለህ? በበረሓ ያሉትንስ እነዚያን ጥቂቶች በጎችህን ለማን ተውካቸው? እኔ ትዕቢተኛነትህንና የልብህን ክፋት ዐውቃለሁ! አሁን የመጣኸው እኮ የጦርነቱን ሁኔታ ለመመልከት ነው!” አለው። ዳዊትም “አሁን እኔ ምን አደረግሁ? ለመጠየቅ እንኳ አልችልምን?” ሲል መለሰለት፤ ከዚያም ወደ ሌላው ሰው መለስ ብሎ ያንኑ ጥያቄ አቀረበለት፤ በጠየቀ ቊጥር የሚያገኘው መልስ ተመሳሳይ ነበር። አንዳንድ ሰዎች ዳዊት የተናገረውን ቃል ሰምተው ስለ ነበር፥ ሄደው ለሳኦል ነገሩት፤ ሳኦልም ልኮ ዳዊትን አስጠራው። ዳዊትም ሳኦልን “ንጉሥ ሆይ! ከዚህ ፍልስጥኤማዊ የተነሣ ማንም ሰው መፍራት የለበትም! እኔ ያንተ አሽከር ሄጄ እርሱን እዋጋዋለሁ” አለው። ሳኦልም ዳዊትን፦ “አንተ ገና ልጅ ነህ፤ እርሱም ከልጅነቱ ጀምሮ ጦረኛ ስለ ሆነ ይህን ፍልስጥኤማዊ ለመውጋት ትሄድ ዘንድ አትችልም” አለው። ዳዊትም እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ ሆይ! እኔ ያንተ አሽከር የአባቴን በጎች የምጠብቅ እረኛ ነኝ፤ አንበሳም ሆነ ድብ መጥቶ ጠቦት በሚነጥቅበት ጊዜ፥ ተከትዬው ሄጄ አደጋ በመጣል የወሰደውን ጠቦት አስጥለው ነበር፤ አንበሳው ወይም ድቡ ወደ እኔ ተመልሶ በሚመጣበትም ጊዜ ጉሮሮውን አንቄ በመምታት እገድለው ነበር። እኔ ያንተ አሽከር አንበሳና ድብ ገድያለሁ፤ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት ስለ ተፈታተነ ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። ከአንበሳና ድብ ያዳነኝ እግዚአብሔር ከዚህም ፍልስጥኤማዊ እጅ ያድነኛል።” ሳኦልም “መልካም ነው! እንግዲህ ሂድ፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን!” ሲል መለሰለት። ሳኦልም የገዛ ራሱን የጦር ልብስ ለዳዊት አለበሰው፤ ከነሐስ የተሠራውን የራስ ቊር በዳዊት ራስ ላይ ደፍቶ ጥሩርም አለበሰው፤ ዳዊትም ይህን ዐይነት ልብስ ለብሶ ስለማያውቅ ሰይፉን በጦር ልብሱ ላይ ታጥቆ ለመሄድ ሲነሣ መራመድ አልቻለም፤ ስለዚህ ዳዊት ሳኦልን፦ “ያልተለማመድኩት ነገር ስለ ሆነ ይህን ሁሉ ልብስ ለብሼ መዋጋት አልችልም፤” አለ፤ ስለዚህም ያንን ሁሉ አወለቀ፤ በትሩን አንሥቶ፥ ከወንዝ ዳር አምስት ድቡልቡል ድንጋዮች መርጦ በመልቀም በእረኝነት ኮረጆው ከተተ፤ ወንጭፉንም ይዞ ወደ ፍልስጥኤማዊው ቀረበ። ፍልስጥኤማዊው ጎልያድ ወደ ዳዊት ለመቅረብ መራመድ ጀመረ፤ ጋሻጃግሬውም በፊት በፊቱ ይሄድ ነበር፤ ዳዊት ቀይ፥ መልከ መልካም፥ ትንሽ ልጅ ስለ ነበረ ዳዊትን ጎልያድ ትኲር ብሎ ባየው ጊዜ በንቀት ዐይን ተመለከተው፤ ስለዚህም ጎልያድ ዳዊትን “በትር ይዘህ የምትመጣው እኔ ውሻ ነኝን” ካለው በኋላ በአማልክቱ ስም ረገመው። ቀጥሎም “ወዲህ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞራዎችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው። ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰ “አንተ ሰይፍ፥ ጦርና ሾተል ይዘህ መጥተህብኛል፤ እኔ ደግሞ አንተ በምትፈታተነውና በእስራኤል ሠራዊት አምላክ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ፤ በዚህች ቀን እግዚአብሔር በአንተ ላይ ድልን ያጐናጽፈኛል፤ እኔም ራስህን እቈርጣለሁ፤ የፍልስጥኤማውያንንም ወታደሮች ሥጋ ለአሞራዎችና ለአራዊት ምግብ አድርጌ እሰጣለሁ፤ ከዚያም በኋላ መላው ዓለም በእስራኤል ዘንድ አምላክ እንዳለ ያውቃል። እዚህ የተሰበሰቡት ሁሉ እግዚአብሔር የሚያድነው በሰይፍና በጦር አለመሆኑን ያውቃሉ፤ ጦርነቱ የእግዚአብሔር ነውና፤ በእናንተም ላይ ድልን እንድንጐናጸፍ ያደርገናል።” ፍልስጥኤማዊው አደጋ ሊጥልበት ወደ ዳዊት በቀረበ ጊዜ ዳዊት ጎልያድን ለመግጠም ወደ ጦሩ ግንባር እየሮጠ ሄደ። እጁንም ወደ ኮረጆው ከቶ አንዲት ድንጋይ በማውጣት በጎልያድ ላይ ወነጨፈ፤ ድንጋዩም ግንባሩን በጥርቆ ወደ ራስ ቅሉ ገባ፤ ጎልያድም በምድር ላይ በግንባሩ ተደፋ። በዚህም ዐይነት ዳዊት በወንጭፍና በድንጋይ ጎልያድን መትቶ በመግደል ድል አደረገ! በእጁም ሰይፍ አልነበረም። ወደ እርሱም ሮጦ በመሄድ በላዩ ላይ ቆመ፤ የጎልያድንም ሰይፍ ከሰገባው በመምዘዝ ራሱን ቈረጠው። ፍልስጥኤማውያንም የእነርሱ ዝነኛ ተዋጊ ጎልያድ መገደሉን ባዩ ጊዜ ሸሹ።
1 ሳሙኤል 17:1-51 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ፍልስጥኤማውያን ሠራዊታቸውን ለጦርነት አሰባስበው፥ በይሁዳ ምድር በሰኮ ላይ አከማቹ፤ በሰኮና በዓዜቃ መካከል ባለው በኤፌስደሚምም ሰፈሩ። ሳኦልና እስራኤላውያን ደግሞ ተሰብስበው በዔላ ሸለቆ ሰፈሩ፤ ፍልስጥኤማውያንንም ለመግጠም ተሰለፉ። በመካከላቸው ሸለቆ ሆኖ፥ ፍልስጥኤማውያን አንዱን ተራራ እስራኤላውያን ደግሞ ሌላውን ተራራ ያዙ። ከጋት ከተማ የመጣ፥ ቁመቱ ስድስት ክንድ ከስንዝር የነበር ጎልያድ ተብሎ የሚጠራ አንድ ግዙፍ ዋነኛ ጀግና ሰው፥ ከፍልስጥኤማውያን ሰፈር ወጣ። እርሱም ከናስ የተሠራ የናስ ቁር ደፍቶ፥ ክብደቱ አምስት ሺህ ሰቅል የሆነ የናሐስ ጥሩርም ለብሶ ነበር። በእግሮቹም ላይ የሐናስ ገምባሌ አድርጎ፥ በጫንቃው ላይ ደግሞ የናሐስ ጭሬ ይዞ ነበር። የጦሩም ዘንግ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የወፈረ፥ የጦሩም ብረት ስድስት መቶ ሰቅል ያህል የሚመዝን ነበር፤ ጋሻ ጃግሬውም ከፊት ከፊቱ ይሄድ ነበር። ጎልያድ ቆሞ ለተሰለፈው የእስራኤል ሠራዊት እንዲህ ሲል ጮኾ ተናገረ፤ “ለውጊያ ተሰልፋችሁ መውጣታችሁ ስለ ምንድነው? እኔ ፍልስጥኤማዊ፥ እናንተም የሳኦል አገልጋዮች አይደላችሁምን? አንድ ሰው ምረጡና እኔ ወደ አለሁበት ይውረድ፤ ከእኔ ጋር ሊዋጋና ሊገድለኝ ከቻለ፥ እኛ ባርያዎቻችሁ እንሆናለን፤ እኔ ባሸንፈውና ብገድለው ግን እናንተ ባርያዎቻችን ትሆናላችሁ፤ ትገዙልናላችሁ።” ከዚያም ፍልስጥኤማዊው፥ “ዛሬ የእስራኤልን ሠራዊት እገዳደራለሁ፤ እንዋጋ ዘንድ ሰው ስጡኝ” አለ። ሳኦልና እስራኤላውያን ሁሉ የፍልስጥኤማዊውን ቃል በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፤ ደነገጡም። ዳዊት፥ በይሁዳ ስምንት ወንዶች ልጆች የነበሩት፥ የቤተልሔሙ ሰው የኤፍራታዊው የእሴይ ልጅ ነበር። እሴይም በሳኦል ዘመን ያረጀና ዕድሜው የገፋ ሰው ነበር። ሦስቱ የእሴይ ታላላቅ ልጆች ሳኦልን ተከትለው ወደ ጦርነት ሄደው ነበር፤ እነርሱም ታላቁ ኤሊአብ፥ ሁለተኛው አሚናዳብ፥ ሦስተኛውም ሻማ ይባላሉ፤ ዳዊት የሁሉም ታናሽ ነበር። ሦስቱ ታላላቅ ወንድሞቹ ሳኦልን ተከትለው ሄዱ፤ ዳዊት ግን የአባቱን በጎች ለመጠበቅ ከሳኦል ዘንድ ወደ ቤተልሔም ይመላለስ ነበር። ፍልስጥኤማዊውም አርባ ቀን ሙሉ ጠዋትና ማታ እየመጣ በመቆም ይታያቸው ነበር። በዚህ ጊዜ እሴይ ልጁን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ይህን ዐሥር ኪሎ የተጠበሰ እሸትና ዐሥር እንጀራ ለወንድሞችህ ይዘህ ወዳሉበት የጦር ሰፈር በቶሎ ድረስ። ይህንም ዐሥር የአይብ ጥፍጥፍ ለሻለቃው የጦር አዛዥ አብረህ ውሰድ፤ ወንድሞችህም እንዴት እንደ ሆኑ አይተህ፥ ደኅንነታቸውን የሚያረጋግጥ ምልክት ከእነርሱ ዘንድ አምጣልኝ። እነርሱ ከሳኦልና ከእስራኤል ሰዎች ሁሉ ጋር ሆነው በዔላ ሸለቆ ከፍልስጥኤማውያን ጋር እየተዋጉ ናቸው።” ዳዊት በማለዳ በጎቹን ለጠባቂ ትቶ፥ እሴይ እንዳዘዘው ዕቃውን ይዞ ጉዞ ጀመረ። ልክ ሠራዊቱ እየፎከረ ለውጊያ ቦታ ቦታውን ለመያዝ በሚወጣበት ጊዜ ከጦሩ ሰፈር ደረሰ። እስራኤልና ፍልስጥኤማውያን ቦታ ቦታቸውን ይዘው ፊት ለፊት ተፋጠው ይጠባበቁ ነበር። ዳዊት ዕቃውን ከስንቅ ጠባቂው ዘንድ አስቀምጦ ወደ ጦሩ ግንባር ሮጠ፤ ወንድሞቹንም አግኝቶ ደኅንነታቸውን ጠየቀ። ከእነርሱም ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ፥ እነሆ፥ ከጌት የመጣው ፍልስጥኤማዊው ጀግና ጎልያድ ከሰልፉ መካከል ወጥቶ እንደ ለመደው ሲደነፋ ዳዊት ሰማ። እስራኤላውያንም ሰውየውን ባዩት ጊዜ ሁሉም በታላቅ ፍርሃት ከፊቱ ሸሹ። እስራኤላውያንም እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው በየቀኑ እየመጣ እስራኤልን እንደሚገዳደር ታያላችሁ? ይህን ሰው ለሚገድል፥ ንጉሡ ብዙ ሀብት ይሰጠዋል፤ ሴት ልጁን ይድርለታል፥ የአባቱንም ቤት በእስራኤል ዘንድ ከግብር ነጻ ያደርገዋል” ይባባሉ ነበር። ዳዊት በአጠገቡ የቆሙትን ሰዎች፥ “ይህን ፍልስጥኤማዊ ገድሎ እንዲህ ያለውን ውርደት ከእስራኤል ለሚያስወግድ ሰው ምን ይደረግለታል? ደግሞስ የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት ይገዳደር ዘንድ ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እርሱ ማነው?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም፥ “ለሚገድለው ሰው የሚደረግለትማ ይህ ነው” ሲሉ አስቀድመው ያሉትን ደግመው ነገሩት። ታላቅ ወንድሙ ኤሊአብ፥ ዳዊት ከሰዎች ጋር ሲነጋገር በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጥቶ፥ “ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂት በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውካቸው? ዕብሪትህንና የልብህን ክፋት ዐውቃለሁ፤ የመጣኸው ጦርነቱን ለማየት ብቻ ነው” አለው። ዳዊትም፥ “እኔ ምን አደረግሁ? መጠየቅ እንኳ አልችልምን?” አለ። ከዚያም ወደ ሌላ ሰው ዘወር ብሎ፥ ያንኑ ጥያቄ ጠየቀ፤ ሰዎቹም እንደ ቀድሞው መለሱለት፤ ዳዊት የተናገረው ነገር ወደ ሳኦል ጆሮ ደረሰ፤ ሳኦልም ልኮ አስጠራው። ዳዊትም ሳኦልን፥ “ከዚህ ፍልስጥኤማዊ የተነሣ የማንም ሰው ልብ አይሸበር፤ እኔ አገልጋይህ ሄጄ እዋጋዋለሁ” አለው። ሳኦልም መልሶ “አንተ ገና ልጅ ነህ፥ ሰውየው ግን ከልጅነቱ ጀምሮ ውጊያ የተለማመደ ስለሆነ፥ ወጥተህ ይህን ፍልስጥኤማዊ ልትገጥመው አትችልም” አለው። ዳዊት ግን ሳኦልን እንዲህ አለው፥ “አገልጋይህ የአባቱን በጎች በሚጠብቅበት ጊዜ፤ አንበሳ ወይም ድብ መጥቶ ከመንጋው አንድ በግ ነጥቆ ሲሄድ፥ ተከትዬ በመሄድ እመታውና ከአፉ አስጥል ነበር፤ ፊቱን ወደ እኔ በሚያዞርበትም ጊዜ ጉሮሮውን ይዤ በመምታት እገድለው ነበር። ባርያህ አንበሳውንም ድቡንም ገድሏል፤ ይህም ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ የሕያው እግዚአብሔርን ሠራዊት ተገዳድሯልና መጨረሻው ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። ከአንበሳ መዳፍና ከድብ መንጋጋ ያዳነኝ ጌታ አሁንም ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያድነኛል።” ሲል ዳዊት ተናገረ። ሳኦልም ዳዊትን፥ “ሂድ፤ ጌታ ካንተ ጋር ይሁን!” አለው። ከዚያም ሳኦል ለዳዊት የገዛ ራሱን የጦር ልብስ አለበሰው፤ ከናሐስ የተሠራ ቁር ደፋለት፤ ጥሩርም አለበሰው። ዳዊትም ይህን ዓይነት ልብስ ለብሶ ስለማያውቅ፥ ሰይፉን በጦር ልብሱ ላይ ታጥቆ ለመራመድ ሞከረ፤ እርሱም ሳኦልን፥ “ያልተለማመድሁት ስለሆነ እንደዚህ ሆኜ መራመድ አልችልም” አለው። ስለዚህ ያንን አወለቀው። ከዚያም በትሩን በእጁ ያዘ፤ አምስት ድቡልቡል ድንጋዮች ከወንዝ መርጦ በእረኛ ኮረጆው ከጨመረ በኋላ፥ ወንጭፉን በእጁ ይዞ ወደ ፍልስጥኤማዊው ቀረበ። ፍልስጥኤማዊውም፥ ጋሻ ጃግሬውን ከፊት ከፊቱ በማስቀደም፥ ወደ ዳዊት እየቀረበ መጣ። እርሱም ዳዊትን ትኩር ብሎ ሲያየው፥ ደም ግባት ያለው፥ መልከ መልካምና ልጅ ነበር፤ ስለዚህ በንቀት ዐይን ተመለከተው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፥ “በትር ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን?” አለው፤ በአማልክቱም ስም ረገመው። እርሱም ዳዊትን፥ “እስቲ ወደኔ ና! ሥጋህን ለሰማይ አሞሮችና፥ ለምድር አራዊት እሰጣለሁ” አለው። ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን እንዲህ አለው፤ “አንተ ሰይፍ፥ ጦርና ጭሬ ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን አንተ በተገዳደርኸው የእስራኤል ሠራዊት አምላክ በሆነው፥ ሁሉን በሚችል በሠራዊት ጌታ ስም እመጣብሃለሁ። ጌታ ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እኔ መትቼ እጥልሃለሁ፤ ራስህንም እቆርጠዋለሁ። በዚህች ዕለት የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ሬሣ ለሰማይ አሞሮችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ፤ ዓለምም ሁሉ በእስራኤል ዘንድ እግዚአብሔር መኖሩን ያውቃል። እዚህ የተሰበሰቡትም ሁሉ ጌታ ያለ ሰይፍ ወይም ያለ ጦር እንደሚያድን ያውቃሉ፤ ሰልፉ የጌታ ስለ ሆነም ሁላችሁን በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።” ፍልስጥኤማዊው ሊመታው በቀረበ ጊዜ፥ ዳዊትም ሊገጥመው ወደ ውጊያው ሜዳ በፍጥነት ሮጠ። እጁንም ወደ ኮሮጆው በመስደድ አንድ ድንጋይ አውጥቶ ወነጨፈው፤ ፍልስጥኤማዊውንም ግንባሩ ላይ መታው። ድንጋዩም ግንባሩ ውስጥ ገብቶ ተቀረቀረ፤ በግምባሩም ምድር ላይ ተደፋ። በዚህ ሁኔታ ዳዊት በወንጭፍና በድንጋይ ብቻ ፍልስጥኤማዊውን አሸነፈው፤ በእጁም ሰይፍ ሳይዝ ፍልስጥኤማዊውን መታው፤ ገደለውም። ዳዊት ሮጦ በላዩ ላይ ቆመ፤ ከዚያም የፍልስጥኤማዊውን ሰይፍ ከሰገባው መዞ አወጣው፤ እርሱንም ከገደለው በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጠው። ፍልስጥኤማውያንም ጀግናቸው መሞቱን ባዩ ጊዜ ሸሹ።