1 ሳሙኤል 16:1-23
1 ሳሙኤል 16:1-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ሳሙኤልን፥ “በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? የዘይቱን ቀንድ ሞልተህ ና፤ በልጆቹ መካከል ለእኔ ንጉሥ አዘጋጅቼአለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተ ልሔም እልክሃለሁ” አለው። ሳሙኤልም፥ “እንዴት እሄዳለሁ? ሳኦል ቢሰማ ይገድለኛል” አለ። እግዚአብሔርም፥ “አንዲት ጊደር ይዘህ ሂድና፦ ‘ለእግዚአብሔር እሠዋ ዘንድ መጣሁ’ በል። እሴይንም ወደ መሥዋዕቱ ጥራው፥ የምታደርገውንም አስታውቅሃለሁ፤ የምነግርህንም ቅባው” አለው። ሳሙኤልም እግዚአብሔር የተናገረውን አደረገ፤ ወደ ቤተ ልሔምም መጣ። የከተማውም ሽማግሌዎች በተገናኙት ጊዜ ደነገጡ፥ “ነቢይ! የመጣኸው ለሰላም ነውን?” አሉት። እርሱም፥ “ለሰላም ነው፤ ለእግዚአብሔር እሠዋ ዘንድ መጣሁ፤ ቅዱሳን ሁኑ፤ ከእኔም ጋር ዛሬ ደስ ይበላችሁ፤ ከእኔም ጋር ወደ መሥዋዕቱ ኑ” አለ። እሴይንና ልጆቹንም ቀደሳቸው፤ ወደ መሥዋዕቱም ጠራቸው። እንዲህም ሆነ፤ በመጡ ጊዜ ወደ ኤልያብ ተመልክቶ፥ “በእውነት እግዚአብሔር የሚቀባው በፊቱ ነው” አለ። እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፥ “ፊቱን፥ የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፤ ሰው እንደሚያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፤ ሰው ፊትን ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” አለው። እሴይም አሚናዳብን ጠርቶ በሳሙኤል ፊት አሳለፈው፤ እርሱም፥ “ይህን ደግሞ እግዚአብሔር አልመረጠውም” አለ። እሴይም ሣማዕን አሳለፈው፤ እርሱም፥ “ይህን ደግሞ እግዚአብሔር አልመረጠውም” አለ። እሴይም ከልጆቹ ሰባቱን በሳሙኤል ፊት አሳለፋቸው። ሳሙኤልም እሴይን፥ “እግዚአብሔር እነዚህን አልመረጠም” አለው። ሳሙኤልም እሴይን፥ “ልጆችህ እኒህ ብቻ ናቸው?” አለው። እርሱም፥ “ታናሹ ገና ቀርቶአል፤ እነሆም፥ በጎችን ይጠብቃል” አለ። ሳሙኤልም እሴይን፥ “እርሱ እስኪመጣ ድረስ ለማዕድ አንቀመጥምና ልከህ አስመጣው” አለው። ልኮም አስመጣው፤ እርሱም ቀይ፥ ዐይኑም የተዋበ፥ መልኩም ያማረ ነበረ። እግዚአብሔርም ሳሙኤልን፥ “ይህ መልካም ነውና ተነሥተህ ዳዊትን ቅባው” አለው። ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ መጣ። ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ አርማቴም ሄደ። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከሳኦል ራቀ፤ ክፉም መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ አስጨነቀው። የሳኦልም ብላቴኖች፥ “እነሆ፥ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያስጨንቅሃል፤ አገልጋዮችህ በፊትህ ይናገሩ፤ በበገና የሚዘምር ሰውም ለጌታቸው ይፈልጉለት፤ ክፉ መንፈስም በመጣብህ ጊዜ በገናውን ሲመታ አንተ ደኅና ትሆናለህ፤ እርሱም ያሳርፍሃል” አሉት። ሳኦልም ብላቴኖቹን፥ “መልካም አድርጎ በገና መምታት የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ” አላቸው። ከብላቴኖቹም አንዱ መልሶ፥ “እነሆ፥ መልካም አድርጎ በገና ሲመታ የቤተ ልሔሙን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ፤ ሰውየውም ጠቢብ፥ ተዋጊም ነው፤ በነገርም ብልህ፥ መልኩም ያማረ ነው፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው” አለ። ሳኦልም ወደ እሴይ መልእክተኞችን ልኮ፥ “ከመንጋዎችህ ጋር ያለውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ” አለ። እሴይም እንጀራና የወይን ጠጅ አቁማዳ የተጫነ አህያ፥ አንድም የፍየል ጠቦት ወስዶ በልጁ በዳዊት እጅ ወደ ሳኦል ላከ። ዳዊትም ወደ ሳኦል መጣ፤ በፊቱም ቆመ፤ እጅግም ወደደው፤ ለእርሱም ጋሻ ጃግሬው ሆነ። ሳኦልም ወደ እሴይ፥ “በዐይኔ ሞገስ አግኝቶአልና ዳዊት በፊቴ እባክህ ይቁም፥” ብሎ ላከ። እንዲህም ሆነ፤ ያ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በሆነ ጊዜ ዳዊት በገና ይዞ በእጁ ይመታ ነበር፤ ሳኦልንም ደስ ያሰኘው፥ ያሳርፈውም ነበር፥ ክፉው መንፈስም ከእርሱ ይርቅ ነበር።
1 ሳሙኤል 16:1-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሳሙኤልን፣ “በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? ወደ ቤተ ልሔሙ ሰው ወደ እሴይ ስለምልክህ፣ ዘይት በቀንድ ሞልተህ ሂድ፤ ከልጆቹ አንዱ ንጉሥ ይሆን ዘንድ መርጬዋለሁ” አለው። ሳሙኤል ግን፣ “ሳኦል ከሰማ ስለሚገድለኝ እንዴት መሄድ እችላለሁ?” አለ። እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “አንዲት ጊደር ይዘህ ሂድና፣ ‘ለእግዚአብሔር ልሠዋ መጥቻለሁ’ በል። እሴይን ወደ መሥዋዕቱ ጥራው፤ ከዚያም የምታደርገውን አሳይሃለሁ፤ የምነግርህንም ሰው ትቀባልኛለህ።” ሳሙኤል እግዚአብሔር ያለውን ነገር አደረገ። ቤተ ልሔም እንደ ደረሰም፣ የከተማዪቱ ሽማግሌዎች እየተንቀጠቀጡ ሊገናኙት መጡ፣ እነርሱም “አመጣጥህ ለሰላም ነውን?” ብለው ጠየቁት። ሳሙኤልም፣ “አዎን፤ ለሰላም ነው፤ የመጣሁትም ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ላቀርብ ነው፤ እናንተም ራሳችሁን ቀድሳችሁ ከእኔ ጋራ ወደ መሥዋዕቱ ኑ” ሲል መለሰላቸው። ከዚያም እሴይንና ልጆቹን ቀደሳቸው፤ ወደ መሥዋዕቱም እንዲመጡ ጠራቸው። እዚያ በደረሱ ጊዜም፣ ሳሙኤል ኤልያብን አይቶ፣ “በርግጥ እግዚአብሔር የቀባው ሰው እነሆ፤ በእግዚአብሔር ፊት ቆሟል” ብሎ ዐሰበ። እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፣ “መልኩን ወይም ቁመቱን አትይ፤ እኔ ንቄዋለሁና። እግዚአብሔር የሚያየው፣ ሰው እንደሚያየው አይደለም። ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” አለው። ከዚያም እሴይ አሚናዳብን ጠርቶ በሳሙኤል ፊት እንዲያልፍ አደረገ፤ ሳሙኤል ግን፣ “እግዚአብሔር ይህንም አልመረጠውም” አለው። እሴይም ሣማን አሳለፈ፤ ሳሙኤልም፣ “እርሱንም እግዚአብሔር አልመረጠውም” አለ። እሴይም ሰባቱን ልጆቹን በሳሙኤል ፊት እንዲያልፉ አደረገ፤ ሳሙኤል ግን፣ “እግዚአብሔር እነዚህንም አልመረጣቸውም” አለው። ቀጥሎም እሴይን፣ “ልጆችህ እነዚሁ ብቻ ናቸውን?” ሲል ጠየቀው። እሴይም፣ “የሁሉም ታናሽ ገና አልመጣም፤ ነገር ግን በጎች እየጠበቀ ነው” ብሎ መለሰ። ሳሙኤልም፣ “በል ልከህ አስመጣው፤ እስኪመጣ ድረስ አንቀመጥምና” አለው። ስለዚህ ልኮ አስመጣው፤ እርሱም ደም ግባት ያለው፣ ዐይኑ የሚያምርና መልከ መልካም ነበረ። እግዚአብሔርም፣ “የመረጥሁት ይህ ነውና ተነሥተህ ቀባው” አለው። ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ ፊት ቀባው። ከዚያ ቀን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንፈስ በዳዊት ላይ በኀይል መጣ፤ ሳሙኤልም ወደ አርማቴም ሄደ። የእግዚአብሔር መንፈስ ከሳኦል ስለ ራቀ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ክፉ መንፈስ ያሠቃየው ነበር። የሳኦል አገልጋዮችም እንዲህ አሉት፤ “እነሆ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ክፉ መንፈስ እያሠቃየህ ነው። እንግዲህ በገና መደርደር የሚችል ሰው እንዲፈልጉ፣ ጌታችን በፊቱ የሚቆሙትን አገልጋዮቹን ይዘዝ፤ ከዚያም ከእግዚአብሔር የታዘዘው ክፉ መንፈስ ባንተ ላይ በሚመጣ ጊዜ በገና ይደረድርልሃል፤ ደኅናም ትሆናለህ።” ስለዚህ ሳኦል አገልጋዮቹን፣ “መልካም አድርጎ በገና መደርደር የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ” አላቸው። ከአገልጋዮቹም አንዱ፣ “መልካም አድርጎ በገና መደርደር የሚችለውን የቤተ ልሔሙን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ፣ እርሱም ጀግናና ተዋጊ ነው፤ በአነጋገሩ አስተዋይና የደስ ደስ ያለው ነው፤ እግዚአብሔርም ከርሱ ጋራ ነው” ብሎ መለሰ። ከዚያም ሳኦል፣ “ከበጎች ጋራ ያለውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ” ሲል መልክተኞችን ወደ እሴይ ላከ። እሴይም እንጀራና በወይን ጠጅ የተሞላ አቍማዳ በአህያ አስጭኖ፣ የፍየል ጠቦትም አስይዞ ልጁን ዳዊትን ወደ ሳኦል ላከው። ዳዊት ወደ ሳኦል መጥቶ አገልግሎቱን ጀመረ፤ ሳኦልም እጅግ ወደደው፣ እርሱም የሳኦል ጋሻ ጃግሬ ሆነ። ከዚያም ሳኦል፣ “ዳዊትን ወድጄዋለሁና ከእኔ ዘንድ ሆኖ እንዲያገለግለኝ ፍቀድልኝ” ብሎ ወደ እሴይ ላከ። ክፉው መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሳኦል ላይ በሚመጣበት ጊዜ፣ ዳዊት በገናውን ይዞ ይደረድር ነበር፤ ሳኦልም ይሻለው ነበር፤ ክፉውም መንፈስ ከርሱ ይርቅ ነበር።
1 ሳሙኤል 16:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ሳሙኤልን፦ በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? በቀንድህ ዘይቱን ሞልተህ ሂድ፥ በልጆቹ መካከል ንጉሥ አዘጋጅቻለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተ ልሔም እልክሃለሁ አለው። ሳሙኤልም፦ እንዴት እሄዳለሁ? ሳኦል ቢሰማ ይገድለኛል አለ። እግዚአብሔርም፦ አንዲት ጊደር ይዘህ ሂድና፦ ለእግዚአብሔር እሠዋ ዘንድ መጣሁ በል። እሴይንም መሥዋዕቱ ጥራው፥ የምታደርገውንም አስታውቅሃለሁ፥ የምነግርህንም ቅባልኝ አለው። ሳሙኤልም እግዚአብሔር የተናገረውን አደረገ፥ ወደ ቤተ ልሔምም መጣ። የአገሩም ሽማግሌዎች እየተንቀጠቀጡ ሊገናኙት መጡና፦ የመጣኸው ለደኅንነት ነውን? አሉት። እርሱም፦ ለደኅነት ነው፥ ለእግዚአብሔር እሠዋ ዘንድ መጣሁ፥ ቅዱሳን ሁኑ፥ ከእኔም ጋር ወደ መሥዋዕቱ ኑ አለ። እሴይንና ልጆቹንም ቀደሳቸው፥ ወደ መሥዋዕቱም ጠራቸው። እንዲህም ሆነ፥ በመጡ ጊዜ ወደ ኤልያብ ተመልክቶ፦ በእውነት እግዚአብሔር የሚቀባው በፊቱ ነው አለ። እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፦ ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፥ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፥ ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል አለው። እሴይም አሚናዳብን ጠርቶ በሳሙኤል ፊት አሳለፈው፥ እርሱም፦ ይህን ደግሞ እግዚአብሔር አልመረጠውም አለ። እሴይም ሣማን አሳለፈው፥ እርሱም፦ ይህን ደግሞ እግዚአብሔር አልመረጠውም አለ። እሴይም ከልጆቹ ሰባቱን በሳሙኤል ፊት አሳለፋቸው። ሳሙኤልም እሴይን፦ እግዚአብሔር እነዚህን አልመረጠም አለው። ሳሙኤልም እሴይን፦ የቀረ ሌላ ልጅ አለህን? አለው። እርሱም፦ ታናሹ ገና ቀርቶአል፥ እነሆም፥ በጎችን ይጠብቃል አለ። ሳሙኤልም እሴይን፦ እርሱ እስኪመጣ ድረስ አንረፍቅምና ልከህ አስመጣው አለው። ልኮም አስመጣው፥ እርሱም ቀይ፥ ዓይኑም የተዋበ፥ መልኩም ያማረ ነበረ። እግዚአብሔርም፦ ይህ ነውና ተነሥተህ ቅባው አለ። ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ በኃይል መጣ። ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ አርማቴም ሄደ። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከሳኦል ራቀ፥ ክፉም መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ አሠቃየው። የሳኦልም ባሪያዎች፦ እነሆ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያሠቃይሃል፥ በገና መልካም አድርጎ የሚመታ ሰው ይሹ ዘንድ ጌታችን በፊቱ የሚቆሙትን ባሪያዎቹን ይዘዝ፥ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ክፉ መንፈስ በሆነብህ ጊዜ በእጅ ሲመታ አንተ ደኅና ትሆናለህ አሉት። ሳኦልም ባሪያዎቹን፦ መልካም አድርጎ በገና መምታት የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ አላቸው። ከብላቴኖቹም አንዱ መልሶ፦ እነሆ፥ መልካም አድርጎ በገና የሚመታ የቤተ ልሔማዊውን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ፥ እርሱም ጽኑዕ ኃይል ነው፥ በነገርም ብልህ፥ መልኩም ያማረ ነው፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው አለ። ሳኦልም ወደ እሴይ መልክተኞች ልኮ፦ ከበጎች ጋር ያለውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ አለ። እሴይም እንጀራና የወይን ጠጅ አቁማዳ የተጫነ አህያ የፍየልም ጠቦት ወስዶ በልጁ በዳዊት እጅ ወደ ሳኦል ላከ። ዳዊትም ወደ ሳኦል መጣ፥ በፊቱም ቆመ፥ እጅግም ወደደው፥ ለእርሱም ጋሻ ጃግሬው ሆነ። ሳኦልም ወደ እሴይ፦ በዓይኔ ሞገስ አግኝቶአልና ዳዊት በፊቴ፥ እባክህ፥ ይቁም ብሎ ላከ። እንዲህም ሆነ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በሆነ ጊዜ ዳዊት በገና ይዞ በእጁ ይመታ ነበር፥ ሳኦልም ደስ ያሰኘው ያሳርፈውም ነበር፥ ክፉ መንፈስም ከእርሱ ይርቅ ነበር።
1 ሳሙኤል 16:1-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “ከንጉሥነት ስለ ሻርኩት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ድረስ ነው? እኔ እርሱ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ ይኖር ዘንድ አልፈልገውም። ይልቅስ የወይራ ዘይት በቀንድ ሞልተህ በመያዝ በቤተልሔም ወደሚኖረው እሴይ ተብሎ ወደሚጠራው ሰው ዘንድ ሂድ፤ እኔ ከእርሱ ልጆች መካከል አንዱን ንጉሥ እንዲሆን መርጬአለሁ።” ሳሙኤልም “ይህን ለማድረግ እንዴት ይቻለኛል? ሳኦል ይህን ቢሰማ ይገድለኛል!” ሲል ጠየቀ። እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ ‘ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ለማቅረብ መጥቻለሁ’ ብለህ ጊደር ይዘህ ሂድ፤ እሴይንም ወደ መሥዋዕቱ እንዲመጣ ጥራው፤ እኔም የምታደርገውን ነገር እነግርሃለሁ፤ እኔ የምነግርህንም ሰው ቀብተህ ታነግሣለህ።” ሳሙኤልም እግዚአብሔር ያዘዘውን ለማድረግ ወደ ቤተልሔም ሄደ፤ እዚያም እንደ ደረሰ የከተማይቱ መሪዎች በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ ወደ ሳሙኤል ቀርበው “አመጣጥህ ለሰላም ነውን?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም “አዎ! ለሰላም ነው፤ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀርብ ዘንድ መጥቻለሁ፤ ራሳችሁን በማንጻት ወደ እኔ ኑ” ሲል መለሰላቸው። እሴይና ልጆቹም ራሳቸውን እንዲያነጹ በመንገር ወደ መሥዋዕቱ እንዲመጡ ጠራቸው። እዚያም በደረሱ ጊዜ ሳሙኤል ኤሊአብ ተብሎ የሚጠራውን የእሴይን ልጅ አይቶ “በእግዚአብሔር ፊት የቆመው ይህ ሰው በእርግጥ ለንጉሥነት የተመረጠ ነው” ሲል አሰበ። እግዚአብሔር ግን “የኤሊአብን ቁመት መርዘምና መልከ ቀናነቱን አትይ፤ እኔ እርሱን አልፈለግሁትም፤ እኔ የምፈርደው ሰዎች እንደሚፈርዱት አይደለም፤ ሰው የውጪ መልክን ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” አለው። ከዚህ በኋላ እሴይ አቢናዳብ ተብሎ የሚጠራውን ልጁን ወደ ሳሙኤል አመጣለት፤ ሳሙኤል ግን “እግዚአብሔር ይህኛውንም አልመረጠውም” አለ። ቀጥሎም እሴይ ሻማ ተብሎ የሚጠራውን ልጁን አመጣ፤ ሳሙኤል ግን “እግዚአብሔር ይህኛውንም አልመረጠም” አለ። በዚህም ዐይነት እሴይ ሰባቱንም ልጆቹን አቅርቦ በሳሙኤል ፊት አሰለፋቸው፤ ሳሙኤልም እሴይን “እነሆ፥ ከእነዚህ መካከል እግዚአብሔር አንዱንም አልመረጠም” አለው። “ታዲያ ሌሎች ልጆች የሉህምን?” ሲል ጠየቀው። እሴይም “የሁሉ ታናሽ የሆነ አንድ ልጅ አለ፤ እርሱ ግን ወደ በግ እረኝነት ሄዶአል” ሲል መለሰለት። ሳሙኤልም “እርሱን አስጠርተህ አምጣው፤ እርሱ ሳይመጣ መሥዋዕት አናቀርብም” አለው። ስለዚህም እሴይ ልኮ አስጠራው፤ እርሱ ቀይ፥ መልከ መልካምና ዐይኖቹ የሚያበሩ ጤናማ ወጣት ነበር፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን “የመረጥኩት ሰው ይህ ነውና ተነሥተህ እርሱን ቀባው!” አለው። ሳሙኤልም በወይራ ዘይት የተሞላውን ቀንድ ወስዶ ዳዊትን በወንድሞቹ ፊት ቀባው፤ ወዲያውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ በዳዊት አደረበት፤ ከዚያም ቀን ጀምሮ ከእርሱ አልተለየም፤ ከዚህም በኋላ ሳሙኤል ወደ ራማ ተመለሰ። የእግዚአብሔር መንፈስ ከሳኦል ስለ ተለየ ከእግዚአብሔር የተላከ ክፉ መንፈስ ያሠቃየው ነበር፤ አገልጋዮቹም እንዲህ አሉት፤ “እነሆ ከእግዚአብሔር የተላከ ክፉ መንፈስ ያሠቃይሃል፤ ስለዚህ ንጉሥ ሆይ! በገና መደርደር የሚያውቅ ሰው ፈልገን እንድናመጣልህ እዘዘን፤ ከዚያም በኋላ ክፉ መንፈስ በሚመጣብህ ጊዜ ያ ሰው በገና ይደረድርልሃል፤ አንተም እንደገና ጤናማ ትሆናለህ።” ሳኦልም “በገና በመደርደር የታወቀ ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ” አላቸው። ከአገልጋዮቹም አንዱ “የቤተልሔም ከተማ ነዋሪ የሆነው እሴይ በገና መደርደር የሚችል ልጅ እንዳለው አይቼአለሁ ይህም ብቻ ሳይሆን ጀግና፥ መልከ ቀና፥ ብርቱ ወታደርና ንግግር ዐዋቂ ነው፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው” አለው። ስለዚህም ሳኦል ወደ እሴይ መልእክተኞች ልኮ “የበጎች እረኛ የሆነውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ” አለው። እሴይም ዳዊትን አንድ ትንሽ የፍየል ጠቦት አስይዞ፥ እንጀራና የወይን ጠጅ የተሞላበት አቁማዳ ከተጫነ አንድ አህያ ጋር ወደ ሳኦል ላከው። ዳዊትም ወደ ሳኦል መጥቶ ሥራውን ጀመረ፤ ሳኦልም በጣም ስለ ወደደው የእርሱ መሣሪያ ያዥ ጋሻጃግሬ አደረገው። ከዚያም በኋላ ሳኦል ወደ እሴይ መልእክት ልኮ “ዳዊትን ወድጄዋለሁ፤ ስለዚህ እዚህ በመቈየት ያገልግለኝ” አለው። ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ከእግዚአብሔር የተላከ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በሚመጣበት ጊዜ ሁሉ ዳዊት በገናውን አንሥቶ ይደረድራል፤ ክፉውም መንፈስ ለቆት ስለሚሄድ ሳኦል እየተሻለው እንደገና ጤናማ ይሆናል።
1 ሳሙኤል 16:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታ ሳሙኤልን፥ “በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? ወደ ቤተልሔሙ ሰው ወደ እሴይ ስለምልክህ፥ ዘይት በቀንድ ሞልተህ ሂድ፤ ከልጆቹ አንዱ ንጉሥ ይሆን ዘንድ መርጬዋለሁ” አለው። ሳሙኤል ግን፥ “ሳኦል ከሰማ ስለሚገድለኝ እንዴት መሄድ እችላለሁ?” አለ። ጌታም እንዲህ አለው፤ “አንዲት ጊደር ይዘህ ሂድና፥ ‘ለጌታ ልሠዋ መጥቻለሁ’ በል። እሴይንም ወደ መሥዋዕቱ ጥራው፤ ከዚያም የምታደርገውን አሳይሃለሁ፤ የምነግርህንም ሰው ትቀባልኛለህ።” ሳሙኤል ጌታ ያለውን ነገር አደረገ። ቤተልሔም እንደደረሰም፥ የከተማዪቱ ሽማግሌዎች እየተንቀጠቀጡ ሊገናኙት መጡ፥ እነርሱም “አመጣጥህ ለሰላም ነውን?” ብለው ጠየቁት። ሳሙኤልም፥ “አዎን፤ ለሰላም ነው፤ የመጣሁትም ለጌታ መሥዋዕት ላቀርብ ነው፤ እናንተም ራሳችሁን ቀድሳችሁ ከእኔ ጋር ወደ መሥዋዕቱ ኑ” ሲል መለሰላቸው። ከዚያም እሴይንና ልጆቹን ቀደሳቸው፤ ወደ መሥዋዕቱም እንዲመጡ ጠራቸው። እዚያ በደረሱ ጊዜም፥ ሳሙኤል ኤልያብን አይቶ፥ “በእርግጥ ጌታ የቀባው ሰው እነሆ፤ በጌታ ፊት ቆሞአል” ብሎ አሰበ። ጌታ ግን ሳሙኤልን፥ “መልኩን ወይም ቁመቱን አትይ፤ እኔ ንቄዋለሁና። ጌታ የሚያየው፥ ሰው እንደሚያየው አይደለም። ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ ጌታ ግን ልብን ያያል” አለው። ከዚያም እሴይ አሚናዳብን ጠርቶ በሳሙኤል ፊት እንዲያልፍ አደረገ፤ ሳሙኤል ግን፥ “ጌታ ይህንንም አልመረጠውም” አለው። እሴይም ሻማን አሳለፈ፤ ሳሙኤልም፥ “እርሱንም ጌታ አልመረጠውም” አለ። እሴይም ሰባቱን ልጆቹን በሳሙኤል ፊት እንዲያልፉ አደረገ፤ ሳሙኤል ግን፥ “ጌታ እነዚህንም አልመረጣቸውም” አለው። ቀጥሎም እሴይን፥ “ልጆችህ እነዚሁ ብቻ ናቸውን?” ሲል ጠየቀው። እሴይም፥ “የሁሉም ታናሽ ገና አልመጣም፤ ነገር ግን በጎች እየጠበቀ ነው” ብሎ መለሰ። ሳሙኤልም እሴይን፥ “በል ልከህ አስመጣው፤ እስኪመጣ ድረስ አንቀመጥም” አለው። ስለዚህ ልኮ አስመጣው፤ እርሱም ደም ግባት ያለው፥ ዐይኑ የሚያምርና መልከ መልካም ነበረ። ጌታም፥ “የመረጥሁት ይህ ነውና ተነሥተህ ቀባው” አለው። ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ ፊት ቀባው። ከዚያ ቀን ጀምሮ የጌታ መንፈስ በዳዊት ላይ በኃይል መጣ፤ ሳሙኤልም ወደ ራማ ተመለሰ። የጌታ መንፈስ ከሳኦል ስለ ራቀ፤ ከጌታ ዘንድ የታዘዘ ክፉ መንፈስ ያሠቃየው ነበር። የሳኦል አገልጋዮችም እንዲህ አሉት፤ “እነሆ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ክፉ መንፈስ እያሠቃየህ ነው። እንግዲህ በገና መደርደር የሚችል ሰው እንዲፈልጉ፥ ጌታችን በፊቱ የሚቆሙትን አገልጋዮቹን ይዘዝ፤ ከዚያም ከእግዚአብሔር የታዘዘው ክፉ መንፈስ ባንተ ላይ በሚመጣ ጊዜ በገና ይደረድርልሃል፤ ደኅናም ትሆናለህ።” ስለዚህ ሳኦል አገልጋዮቹን፥ “መልካም አድርጎ በገና መደርደር የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ” አላቸው። ከአገልጋዮቹም አንዱ፥ “መልካም አድርጎ በገና መደርደር የሚችለውን የቤተልሔሙን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ፥ እርሱም ጀግናና ተዋጊ ነው፤ በአነጋገሩ አስተዋይና የደስ ደስ ያለው ነው፤ ጌታም ከእርሱ ጋር ነው” ብሎ መለሰ። ከዚያም ሳኦል፥ “ከበጎች ጋር ያለውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ” ሲል መልክተኞችን ወደ እሴይ ላከ። እሴይም እንጀራና በወይን ጠጅ የተሞላ አቁማዳ በአህያ አስጭኖ፥ የፍየል ጠቦትም አስይዞ ልጁን ዳዊትን ወደ ሳኦል ላከው። ዳዊት ወደ ሳኦል መጥቶ አገልግሎቱን ጀመረ፤ ሳኦልም እጅግ ወደደው፥ እርሱም የሳኦል ጋሻ ጃግሬ ሆነ። ከዚያም ሳኦል፥ “ዳዊትን ወድጄዋለሁና ከእኔ ዘንድ ሆኖ እንዲያገለግለኝ ፍቀድልኝ” ብሎ ወደ እሴይ ላከ። ክፉው መንፈስ ከእግዚአብሔር ተልኮ በሳኦል ላይ በሚመጣበት ጊዜ፥ ዳዊት በገናውን ይዞ ይደረድር ነበር፤ ሳኦልም ይሻለው ነበር፤ ክፉውም መንፈስ ከእርሱ ይርቅ ነበር።