1 ሳሙኤል 15:17-26
1 ሳሙኤል 15:17-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሳሙኤልም ሳኦልን አለው፥ “በፊቱ ምንም ታናሽ ብትሆን ለእስራኤል ነገዶች አለቃ አልሆንህምን? እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባህ። እግዚአብሔርም፦ ሄደህ ኀጢኣተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው፤ እስኪጠፉም ድረስ ውጋቸው ብሎ በመንገድ ላከህ። ለምርኮ ሳስተህ ለምን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህም? ለምንስ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረግህ?” ሳኦልም ሳሙኤልን፥ “የእግዚአብሔርን ቃል ስለሰማሁ፥ እግዚአብሔር በላከኝ መንገድ ሄጃለሁ፤ የአማሌቅን ንጉሥ አጋግንም አምጥቻለሁ፤ አማሌቃውያንንም ፈጽሜ አጥፍቻለሁ። ሕዝቡ ግን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር በጌልጌላ ይሠዉ ዘንድ ከእርሙ የተመረጡትን በጎችና በሬዎች ከምርኮው ወሰዱ” አለው። ሳሙኤልም ሳኦልን፥ “በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል። ኀጢኣት እንደ ምዋርተኝነት ናትና አምልኮተ ጣዖትም ደዌንና ኀዘንን ያመጣል። የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና እግዚአብሔር ንጉሥ እንዳትሆን ናቀህ” አለው። ሳኦልም ሳሙኤልን፥ “ሕዝቡን ስለ ፈራሁ፥ ቃላቸውንም ስለ ሰማሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና የአንተን ቃል በመተላለፍ በድያለሁ። አሁንም እባክህ ኀጢኣቴን ይቅር በለኝ፤ ለእግዚአብሔርም እሰግድ ዘንድ ከእኔ ጋር ተመለስ” አለው። ሳሙኤልም ሳኦልን፥ “የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና፥ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃልና ከአንተ ጋር አልመለስም” አለው።
1 ሳሙኤል 15:17-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሳሙኤልም እንዲህ አለው፤ “በዐይንህ ፊት ታናሽ የነበርህ ብትሆንም፣ የእስራኤል ነገዶች መሪ ሆነህ የለምን? እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ቀብቶ አንግሦሃል። እግዚአብሔርም፣ ‘ሄደህ እነዚያን ኀጢአተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው፤ ጨርሰህ እስክታጠፋቸውም ድረስ ውጋቸው’ ብሎ ልኮህ ነበር። ታዲያ እግዚአብሔርን ለምን አልታዘዝህም? ለምርኮውስ ተስገብግበህ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ለምን አደረግህ?” ሳኦልም ሳሙኤልን መልሶ እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔርን ታዝዣለሁ፤ እግዚአብሔር በላከኝ መሠረት ሄጃለሁ፤ አማሌቃውያንን በሙሉ አጥፍቼ ንጉሣቸውን አጋግን አምጥቻለሁ። ሰራዊቱ ግን ከምርኮው ከተለዩት መካከል፣ ምርጥ ምርጡን በግና በሬ፣ በጌልገላ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ይሠዉ ዘንድ ወስደዋል።” ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ ደስ የሚለውን ያህል፣ እግዚአብሔር፣ በሚቃጠል ቍርባንና መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ! መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ ማዳመጥም ከአውራ በግ ሥብ ይበልጣል። ዐመፅ እንደ ጥንቈላ ያለ ኀጢአት፣ እልኸኝነትም እንደ ጣዖት አምልኮ ያለ ክፉ ነገር ነው። አንተ የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ናቅህ፣ እርሱም ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል።” ከዚያም ሳኦል ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና የአንተን መመሪያ ጥሻለሁ፤ ሕዝቡን ፈርቼ ስለ ነበር፣ የጠየቁኝን ታዝዣለሁ። አሁንም ኀጢአቴን ይቅር እንድትለኝ፣ ለእግዚአብሔርም እሰግድ ዘንድ ዐብረኸኝ እንድትመለስ እለምንሃለሁ።” ሳሙኤል ግን፣ “ከአንተ ጋራ አልመለስም፤ አንተ የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃል፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል” አለው።
1 ሳሙኤል 15:17-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሳሙኤልም አለ፦ በዓይንህ ምንም ታናሽ ብትሆን ለእስራኤል ነገዶች አለቃ አልሆንህምን? እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባህ። እግዚአብሔርም፦ ሄደህ ኃጢአተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው፥ እስኪጠፉም ድረስ ውጋቸው ብሎ በመንገድ ላከህ። ለምርኮ ሳስተህ ለምን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህም? ለምንስ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረግህ? ሳኦልም ሳሙኤልን፦ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቻለሁ፥ እግዚአብሔርም በላከኝ መንገድ ሄጃለሁ፥ የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን አምጥቻለሁ፥ አማሌቃውያንንም ፈጽሜ አጥፍቻለሁ። ሕዝቡ ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በጌልገላ ይሠዉ ዘንድ ከእርሙ የተመረጡትን በጎችንና በሬዎችን ከምርኮው ወሰዱ አለው። ሳሙኤልም፦ በውኑ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ደስ እንደሚለው እግዚአብሔር በሚቃጠልና በሚታረድ መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ፥ መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል። ዓመፀኝነት እንደ ምዋርተኛ ኃጢአት፥ እልከኝነትም ጣዖትንና ተራፊምን እንደ ማምለክ ነው፥ የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና እግዚአብሔር ንጉሥ እንዳትሆን ናቀህ አለ። ሳኦልም ሳሙኤልን፦ ሕዝቡን ስለ ፈራሁ፥ ቃላቸውንም ስለ ሰማሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና የአንተን ቃል በመተላለፍ በድያለሁ። አሁንም፥ እባክህ፥ ኃጢአቴን ይቅር በለኝ፥ ለእግዚአብሔርም እሰግድ ዘንድ ከእኔ ጋር ተመለስ አለው። ሳሙኤልም ሳኦልን፦ የእግዚአብሔርን ቃል ንቀሃልና፥ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃልና ከአንተ ጋር አልመለስም አለው።
1 ሳሙኤል 15:17-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሳሙኤልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አንተ ስለ ራስህ የነበረህ ግምት አነስተኛ ቢሆንም የእስራኤል ነገዶች መሪ አልሆንክምን? እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ቀብቶ አንግሦሃል፤ ኃጢአተኞች የሆኑትን እነዚያን አማሌቃውያንን እንድትደመስስ ልኮሃል፤ እስኪጠፉም ድረስ እነርሱን ግደል ብሎ ነግሮሃል። ታዲያ ስለምን ትእዛዙን አልፈጸምክም? ለምርኮስ በመሳሳትና በመስገብገብ እግዚአብሔርን ደስ የማያሰኝ ነገር ስለምን አደረግህ?” ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ፈጽሜአለሁ፤ ባዘዘኝም መሠረት ዘምቻለሁ፤ ንጉሥ አጋግን ብቻ ማርኬ ሳመጣ ሌሎችን ዐማሌቃውያን ሁሉ ገድያለሁ፤ ነገር ግን ወታደሮቼ የማረኩአቸውን ምርጥ ምርጥ የሆኑ በጎችንና የቀንድ ከብቶችን አልገደሉአቸውም፤ ይህን በማድረግ ፈንታ በጌልገላ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርገው ለማቅረብ አምጥተዋቸዋል።” ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር የሚወደው የቱን ይመስልሃል? መታዘዝን ወይስ ቊርባንና መሥዋዕት ማቅረብን? ለእርሱ መታዘዝ ምርጥ የበግ መሥዋዕት ከማቅረብ ይበልጣል፤ በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ እንደ ሟርተኛነት፥ የትዕቢት እልኸኛነትም ጣዖትን በማምለክ ኃጢአት እንደ መሥራት ይቈጠራል፤ አንተ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ተውክ በንጉሥነትህ እንዳትቀጥል እርሱም አንተን ትቶሃል።” ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አዎ፤ እኔ ኃጢአት ሠርቼአለሁ፤ የእግዚአብሔርን ትእዛዝና አንተ የሰጠኸኝን መመሪያ አልጠበቅሁም፤ ወታደሮቼን በመፍራት እነርሱ የፈለጉትን ሁሉ አደረግሁ፤ አሁን ግን እለምንሃለሁ በደሌን ይቅር በለኝ፤ በዚያ ለእግዚአብሔር እሰግድ ዘንድ ከእኔም ጋር ወደ ጌልጌላ ተመለሰ።” ሳሙኤልም “እኔ ከአንተ ጋር አልሄድም፤ አንተ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸም ትተሃል፤ አንተም የእስራኤል ንጉሥ ሆነህ እንዳትቀጥል እርሱ ትቶሃል” ሲል መለሰለት።
1 ሳሙኤል 15:17-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሳሙኤልም እንዲህ አለው፤ “ስለ ራስህ የነበረህ ግምት ታናሽ የነበር ቢሆንም፥ የእስራኤል ነገዶች መሪ አልሆንክምን? ጌታም በእስራኤል ላይ ቀብቶ አንግሦሃል። ጌታም፥ ‘ሄደህ ኃጢአተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው፥ እስኪጠፉም ድረስ ውጋቸው’ ብሎ ልኮህ ነበር። ታዲያ የጌታን ቃል ለምን አልታዘዝህም? ለምርኮውስ ተስገብግበህ በጌታ ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ለምን አደረግህ?” ሳኦልም መልሶ እንዲህ አለ፤ “የጌታን ቃል ታዝዣለሁ፤ ጌታ በላከኝ መሠረት ሄጃለሁ፤ አማሌቃውያንን በሙሉ አጥፍቼ ንጉሣቸውን አጋግን አምጥቻለሁ። ሕዝቡ ግን በጌልገላ ለአምላክህ ለጌታ ለመሠዋት ከምርኮው ከተለዩት መካከል፥ ምርጥ ምርጡን በግና በሬ ወስደዋል።” ሳሙኤልም፦ “ጌታ ለቃሉ በመታዘዝ ደስ የሚለውን ያህል፥ ጌታ፥ በሚቃጠል ቁርባንና መሥዋዕት ደስ ይለዋልን? እነሆ! መታዘዝ ከመሥዋዕት፥ ማዳመጥም ከአውራ በግ ሥብ ይበልጣል። ዐመፅ እንደ ሟርተኛነት ያለ ኃጢአት፥ እልኸኝነትም እንደ ጣዖት አምልኮ ያለ ክፉ ነገር ነው፤ አንተ የጌታን ቃል ንቀሃልና እርሱም ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል።” ሳኦልም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ኃጢአት ሠርቼአለሁ፤ የጌታን ትእዛዝና የአንተን ቃል አልጠበቅሁም፤ ሕዝቡን በመፍራት የፈለጉትን ሁሉ አደረግሁ፤ አሁንም፥ ኀጢአቴን ይቅር እንድትለኝ፥ ለእግዚአብሔርም እሰግድ ዘንድ አብረኸኝ እንድትመለስ እለምንሃለሁ።” ሳሙኤል ግን ሳኦልን፥ “ከአንተ ጋር አልመለስም፤ አንተ የጌታን ቃል ንቀሃል፤ ጌታም በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዳትሆን ንቆሃል” አለው።