1 ሳሙኤል 14:1-6
1 ሳሙኤል 14:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በነጋም ጊዜ፥ የሳኦል ልጅ ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን፥ “ና፤ በዚያ በኩል ወዳለው ወደ ፍልስጥኤማውያን ሰፈር እንለፍ” አለው፤ ለአባቱም አልነገረውም። ሳኦልም በመጌዶን ባለው በሮማኑ ዛፍ በታች በኮረብታው ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ስድስት መቶ የሚያህል ሰው ነበረ። የዔሊ ልጅ፥ የፊንሐስ ልጅ፥ የዮካብድ ወንድም፥ የአኪጦብ ልጅ በሴሎ ለእግዚአብሔር ካህን የሆነ፥ ኤፉድም የለበሰ አኪያ አብሮ ነበር፤ ሕዝቡም ዮናታን እንደ ሄደ አላወቁም ነበር። ዮናታንም ወደ ፍልስጥኤማውያን ሰፈር ሊሻገርበት በወደደው መተላለፊያ መካከል በወዲህ አንድ ሾጣጣ፥ በወዲህም አንድ ሾጣጣ ድንጋዮች ነበሩ፤ የአንዱም ስም ባዚስ፥ የሁለተኛውም ስም ሴና ነበረ። አንደኛዋ መንገድ በማኪማስ አንጻር በመስዕ በኩል የምትመጣ ናት፤ ሁለተኛዋም መንገድ በገባዖን አንጻር በአዜብ በኩል የምትመጣ ነበረች። ዮናታንም ጋሻ ጃግሬውን፥ “ና፥ ወደ እነዚህ ቈላፋን ሰፈር እንለፍ፤ በብዙ ወይም በጥቂት ማዳን እግዚአብሔርን አያስቸግረውምና ምናልባት እግዚአብሔር ይረዳን ይሆናል” አለው።
1 ሳሙኤል 14:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አንድ ቀን የሳኦል ልጅ ዮናታን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን፣ “ና በሌላ በኩል ወዳለው የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር እንሻገር” አለው። ይህን ግን ለአባቱ አልነገረውም ነበር። ሳኦልም በጊብዓ ዳርቻ ሚግሮን በተባለ ስፍራ ከአንድ የሮማን ዛፍ ሥር ሰፍሮ ነበር፤ ስድስት መቶ ያህል ሰዎችም ዐብረውት ነበሩ፤ ኤፉድ ይለብስ የነበረውም አኪያ በመካከላቸው ነበር። እርሱም በሴሎ የእግዚአብሔር ካህን የነበረው የዔሊ ልጅ፣ የፊንሐስ ልጅ የኢካቦድ ወንድም የአኪጦብ ልጅ ነበር። ዮናታን አለመኖሩን ግን ያወቀ ሰው አልነበረም። ዮናታን ወደ ፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር ለመሻገር በፈለገበት መተላለፊያ ግራና ቀኝ አንዱ ቦጼጽ ሌላው ሴኔ የተባሉ ሁለት ሾጣጣ ዐለቶች ነበሩ። አንዱ ዐለት በስተሰሜን በኩል በማክማስ አንጻር፣ ሌላው ደግሞ በስተ ደቡብ በኩል በጌባዕ አንጻር ይገኝ ነበር። ዮናታን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን፣ “ና፤ ወደነዚያ ሸለፈታሞች ጦር ሰፈር እንሻገር፤ ምናልባትም እግዚአብሔር ይዋጋልን ይሆናል፤ በብዙም ሆነ በጥቂት ለማዳን እግዚአብሔርን የሚያግደው የለምና” አለው።
1 ሳሙኤል 14:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፥ የሳኦል ልጅ ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን፦ ና፥ በዚያ በኩል ወዳለው ወደ ፍልስጥኤማውያን ጭፍራ እንለፍ አለው፥ ለአባቱም አልነገረውም። ሳኦልም በመጌዶን ባለው በሮማኑ ዛፍ በታች በጊብዓ ዳርቻ ተቀምጦ ነበር፥ ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ስድስት መቶ የሚያህል ሰው ነበረ። የኢካቦድ ወንድም የአኪጦብ ልጅ የፊንሐስ ልጅ የዔሊ ልጅ በሴሎ ለእግዚአብሔር ካህን የሆነ ኤፉድም የለበሰ አኪያ አብሮ ነበር፥ ሕዝቡ ዮናታን እንደ ሄደ አላወቁም። ዮናታንም ወደ ፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ሊሻገርበት በወደደው መተላለፊያ መካከል በወዲህ አንድ ሾጣጣ በወዲህ አንድ ሾጣጣ ድንጋዮች ነበሩ፥ የአንዱም ስም ቦጼጽ የሁለተኛውም ስም ሴኔ ነበረ። አንዱም ሾጣጣ በማክማስ አንጻር በሰሜን በኩል፥ ሁለተኛውም በጊብዓ አንጻር በደቡብ በኩል የቆሙ ነበሩ። ዮናታንም ጋሻ ጃግሬውን፦ ና፥ ወደ እነዚህ ቆላፋን ጭፍራ እንለፍ፥ በብዙ ወይም በጥቂቱ ማዳን እግዚአብሔርን አያስቸግረውምና ምናልባት እግዚአብሔር ይሠራልን ይሆናል አለው።
1 ሳሙኤል 14:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አንድ ቀን የሳኦል ልጅ ዮናታን የጦር መሣሪያ የሚሸከምለትን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን “ወደ ፍልስጥኤማውያን የጦር ሰፈር እንሻገር” አለው። ነገር ግን ዮናታን ይህን ጉዳይ ለአባቱ እንኳ አልነገረውም፤ በዚህ ጊዜ ሳኦል ከጊብዓ በጣም ሳይርቅ በሚግሮን በአንድ የሮማን ዛፍ ሥር ሰፍሮ ነበር፤ ከእርሱም ጋር ስድስት መቶ ያኽል ጭፍሮች ነበሩ፤ በሴሎ የእግዚአብሔር ካህን የነበረው የዔሊ ልጅ ካህኑ ፊንሐስ የወለደው የኢካቦድ ወንድም የአሒጡብ ልጅ አኪያ ኤፉድ ለብሶ ከእርሱ ጋር አብሮ ነበር። እነርሱም ዮናታን ወዴት እንደ ሄደ አላወቁም ነበር። ዮናታን ወደ ፍልስጥኤማውያን ሰፈር ለመድረስ በሚክማስ መተላለፊያ መውጣት ነበረበት፤ በመተላለፊያውም ከግራና ከቀኝ ሁለት ሾጣጣ አለቶች ሲኖሩ የአንደኛው አለት ስም ቦጼጽ፥ የሁለተኛውም ስም ሴኔ ተብሎ ይጠራል፤ ከአለቶቹም አንዱ ከመተላለፊያው በስተ ሰሜን በኩል በሚክማስ ፊት ለፊት የሚገኘው ሲሆን፥ ሁለተኛውም በስተደቡብ በኩል በጌባዕ ፊት ለፊት ይገኝ ነበር። ዮናታን ጋሻ ጃግሬ የሆነውን ወጣት “ና ወደ እነዚያ ወደ አልተገረዙት ወገኖች የጦር ሰፈር እንሻገር እግዚአብሔር ይረዳን ይሆናል፤ በብዙም ሆነ በጥቂት እግዚአብሔር ማዳን አይሳነውም” አለው።
1 ሳሙኤል 14:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አንድ ቀን የሳኦል ልጅ ዮናታን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን፥ “ና በሌላ በኩል ወዳለው የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር እንሻገር” አለው። ይህን ግን ለአባቱ አልነገረውም ነበር። ሳኦልም በጊብዓ ዳርቻ በሚግሮን ከአንድ የሮማን ዛፍ ሥር ሰፍሮ ነበር፤ ስድስት መቶ ያህል ሰዎችም አብረውት ነበሩ፤ ኤፉድ ይለብስ የነበረውም አኪያ በመካከላቸው ነበር። እርሱም በሴሎ የጌታ ካህን የነበረው የዔሊ ልጅ፥ የፊንሐስ ልጅ የኢካቦድ ወንድም የአኪጦብ ልጅ ነበር። ሕዝቡም ዮናታን አለመኖሩን አላወቁም ነበር። ዮናታን ወደ ፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር ለመሻገር በፈለገበት መተላለፊያ ግራና ቀኝ ሁለት ሾጣጣ ድንጋዮች ነበሩ፤ የአንዱ ስም ቦጼጽ ሲሆን፥ ሌላው ሴኔ ተብሎ ይጠራል። ከድንጋዮቹም አንዱ ከመተላለፊያው በስተ ሰሜን በኩል በሚክማስ ፊት ለፊት የሚገኘው ሲሆን፥ ሁለተኛውም በስተ ደቡብ በኩል በጌባዕ ፊት ለፊት ይገኝ ነበር። ዮናታን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን፥ “ና፤ ወደነዚያ ያልተገረዙ ሰዎች ጦር ሰፈር እንሻገር፤ ምናልባትም ጌታ ይዋጋልን ይሆናል፤ በብዙም ሆነ በጥቂት ለማዳን ጌታን የሚያግደው የለምና” አለው።