1 ሳሙኤል 12:1-5
1 ሳሙኤል 12:1-5 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሳሙኤልም ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ አለ፥ “የነገራችሁኝን ሁሉ ሰምቼ ንጉሥ አንግሼላችኋለሁ። አሁንም እነሆ፥ ንጉሡ በፊታችሁ ይሄዳል፤ እኔም አርጅቻለሁ፤ እንግዲህም አርፋለሁ፤ እነሆም፥ ልጆቼ ከእናንተ ጋር ናቸው፤ እኔም ከሕፃንነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በፊታችሁ ሄድሁ። እነሆኝ፥ በእግዚአብሔርና እርሱ በቀባው ፊት መስክሩብኝ፤ የማንን በሬ ወሰድሁ? የማንንስ አህያ ወሰድሁ? ማንንስ ሸነገልሁ? በማንስ ላይ ግፍ አደረግሁ? ነጠላ ጫማ እንኳን ቢሆን ከማን እጅ መማለጃ ተቀበልሁ? መስክሩብኝ፤ እኔ እመልስላችኋለሁ።” እነርሱም ሳሙኤልን፥ “ግፍም አላደረግህብንም፤ የቀማኸን የለም፤ አላሠቃየኸንም፤ ከእኛም ከማንም እጅ ምንም አልወሰድህም” አሉት። ሳሙኤልም፥ “በእጄ ምንም እንዳላገኛችሁ ዛሬ በዚህች ቀን እግዚአብሔር ምስክር ነው፤ እርሱ የቀባውም ምስክር ነው” አላቸው፤ እነርሱም፥ “አዎ ምስክር ነው” አሉ።
1 ሳሙኤል 12:1-5 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሳሙኤል ለመላው እስራኤል እንዲህ አለ፤ “እነሆ፤ ያላችሁኝን ሁሉ ሰምቼ ንጉሥ አንግሼላችኋለሁ። ንጉሥ ሆኖ የሚመራችሁንም ሰው እነሆ፤ አግኝታችኋል። እኔም ዕድሜዬ ገፍቷል፤ ጠጕሬም ሸብቷል፤ ልጆቼም ዐብረዋችሁ አሉ፤ ከወጣትነት ጊዜዬ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ስመራችሁ ቈይቻለሁ። እነሆ፤ ከፊታችሁ ቆሜአለሁ፤ በእግዚአብሔርና እርሱ በቀባው ፊት መስክሩብኝ፤ የማንን በሬ ወሰድሁ? የማንን አህያ ወሰድሁ? ማንን አታለልሁ? በማንስ ላይ ግፍ ሠራሁ? አይቶ እንዳላየ ለመሆንስ ከማን እጅ ጕቦ ተቀበልሁ? ከእነዚህ ሁሉ አንዱን እንኳ አድርጌ ከሆነ እመልስላችኋለሁ።” እነርሱም፣ “አላታለልኸንም ወይም ግፍ አልሠራህብንም፤ ከማንም እጅ አንዳች ነገር አልተቀበልህም” ብለው መለሱለት። ሳሙኤልም፣ “በእጄ ምንም እንዳላገኛችሁ እግዚአብሔርና እርሱ የቀባው ዛሬ በእናንተ ላይ ምስክሮች ናቸው” አላቸው። እነርሱም፣ “እርሱ ምስክር ነው” አሉ።
1 ሳሙኤል 12:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሳሙኤልም እስራኤልን ሁሉ አለ፦ የነገራችሁኝን ሁሉ ሰምቼ አንግሼላችኋለሁ። አሁንም፥ እነሆ፥ ንጉሡ በፊታችሁ ይሄዳል እኔም አርጅቻለሁ ሸምግያለሁም፥ እነሆም፥ ልጆቼ ከእናንተ ጋር ናቸው፥ እኔም ከሕፃንነቴ ጀምሬ እስከ ዛሬ ድረስ በፊታችሁ ሄድሁ። እነሆኝ፥ በእግዚአሔርና እርሱ በቀባው ፊት መስክሩብኝ፥ የማንን በሬ ወሰድሁ? የማንንስ አህያ ወሰድሁ? ማንንስ ሸነገልሁ? በማንስ ላይ ግፍ አደረግሁ? ዓይኖቼንስ ለማሳወር ከማን ጋር እጅ ጉቦ ተቀበልሁ? እኔም እመልስላችኋለሁ። እነርሱም፦ አልሸነገልኸንም፥ ግፍም አላደረግህብንም፥ ከሰውም እጅ ምንም አልወሰድህም አሉ። እርሱም፦ በእጄ ምንም እንዳላገኛችሁ እግዚአብሔርና እርሱ የቀባው ዛሬ በእናንተ ላይ ምስክሮች ናቸው አላቸው፥ እነርሱም፦ ምስክር ነው አሉ።
1 ሳሙኤል 12:1-5 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ሳሙኤል ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ አለ፤ “ጥያቄአችሁን ሁሉ ተቀብዬ ንጉሥ አንግሼላችኋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ የሚመራችሁ ንጉሥ አግኝቼአለሁ፤ እኔ ግን ዕድሜዬ ስለ ገፋ ሸምግዬአለሁ፤ ልጆቼም ከእናንተው ጋር አሉ፤ ከወጣትነት ጊዜዬ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የእናንተ መሪ ሆኜ ቈይቼአለሁ። እነሆ አሁን በፊታችሁ ቆሜአለሁ፤ በእግዚአብሔርና እርሱ በቀባው ንጉሥ ፊት መስክሩብኝ፤ የማንን በሬ ወስጄአለሁ? የማንንስ አህያ ወስጄአለሁ? ማንንስ አታልዬአለሁ? ማንንስ ጨቊኜአለሁ? ፍርድን ለማዛባት ከማን ላይ ጉቦ ተቀብዬአለሁ? ከእነዚህ ሁሉ አንዱን አድርጌ ከሆነ የወሰድኩትን ለመመለስ ዝግጁ ነኝ።” ሕዝቡም “ከቶ አላታለልከንም፤ አልጨቈንከንም፤ ከማንም ሰው ምንም ነገር አልወሰድክም” ሲሉ መለሱለት። ሳሙኤልም “እንግዲህ ዛሬ በፊታችሁ ንጹሕ ሆኜ ስለ መገኘቴ እግዚአብሔርና እርሱ የመረጠው ንጉሥ ምስክሮች ናቸው” አለ። ሕዝቡም “አዎ! እግዚአብሔር ምስክር ነው!” ሲሉ መለሱለት።
1 ሳሙኤል 12:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሳሙኤል ለመላው እስራኤል እንዲህ አለ፤ “እነሆ፤ ያላችሁኝን ሁሉ ሰምቼ ንጉሥ አንግሼላችኋለሁ። ንጉሥ ሆኖ የሚመራችሁንም ሰው እነሆ፤ አግኝታችኋል። እኔም ዕድሜዬ ገፍቷል፤ ጠጉሬም ሸብቷል፤ ልጆቼም አብረዋችሁ አሉ፤ ከወጣትነት ጊዜዬ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ስመራችሁ ቆይቻለሁ። እነሆ፤ ከፊታችሁ ቆሜአለሁ፤ በእግዚአብሔርና እርሱ በቀባው ፊት መስክሩብኝ፤ የማንን በሬ ወሰድሁ? የማንን አህያ ወሰድሁ? ማንን አታለልሁ? በማንስ ላይ ግፍ ሠራሁ? አይቶ እንዳላየ ለመሆንስ ከማን እጅ ጉቦ ተቀበልሁ? ከእነዚህ ሁሉ አንዱን እንኳ አድርጌ ከሆነ እመልስላችኋለሁ።” እነርሱም፥ “አላታለልኸንም ወይም ግፍ አልሠራህብንም፤ ከማንም እጅ አንዳች ነገር አልተቀበልህም” ብለው መለሱለት። ሳሙኤልም፥ “በእጄ ምንም እንዳላገኛችሁ ጌታና እርሱ የቀባው ዛሬ በእናንተ ላይ ምስክሮች ናቸው” አላቸው። እነርሱም፥ “እርሱ ምስክር ነው” አሉ።