1 ሳሙኤል 10:1-16

1 ሳሙኤል 10:1-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ሳሙ​ኤ​ልም የዘ​ይ​ቱን ቀንድ ወስዶ በራሱ ላይ አፈ​ሰ​ሰው፤ ሳመ​ውም፤ እን​ዲ​ህም አለው፥ “በሕ​ዝቡ በእ​ስ​ራ​ኤል ላይ ትነ​ግሥ ዘንድ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቀብ​ቶ​ሃል፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም ሕዝብ ትገ​ዛ​ለህ፤ በዙ​ሪ​ያ​ውም ካሉ ጠላ​ቶ​ቻ​ቸው እጅ ታድ​ና​ቸ​ዋ​ለህ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በር​ስቱ ላይ ትነ​ግሥ ዘንድ እንደ ቀባህ ምል​ክቱ ይህ ነው። ዛሬ ከእኔ በተ​ለ​የህ ጊዜ በብ​ን​ያም ግዛት በቤ​ቴል አው​ራጃ በራ​ሔል መቃ​ብር አጠ​ገብ ሁለት ሰዎች እየ​ቸ​ኰሉ ሲሄዱ ታገ​ኛ​ለህ፤ እነ​ር​ሱም፦ ልት​ፈ​ል​ጉ​አ​ቸው ሂዳ​ችሁ የነ​በ​ራ​ች​ሁ​ላ​ቸው አህ​ዮች ተገ​ኝ​ተ​ዋል፤ እነ​ሆም፥ አባ​ትህ ስለ አህ​ዮቹ ማሰብ ትቶ፦ የል​ጄን ነገር እን​ዴት አደ​ር​ጋ​ለሁ? እያለ ስለ እና​ንተ ይጨ​ነ​ቃል ይሉ​ሃል። ከዚ​ያም ደግሞ አል​ፈህ፥ ወደ ትልቁ የታ​ቦር ዛፍ ትደ​ር​ሳ​ለህ፤ በዚ​ያም ሦስት ሰዎች፥ አንዱ ሦስት የፍ​የል ጠቦ​ቶች ሲነዳ፥ ሁለ​ተ​ኛው ሦስት የዳቦ ስልቻ፥ ሦስ​ተ​ኛ​ውም የወ​ይን ጠጅ አቁ​ማዳ ይዘው ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ወደ ቤቴል ሲወጡ ታገ​ኛ​ለህ፤ ሰላ​ም​ታም ይሰ​ጡ​ሃል፤ የመ​ጀ​መ​ሪ​ያ​ዎ​ቹን ሁለት ዳቦ​ዎ​ችም ይሰ​ጡ​ሃል፤ ከእ​ጃ​ቸ​ውም ትቀ​በ​ላ​ለህ። ከዚ​ያም በኋላ የፍ​ል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ው​ያን ጭፍራ ወዳ​ለ​በት ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ኮረ​ብታ ትመ​ጣ​ለህ፤ በዚ​ያም ፍል​ስ​ጥ​ኤ​ማ​ዊው ናሴብ አለ፤ ወደ​ዚ​ያም ወደ ከተ​ማ​ዪቱ በደ​ረ​ስህ ጊዜ በገ​ናና ከበሮ፥ እም​ቢ​ል​ታና መሰ​ንቆ ይዘው ትን​ቢት እየ​ተ​ና​ገሩ ከኰ​ረ​ብ​ታው መስ​ገጃ የሚ​ወ​ርዱ የነ​ቢ​ያ​ትን ጉባኤ ታገ​ኛ​ለህ። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መን​ፈስ በአ​ንተ ይወ​ር​ዳል፤ ከእ​ነ​ር​ሱም ጋር ትን​ቢት ትና​ገ​ራ​ለህ፤ እንደ ሌላም ሰው ሆነህ ትለ​ወ​ጣ​ለህ። እነ​ዚ​ህም ምል​ክ​ቶች በደ​ረ​ሱህ ጊዜ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከአ​ንተ ጋር ነውና እጅህ የም​ት​ች​ለ​ውን ሁሉ አድ​ርግ። በፊ​ቴም ወደ ጌል​ገላ ትወ​ር​ዳ​ለህ፤ እኔም እነሆ፥ የሚ​ቃ​ጠ​ለ​ውን መሥ​ዋ​ዕት አቀ​ርብ ዘንድ፥ የደ​ኅ​ን​ነ​ት​ንም መሥ​ዋ​ዕት እሠዋ ዘንድ ወደ አንተ እወ​ር​ዳ​ለሁ፤ እኔ ወደ አንተ እስ​ክ​መ​ጣና የም​ታ​ደ​ር​ገ​ውን እስ​ከ​ም​ነ​ግ​ርህ ድረስ ሰባት ቀን ትቈ​ያ​ለህ።” ከሳ​ሙ​ኤ​ልም ዘንድ ለመ​ሄድ ፊቱን በመ​ለሰ ጊዜ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሌላ ልብ ለወ​ጠ​ለት፤ በዚ​ያም ቀን እነ​ዚህ ምል​ክ​ቶች ሁሉ ደረ​ሱ​ለት። ወደ​ዚ​ያም ኮረ​ብታ በደ​ረሰ ጊዜ፥ እነሆ፥ የነ​ቢ​ያት ጉባኤ አገ​ኙት፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም መን​ፈስ በእ​ርሱ ላይ ወረደ፤ በመ​ካ​ከ​ላ​ቸ​ውም ትን​ቢት ተና​ገረ። ቀድ​ሞም የሚ​ያ​ው​ቁት ሁሉ በነ​ቢ​ያት መካ​ከል ባዩት ጊዜ ሕዝቡ እርስ በር​ሳ​ቸው፥ “በቂስ ልጅ ላይ የሆ​ነው ምን​ድን ነው? በውኑ ሳኦል ከነ​ቢ​ያት ወገን ነውን?” ተባ​ባሉ። ከዚ​ያም ስፍራ ያለ አንድ ሰው፥ “አባ​ቱስ ማን ነው?” ብሎ መለሰ። ስለ​ዚ​ህም “ሳኦል ደግሞ ከነ​ቢ​ያት ወገን ነውን?” የሚል ምሳሌ ሆነ። ትን​ቢት መና​ገ​ሩ​ንም በፈ​ጸመ ጊዜ ወደ ኮረ​ብ​ታው ወጣ። ከቤተ ሰቡም አንዱ እር​ሱ​ንና ብላ​ቴ​ና​ውን፥ “ወዴት ሄዳ​ችሁ ኖሮ​አል?” አላ​ቸው። እነ​ር​ሱም፥ “አህ​ዮ​ችን ልን​ፈ​ልግ ሄደን ነበር፤ ባጣ​ና​ቸ​ውም ጊዜ ወደ ሳሙ​ኤል መጣን” አሉት። ያም ቤተ ሰብ፥ “ሳሙ​ኤል ምን አለ? እባ​ክህ! ንገ​ረኝ” አለው፤ ሳኦ​ልም ለቤተ ሰቡ፥ “አህ​ዮች እንደ ተገኙ ገለ​ጠ​ልን” አለው፤ ነገር ግን የመ​ን​ግ​ሥ​ትን ነገር አላ​ወ​ራ​ለ​ትም።

1 ሳሙኤል 10:1-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚያም ሳሙኤል የዘይቱን ብርሌ ወስዶ፣ ዘይቱን በሳኦል ራስ ላይ ካፈሰሰ በኋላ እንዲህ ሲል ሳመው፤ “በርስቱ ላይ ገዥ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶህ የለምን? ዛሬ ከእኔ ተለይተህ ስትሄድ፣ በብንያም ወሰን ላይ በምትገኘው ጼልጻህ በተባለች ስፍራ በራሔል መቃብር አጠገብ ሁለት ሰዎች ታገኛለህ። እነርሱም፣ ‘የምትፈልጋቸው አህዮች ተገኝተዋል፤ አሁን አባትህ ስለ አህዮቹ ማሰቡን ትቶ፣ “ስለ ልጄ ምን ባደርግ ይሻለኛል?” እያለ በመጨነቅ ላይ ነው’ ይሉሃል። “አንተም ጕዞህን በመቀጠል በታቦር እስካለው እስከ ትልቁ ዛፍ ድረስ ትሄዳለህ፤ እዚያም ሦስት ሰዎች፣ አንዱ ሦስት የፍየል ግልገል፣ ሌላው ሦስት ዳቦ፣ ሌላው ደግሞ የወይን ጠጅ የተሞላበት አቍማዳ ይዘው ወደ እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ሲወጡ ያገኙሃል። እነርሱም ሰላም ይሉሃል፤ ሁለት ዳቦ ይሰጡሃል፤ አንተም ትቀበላቸዋለህ። “ከዚያ በኋላ የፍልስጥኤማውያን ጦር ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወደ ጊብዓ ትሄዳለህ። ወደ ከተማዪቱ እንደ ደረስህም የነቢያት ጉባኤ በመሰንቆ፣ በከበሮ፣ በእንቢልታና በበገና ታጅበው ትንቢት እየተናገሩ ከማምለኪያው ኰረብታ ላይ ሲወርዱ ታገኛቸዋለህ። የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ይወርድብሃል፤ ከእነርሱ ጋራ ትንቢት ትናገራለህ፤ እንደ ሌላ ሰውም ሆነህ ትለወጣለህ። እነዚህ ምልክቶች በተፈጸሙ ጊዜ እጅህ ማድረግ የምትችለውን ሁሉ አድርግ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ነውና። “ከፊቴ ቀድመህ ወደ ጌልገላ ውረድ፤ እኔም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕቱን ለማቅረብ ወደ አንተ እመጣለሁ፤ ነገር ግን ወደ አንተ መጥቼ ምን ማድረግ እንዳለብህ እስክነግርህ ድረስ ሰባት ቀን መቈየት አለብህ።” ሳኦል ከሳሙኤል ተለይቶ ለመሄድ ፊቱን በመለሰ ጊዜ፣ እግዚአብሔር የሳኦልን ልብ ለወጠው፤ ምልክቱም ሁሉ በዚያ ዕለት ተፈጸመ። ጊብዓ በደረሱ ጊዜ የነቢያቱ ጉባኤ አገኙት፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ወረደበት፤ ከእነርሱም ጋራ ትንቢት ተናገረ። ቀድሞ የሚያውቁት ሁሉ ከነቢያቱ ጋራ ትንቢት ሲናገር ባዩት ጊዜ፣ እርስ በርሳቸው፣ “የቂስን ልጅ ምን ነካው? ሳኦልም ከነቢያት ወገን ነውን?” ሲሉ ተጠያየቁ። በዚያ ነዋሪ የሆነ አንድ ሰው፣ “የእነርሱስ አባት ማን ነው?” ብሎ መለሰ። ስለዚህ፣ “ሳኦልም ከነቢያት ወገን ነውን?” የሚል ምሳሌያዊ አነጋገር ሆነ። ሳኦል ትንቢት መናገሩን ከፈጸመ በኋላ ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ሄደ። በዚህ ጊዜ የሳኦል አጎት እርሱንና አገልጋዩን፣ “የት ነበራችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እርሱም፣ “አህዮቹን ፍለጋ ሄደን ነበር፤ እንደማይገኙ በተረዳን ጊዜ ግን ወደ ሳሙኤል ሄድን” አለው። የሳኦል አጎትም፣ “እባክህ፣ ሳሙኤል ያለህን ንገረኝ” አለው። ሳኦልም መልሶ፣ “አህዮቹ መገኘታቸውን ገልጾ ነገረን” አለው። ይሁን እንጂ ስለ መንገሡ ሳሙኤል የነገረውን ለአጎቱ አልተናገረም።

1 ሳሙኤል 10:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ሳሙኤልም የዘይቱን ብርሌ ወስዶ በራሱ ላይ አፈሰሰው፥ ሳመውም፥ እንዲህም አለው፦ በርስቱ ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶሃል፥ የእግዚአብሔርንም ሕዝብ ትገዛለህ፥ በዙሪያውም ካሉ ጠላቶቻቸው እጅ ታድናቸዋለህ። ዛሬ ከእኔ በተለየህ ጊዜ በብንያም ዳርቻ በጼልጻህ አገር ባለው በራሔል መቃብር አጠገብ ሁለት ሰዎች ታገኛለህ፥ እነርሱም፦ ልትሻቸው ሄደህ የነበርህላቸው አህዮች ተገኝተዋል፥ እነሆም፥ አባትህ ስለ አህዮች ማሰብ ትቶ፥ የልጄን ነገር እንዴት አደርጋለሁ? እያለ ስለ እናንተ ይጨነቃል ይሉሃል። ከዚያም ደግሞ ወደ ፊት ትሄዳለህ፥ ወደ ታቦር ወደ ትልቁ ዛፍ ትደርሳለህ፥ በዚያም ሦስት ሰዎች፥ አንዱ ሦስት የፍየል ጠቦቶች፥ ሁለተኛው ሦስት ዳቦ፥ ሦስተኛውም የወይን ጠጅ አቁማዳ ይዘው ወደ እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ሲወጡ ያገኙሃል፥ ሰላምታም ይሰጡሃል፥ ሁለትም ዳቦ ይሰጡሃል፥ ከእጃቸውም ትቀበላለህ። ከዚያም በኋላ የፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ኮረብታ ትመጣለህ፥ ወደዚያም ወደ ከተማይቱ በደረስህ ጊዜ፥ በገናና ከበሮ እምቢልታና መሰንቆ ይዘው ትንቢት እየተናገሩ ከኮረብታው መስገጃ የሚወርዱ የነቢያት ጉባኤ ያገኙሃል። የእግዚአብሔርም መንፈስ በኃይል ይወርድብሃል፥ ከእነርሱም ጋር ትንቢት ትናገራለህ፥ እንደ ሌላ ሰውም ሆነህ ትለወጣለህ። እነዚህም ምልክቶች በደረሱህ ጊዜ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና እጅህ የምታገኘውን ሁሉ አድርግ። በፊቴም ወደ ጌልገላ ትወርዳለህ፥ እኔም፥ እነሆ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀርብ ዘንድ፥ የደኅንነትም መሥዋዕት እሠዋ ዘንድ ወደ አንተ እወርዳለሁ፥ እኔ ወደ አንተ እስክመጣና የምታደረገውን እስክነግረህ ድረስ ሰባት ቀን ትቆያለህ። ከሳሙኤልም ዘንድ ለመሄድ ፊቱን በመለሰ ጊዜ እግዚአብሔር ሌላ ልብ ለወጠለት፥ በዚያም ቀን እነዚህ ምልክቶች ሁሉ ደረሱለት። ወደዚያም ኮረብታ በደረሰ ጊዜ፥ እነሆ፥ የነቢያት ጉባኤ አገኙት፥ የእግዚአብሔርም መንፈስ በኃይል ወረደበት፥ በመካከላቸውም ትንቢት ተናገረ። ቀድሞም የሚያውቁት ሁሉ ከነቢያት ጋር ትንቢት ሲናገር ባዩት ጊዜ ሕዝቡ እርስ በርሳቸው፦ የቂስን ልጅ ያገኘው ምንድር ነው? በውኑ ሳኦል ከነቢያት ወገን ነውን? ተባባሉ። ከዚያም ስፍራ ያለ አንድ ሰው፦ አባታቸውስ ማን ነው? ብሎ መለሰ። ስለዚህም፦ ሳኦል ደግሞ ከነቢያት ወገን ነውን? የሚል ምሳሌ ሆነ። ትንቢት መናገሩንም በፈጸመ ጊዜ ወደ ኮረብታው መስገጃ መጣ። አጎቱም ሳኦልንና ብላቴናውን፦ ወዴት ሄዳችሁ ኖርአል? አላቸው። እርሱም፦ አህዮችን ልንሻ ሄደን ነበር፥ ባጣናቸውም ጊዜ ወደ ሳሙኤል መጣን አለ። የሳኦልም አጎት፦ ሳሙኤል የነገረህን፥ እባክህ፥ ንገረኝ አለው። ሳኦልም አጎቱን፦ አህዮች እንደ ተገኙ ገለጠልን አለው፥ ነገር ግን ሳሙኤልን የነገረውን የመንግሥትን ነገር አላወራለትም።

1 ሳሙኤል 10:1-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ሳሙኤል የወይራ ዘይት መያዣውን ቀንድ ወስዶ በሳኦል ራስ ላይ አፈሰሰው፤ ሳመውም። ከዚያም በኋላ “እግዚአብሔር በሕዝቡ በእስራኤል ላይ መሪ እንድትሆን ቀባህ፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ነግሠህ በዙሪያቸው ካሉ ጠላቶች ታድናቸዋለህ እግዚአብሔር በርስቱ ላይ የሾመህ ለመሆኑ ይህ ማስረጃ ነው፤ ዛሬ ከእኔ ተለይተህ በምትሄድበት ጊዜ፥ በብንያም ግዛት በሚገኘው ጼልጻሕ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ባለው በራሔል መቃብር አጠገብ ሁለት ሰዎች ታገኛለህ፤ እነርሱም ስትፈልጋቸው የነበሩ አህዮች መገኘታቸውንና አባትህም ስለ እነርሱ ማሰቡን ትቶ ስለ አንተ በመጨነቅ ‘እንግዲህ ስለ ልጄ ምን ላድርግ’ እያለ በመጠየቅ ላይ መሆኑን ይነግሩሃል። ከዚያም አልፈህ በታቦር ወደሚገኘው ወደ አንድ ትልቅ ዛፍ ትደርሳለህ፤ እዚያም ወደ ቤትኤል ወደ እግዚአብሔር የሚሄዱ ሦስት ሰዎችን ታገኛለህ፤ ከእነርሱ አንዱ ሦስት የፍየል ጠቦቶችን እየሳበ የሚሄድ ሲሆን ሁለተኛው ሰው ሦስት ኅብስት የተሸከመ ነው፤ ሦስተኛውም የወይን ጠጅ የተሞላበት አቁማዳ የተሸከመ ይሆናል፤ እነርሱም ሰላምታ ከሰጡህ በኋላ ከኅብስቶቹ ሁለቱን ይሰጡሃል፤ አንተም መቀበል ይገባሃል፤ ከዚያም አልፈህ የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር ወደሚገኝበት ጊብዓ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ እግዚአብሔር ኮረብታ ትመጣለህ፤ ወደ ከተማይቱም መግቢያ በር በምትደርስበትም ጊዜ በኮረብታው ላይ መሥዋዕት አቅርበው የሚመለሱ የነቢያትን ጉባኤ ታገኛለህ፤ እነርሱም በገና እየደረደሩ፥ ከበሮ እየመቱ፥ ዋሽንት እየነፉ፥ በመሰንቆ ዜማ ሲዘምሩና ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ትንቢት ሲናገሩ ታገኛቸዋለህ። በድንገት የእግዚአብሔር መንፈስ በአንተ ላይ በኀይል ይወርዳል፤ ከእነርሱም ጋር ትንቢት መናገር ትጀምራለህ፤ ልዩ ሰውም ትሆናለህ፤ እነዚህም ምልክቶች በተፈጸሙ ጊዜ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ስለ ሆነ ማድረግ የሚገባህን ሁሉ አድርግ፤ የሚቃጠለውንና የደኅንነት መሥዋዕት ለማቅረብ አንተን ወደማገኝበት ወደ ጌልጌላ ቀድመኸኝ ትሄዳለህ፤ እኔ መጥቼ ምን ማድረግ እንደሚገባህ እስክነግርህ ድረስ ለሰባት ቀን በዚያው ቈይ።” ሳኦልም ከሳሙኤል ተለይቶ በሄደ ጊዜ እግዚአብሔር ሳኦልን ሌላ አዲስ ሰው አደረገው፤ ሳሙኤል በምልክት የነገረውም ሁሉ በዚያን ቀን ተፈጸመ። ሳኦል ወደ ጊብዓ በደረሰ ጊዜ የነቢያት ጉባኤ ከሳኦል ጋር ተገናኘ፤ በድንገት የእግዚአብሔር መንፈስ በሳኦል ላይ ወረደ፤ በዚያን ጊዜም እርሱ ከእነርሱ ጋር ትንቢት መናገር ጀመረ። ከዚያ በፊት እርሱን የሚያውቁትም ሰዎች ይህን ሲያደርግ በተመለከቱ ጊዜ “የቂስን ልጅ ምን ነካው? ሳኦል ደግሞ ከነቢያት ወገን ነውን?” በማለት እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። በዚያም የሚኖር አንድ ሰው “የእነዚህስ የሌሎቹ ነቢያት ሁኔታ እንዴት ነው? አባቶቻቸውስ እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀ፤ “ሳኦልም ደግሞ ከነቢያት ወገን ነውን?” የሚል የምሳሌ አነጋገር የመነጨውም ከዚህ ነው። ሳኦልም ትንቢት መናገሩን ከፈጸመ በኋላ በኮረብታው ላይ ወደሚገኘው መሠዊያ ወጣ። የሳኦል አጐት ሳኦልንና አገልጋዩን አይቶ “የት ነበራችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። ሳኦልም “አህዮች ልንፈልግ ሄደን ልናገኛቸው ስላልቻልን ሳሙኤልን ለመጠየቅ ጎራ ብለን ነበር” ሲል መለሰለት። አጐትየውም “ሳሙኤል የነገረህን ንገረኝ” አለው። ሳኦልም “የአህዮቹን መገኘት ነግሮናል” ሲል መለሰለት፤ ነገር ግን ንጉሥ ስለ መሆኑ ሳሙኤል የነገረውን ሁሉ ለአጐቱ አላወራለትም።

1 ሳሙኤል 10:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከዚያም ሳሙኤል የዘይቱን ብርሌ ወስዶ፥ ዘይቱን በሳኦል ራስ ላይ ካፈሰሰ በኋላ ሳመው፥ እንዲህም አለው፤ “በርስቱ ላይ ገዥ ትሆን ዘንድ ጌታ ቀብቶህ የለምን? ዛሬ ከእኔ ተለይተህ ስትሄድ፥ በብንያም ወሰን ላይ በምትገኘው ጼልጻህ በተባለች ስፍራ በራሔል መቃብር አጠገብ ሁለት ሰዎች ታገኛለህ። እነርሱም፥ ‘የምትፈልጋቸው አህዮች ተገኝተዋል፤ አሁን አባትህ ስለ አህዮቹ ማሰቡን ትቶ፥ ስለ ልጄ ምን ባደርግ ይሻለኛል?’ እያለ በመጨነቅ ላይ ነው” ይሉሃል። “አንተም ጉዞህን በመቀጠል በታቦር እስካለው ባሉጥ ዛፍ ድረስ ትሄዳለህ፤ እዚያም ሦስት ሰዎች፥ አንዱ ሦስት የፍየል ግልገል፥ ሌላው ሦስት ዳቦ፥ ሌላው ደግሞ የወይን ጠጅ የተሞላበት አቁማዳ ይዘው ወደ እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ሲወጡ ያገኙሃል። እነርሱም ሰላም ይሉሃል፤ ሁለት ዳቦ ይሰጡሃል፤ አንተም ከእጃቸው ትቀበላለህ። ከዚያ በኋላ የፍልስጥኤማውያን ጦር ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወደ ጊብዓ ትሄዳለህ። ወደ ከተማዪቱ እንደ ደረስክም የነቢያት ጉባኤ በበገና፥ በከበሮ፥ በዋሽንትና በመሰንቆ ታጅበው ትንቢት እየተናገሩ ከማምለኪያው ኰረብታ ላይ ሲወርዱ ታገኛቸዋለህ። የጌታም መንፈስ በኃይል ይወርድብሃል፤ ከእነርሱም ጋር ትንቢት ትናገራለህ፤ እንደ ሌላ ሰውም ሆነህ ትለወጣለህ። እነዚህ ምልክቶች በተፈጸሙ ጊዜ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና እጅህ ማድረግ የምትችለውን ሁሉ አድርግ። ከፊቴ ቀድመህ ወደ ጌልገላ ውረድ፤ እኔም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነትት መሥዋዕቱን ለማቅረብ ወደ አንተ እመጣለሁ፤ ወደ አንተ መጥቼ ምን ማድረግ እንዳለብህ እስክነግርህ ድረስ ግን ሰባት ቀን መቆየት አለብህ።” ሳኦል ከሳሙኤል ተለይቶ ለመሄድ ፊቱን በመለሰ ጊዜ፥ እግዚአብሔር የሳኦልን ልብ ለወጠው፤ ምልክቱም ሁሉ በዚያ ዕለት ተፈጸመ። ጊብዓ በደረሱ ጊዜ፥ እነሆ የነቢያቱ ጉባኤ አገኙት፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል ወረደበት፤ ከእነርሱም ጋር ትንቢት ተናገረ። ቀድሞ የሚያውቁት ሁሉ ከነቢያቱ ጋር ትንቢት ሲናገር ባዩት ጊዜ፥ እርስ በርሳቸው፥ “የቂስን ልጅ ምን ነካው? ሳኦልም ከነቢያት ወገን ነውን?” ሲሉ ተጠያየቁ። በዚያ ነዋሪ የሆነ አንድ ሰው፥ “አባታቸውስ ማን ነው?” ብሎ መለሰ። ስለዚህ፥ “ሳኦልም ከነቢያት ወገን ነውን?” የሚል ምሳሌያዊ አነጋገር ሆነ። ሳኦል ትንቢት መናገሩን ከፈጸመ በኋላ ወደ ማምለኪያው ኰረብታ ሄደ። በዚህ ጊዜ የሳኦል አጎት እርሱንና አገልጋዩን፥ “የት ነበራችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እርሱም፥ “አህዮቹን ፍለጋ ሄደን ነበር፤ እንደማይገኙ በተረዳን ጊዜ ግን ወደ ሳሙኤል ሄድን” አለው። የሳኦል አጎትም፥ “እባክህ፥ ሳሙኤል ያለህን ንገረኝ” አለው። ሳኦልም መልሶ፥ “አህዮቹ መገኘታቸውን ገልጦ ነገረን” አለው። ነገር ግን ስለ መንገሡ ሳሙኤል የነገረውን ለአጎቱ አልተናገረም።