1 ሳሙኤል 1:4-7
1 ሳሙኤል 1:4-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሕልቃናም የሚሠዋበት ቀን በደረሰ ጊዜ ለሚስቱ ለፍናናና ለልጆችዋ ሁሉ ዕድል ፋንታቸውን ሰጣቸዉ። ለሐናም ልጅ ስላልነበራት አንድ ዕድል ፋንታ ሰጣት፤ ሕልቃናም ከዚያችኛይቱ ይልቅ ሐናን ይወድድ ነበር። እግዚአብሔር ግን ማኅፀንዋን ዘግቶ ነበር። እንደ መከራዋና እንደ ኀዘንዋም እግዚአብሔር ልጅ አልሰጣትም ነበር። ስለዚህም ታዝን ነበር። እግዚአብሔር ማኅፀንዋን ዘግትዋልና፥ ልጆችንም አልሰጣትምና። በየዓመቱም ወደ እግዚአብሔር ቤት በሚወጣበት ጊዜ እንዲህ ያደርግ ነበር፤ እርስዋም ትበሳጭና ታለቅስ ነበር። እህልም አትበላም ነበር።
1 ሳሙኤል 1:4-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሕልቃና ወደ ሴሎ ሄዶ መሥዋዕት የሚሠዋበት ወቅት በደረሰ ጊዜ ሁሉ፣ ለሚስቱ ለፍናና እንዲሁም ለወንዶችና ለሴቶች ልጆቿ ሁሉ ከሥጋው ድርሻቸውን ይሰጣቸው ነበር። ሐናን ግን ይወድዳት ስለ ነበር፣ ዕጥፍ ድርሻ ይሰጣት ነበር፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ማሕፀኗን ዘግቶት ነበር። እግዚአብሔር ማሕፀኗን ስለ ዘጋም ጣውንቷ ታስቈጣት፣ ታበሳጫትም ነበር። ይህም በየዓመቱ ይደጋገም ነበር፤ ሐና ወደ እግዚአብሔር ቤት በምትወጣበት ጊዜ ሁሉ፣ እስክታለቅስና መብላት እስኪያቅታት ድረስ ጣውንቷ ታበሳጫት ነበር።
1 ሳሙኤል 1:4-7 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሕልቃና የሚሠዋበት ቀን በደረሰ ጊዜም ለሚስቱ ለፍናና ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችዋ ሁሉ እድል ፈንታቸውን ሰጣቸው። ሐናንም ይወድድ ነበርና ለሐና ሁለት እጥፍ እድል ፈንታ ሰጣት፥ እግዚአብሔር ግን ማኅፀንዋን ዘግቶ ነበርና ጣውንትዋ ታስቆጣት ታበሳጫትም ነበር። በየዓመቱም እንዲህ ባደረገ ጊዜ እርስዋም ወደ እግዚአብሔር በምትወጣበት ጊዜ ታበሳጫት ነበር፥ ሐናም ታለቅስ ነበር፥ አንዳችም አትቀምስም ነበር።
1 ሳሙኤል 1:4-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሕልቃና መሥዋዕቱን በሚያቀርብበት ጊዜ ሁሉ ከመሥዋዕቱ ሥጋ አንድ ድርሻ ለጵኒና ይሰጣል፤ እንዲሁም ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችዋ ለእያንዳንዳቸው አንዳንድ ድርሻ ያድላል፤ ሐናን ይወዳት ስለ ነበር እጥፍ ድርሻ ይሰጣት ነበር፤ ቢሆንም እግዚአብሔር ልጅ ስላልሰጣት መኻን ነበረች፤ እግዚአብሔርም ልጅ ስላልሰጣት ጣውንትዋ ጵኒና ሐናን የሚያስቈጣ ነገር በመፈለግ ታበሳጫት ነበር፤ ይህም ሳይቋረጥ በየዓመቱ የሚደጋገም ነገር ነበር፤ ይኸውም ወደ እግዚአብሔር ቤት በሄዱ ቊጥር ሐና እያለቀሰች ምግብ ለመብላት እምቢ እስከምትል ድረስ ጵኒና በብርቱ ታበሳጫት ነበር።
1 ሳሙኤል 1:4-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሕልቃና መሥዋዕት የሚሠዋበት ወቅት በደረሰ ጊዜ ሁሉ፥ ለሚስቱ ለጵኒና እንዲሁም ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችዋ ሁሉ ድርሻቸውን ይሰጣቸው ነበር። ሐናንም ይወዳት ስለ ነበር ዕጥፍ ድርሻ ይሰጣት ነበር፤ ይሁን እንጂ ጌታ ማሕፀኗን ዘግቶት ነበር። ጌታ ማሕፀኗን ስለዘጋም ጣውንቷ ሆን ብላ ታስቆጣት፥ ታበሳጫትም ነበር። ወደ ጌታ ቤት በምትወጣበት ጊዜ ሁሉ ይህ በየዓመቱ ይደጋገም ነበር፤ እስክታለቅስና መብላት እስኪያቅታት ድረስ ታበሳጫት ነበር።