1 ጴጥሮስ 2:9-25
1 ጴጥሮስ 2:9-25 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤ እናንተ ቀድሞ ወገን አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ፤ እናንተ ምሕረት ያገኛችሁ አልነበራችሁም፤ አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል። ወዳጆች ሆይ! ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ እለምናችኋለሁ፤ ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፥ ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት ነገር፥ በሚጎበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን። ስለ ጌታ ብላችሁ ለሰው ሥርዐት ሁሉ ተገዙ፤ ለንጉሥም ቢሆን፥ ከሁሉ በላይ ነውና፤ ለመኳንንትም ቢሆን፥ ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ከእርሱ ተልከዋልና ተገዙ። በጎ እያደረጋችሁ፥ የማያውቁትን ሞኞች ዝም ታሰኙ ዘንድ እንዲህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና፤ አርነት ወጥታችሁ እንደ እግዚአብሔር ባሪያዎች ሁኑ እንጂ ያ አርነት ለክፋት መሸፈኛ እንዲሆን አታድርጉ። ሁሉን አክብሩ፤ ወንድሞችን ውደዱ፤ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ንጉሥን አክብሩ። ሎሌዎች ሆይ! ለበጎዎችና ለገሮች ጌቶቻችሁ ብቻ ሳይሆን ለጠማሞች ደግሞ በፍርሃት ሁሉ ተገዙ። በግፍ መከራን የሚቀበል ሰው እግዚአብሔርን እያሰበ ሐዘንን ቢታገሥ ምስጋና ይገባዋልና። ኀጢአት አድርጋችሁ ስትጎሰሙ ብትታገሡ፥ ምን ክብር አለበት? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሡ፥ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ይገባዋል። የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። “እርሱም ኀጢአት አላደረገም፤ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤” ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራንም ሲቀበል አልዛተም፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ ለኀጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኀጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ። እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።
1 ጴጥሮስ 2:9-25 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ የተቀደሰ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ገንዘቡ ያደረገው ሕዝብ ናችሁ። ቀድሞ የርሱ ወገን አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆናችኋል፤ ቀድሞ ምሕረትን አላገኛችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል። ወዳጆች ሆይ፤ በዚህ ዓለም እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ መጠን፣ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት እንድትርቁ እለምናችኋለሁ። ምንም እንኳ ክፉ እንደምትሠሩ አድርገው ቢያሟችሁም፣ ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ መልካሙን ሥራችሁን አይተው እግዚአብሔርን እንዲያከብሩ፣ በአሕዛብ መካከል በመልካም ሕይወት ኑሩ። ስለ ጌታ ብላችሁ ለምድራዊ ባለሥልጣን ሁሉ ተገዙ፤ የበላይ ባለሥልጣን ስለ ሆነ ለንጉሥ ቢሆን፣ ወይም ክፉ አድራጊዎችን ለመቅጣትና በጎ አድራጊዎችን ለማመስገን እርሱ ለሾማቸው ገዦች ታዘዙ፤ ምክንያቱም፣ መልካም በማድረግ የአላዋቂዎችን ከንቱ ንግግር ዝም እንድታሰኙ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። እንደ እግዚአብሔር ባሮች ሆናችሁ በነጻነት ኑሩ እንጂ ነጻነታችሁን የክፋት መሸፈኛ አታድርጉት። ለሰው ሁሉ ተገቢውን አክብሮት ስጡ፤ ወንድሞችን ውደዱ፤ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ንጉሥን አክብሩ። እናንተ አገልጋዮች ሆይ፤ ለደጎችና ለገሮች ጌቶቻችሁ ብቻ ሳይሆን፣ ለክፉዎችም በፍጹም አክብሮት ታዘዙ። ስለ እግዚአብሔር ሲል የግፍ መከራን የሚቀበል ሰው ምስጋናን ያገኛል። ክፉ ሥራ ሠርታችሁ ብትቀጡና ብትታገሡ ምን ምስጋና ይኖራችኋል? ነገር ግን መልካም ሥራ ሠርታችሁ መከራ ብትቀበሉና ብትታገሡ ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ያስገኝላችኋል። የተጠራችሁትም ለዚሁ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው። “እርሱ ኀጢአት አላደረገም፤ በአፉም ተንኰል አልተገኘበትም።” ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ። ለኀጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እርሱ ራሱ በሥጋው ኀጢአታችንን በዕንጨት መስቀል ላይ ተሸከመ፤ በርሱ ቍስል እናንተ ተፈውሳችኋል። ቀድሞ እንደ ጠፉ በጎች ትቅበዘበዙ ነበር፤ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።
1 ጴጥሮስ 2:9-25 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤ እናንተ ቀድሞ ወገን አልነበራችሁም አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ፤ እናንተ ምሕረት ያገኛችሁ አልነበራችሁም አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል። ወዳጆች ሆይ፥ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ እለምናችኋለሁ፤ ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፥ ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት ነገር፥ በሚጎበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን። ስለ ጌታ ብላችሁ ለሰው ሥርዓት ሁሉ ተገዙ፤ ለንጉሥም ቢሆን፥ ከሁሉ በላይ ነውና፤ ለመኳንንትም ቢሆን፥ ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ከእርሱ ተልከዋልና ተገዙ። በጎ እያደረጋችሁ፥ የማያውቁትን ሞኞች ዝም ታሰኙ ዘንድ እንዲህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና፤ አርነት ወጥታችሁ እንደ እግዚአብሔር ባሪያዎች ሁኑ እንጂ ያ አርነት ለክፋት መሸፈኛ እንዲሆን አታድርጉ። ሁሉን አክብሩ፥ ወንድሞችን ውደዱ፥ እግዚአብሔርን ፍሩ፥ ንጉሥን አክብሩ። ሎሌዎች ሆይ፥ ለበጎዎችና ለገሮች ጌቶቻችሁ ብቻ ሳይሆን ለጠማሞች ደግሞ በፍርሃት ሁሉ ተገዙ። በግፍ መከራን የሚቀበል ሰው እግዚአብሔርን እያሰበ ኃዘንን ቢታገሥ ምስጋና ይገባዋልና። ኃጢአት አድርጋችሁ ስትጎሰሙ ብትታገሡ፥ ምን ክብር አለበት? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሡ፥ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ይገባዋል። የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና። እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኵኦልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ። እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።
1 ጴጥሮስ 2:9-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚያስደንቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን አስደናቂ ሥራ እንድታውጁ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ እግዚአብሔር ለራሱ ያደረጋችኹ ቅዱስ ሕዝብ ናችሁ። እናንተ ቀድሞ የእግዚአብሔር ሕዝብ አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ናችሁ፤ ቀድሞ ምሕረት አላገኛችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረት አግኝታችኋል። ወዳጆች ሆይ፥ በዚህ ዓለም እንግዶችና መጻተኞች ስለ ሆናችሁ ከነፍስ ጋር ከሚዋጉት ከሥጋ ፍትወቶች እንድትርቁ ዐደራ እላችኋለሁ። ምናልባት “ክፉ አድራጊዎች ናቸው” ብለው ቢያሙአችሁም እንኳ እግዚአብሔር እኛን ለመጐብኘት በሚመጣበት ቀን አሕዛብ መልካም ሥራችሁን አይተው እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ በእነርሱ መካከል ስትኖሩ መልካም ጠባይ ይኑራችሁ። ስለ ጌታ ኢየሱስ ብላችሁ ሥልጣን ለተሰጣቸው ሕዝባዊ ድርጅቶች ታዘዙ፤ የበላይ ባለሥልጣን ስለ ሆነ ለንጉሠ ነገሥቱም ታዘዙ። ለአገረ ገዢዎችም ታዘዙ፤ እነርሱ ክፉ አድራጊዎችን ለመቅጣት፥ መልካም አድራጊዎችን ለማመስገን ከንጉሠ ነገሥቱ የሚላኩ ናቸው። መልካም በማድረግ የሞኞችን አላዋቂ ንግግር ዝም እንድታሰኙ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ሆናችሁ በነጻነት ኑሩ እንጂ ነጻነታችሁን የክፋት መሸፈኛ አታድርጉት። ሰውን ሁሉ አክብሩ፤ ወንድሞችን ውደዱ፤ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ንጉሥን አክብሩ። እናንተ አገልጋዮች ለጌቶቻችሁ በአክብሮት ታዘዙ፤ የምትታዘዙትም ለደጎቹና ለገሮቹ ብቻ ሳይሆን ለክፉዎችም ነው። ሰው የሚመሰገነው በግፍ መከራ ሲቀበል ስለ እግዚአብሔር ብሎ ቢታገሥ ነው። ክፉ አድርጋችሁ ቅጣት ስትቀበሉ ብትታገሡ ምን ምስጋና ይኖራችኋል? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራ ስትቀበሉ ብትታገሡ ከእግዚአብሔር ምስጋና ታገኛላችሁ። የተጠራችሁትም ለዚሁ ነው፤ የእርሱን አርአያነት እንድትከተሉ ክርስቶስ ለእናንተ መከራን በመቀበል ምሳሌ ሆኖላችኋል። እርሱ ምንም ኃጢአት አላደረገም፤ በአፉ ተንኰል አልተገኘበትም። ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራን ሲቀበል በጽድቅ ለሚፈርደው አምላክ ራሱን ዐደራ ሰጠ እንጂ አልዛተም። ከኃጢአት ተለይተን በጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በመስቀል ላይ ተሸከመ፤ በእርሱ ቊስል እናንተ ተፈውሳችኋል። እናንተ እንደ ጠፉ በጎች ትቅበዘበዙ ነበር፤ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።
1 ጴጥሮስ 2:9-25 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን አስደናቂ ሥራ እንድታውጁ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ እግዚአብሔር ለራሱ ያደረጋችሁ ቅዱስ ሕዝብ ናችሁ። ቀድሞ የእርሱ ወገን አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ፤ ቀድሞ ምሕረትን አላገኛችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል። ወዳጆች ሆይ! ባዕዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ ምናልባት “ክፉ አድራጊዎች ናቸው” ብለው ቢያሙአችሁም እንኳ እግዚአብሔር በሚጎበኝበት ቀን፥ ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ እርሱን እንድያከብሩት በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን። ስለ ጌታ ብላችሁ ሥልጣን ለተሰጣቸው ሰዎች ሁሉ፥ ንጉሥም ቢሆን ከሁሉ በላይ እንደመሆኑ ታዘዙ። ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን ከእርሱ ተልከዋልና ለአገረ ገዢዎችም ቢሆን ታዘዙ። በዚህ መንገድ መልካም በማድረግ የሞኞችን አላዋቂነት ዝም እንድታሰኙ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ሆናችሁ በነጻነት ኑሩ እንጂ ነጻነታችሁን የክፋት መሸፈኛ አታድርጉት። ሰውን ሁሉ አክብሩ፤ ወንድሞችን ውደዱ፤ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ንጉሥን አክብሩ። እናንተ አገልጋዮች ሆይ! ለደጎችና ለገሮች ጌቶቻችሁ ብቻ ሳይሆን ለክፉዎችም በፍጹም አክብሮት ታዘዙ። ስለ እግዚአብሔር ብሎ በግፍ መከራን ሲቀበል የሚታገሥ ምስጋና ይገባዋል። ክፉ ሥራ ሠርታችሁ ቅጣት ስትቀበሉ ብትታገሡ ምን ምስጋና ይኖራችኋል? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሡ፥ ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ያስገኝላችኋል። ለዚህ ተጠርታችኋል፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን አርአያነት እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው። እርሱ ኃጢአት አላደረገም፤ በአፉም ተንኰል አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራንም ሲቀበል አልዛተም፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በመስቀል ላይ ተሸከመ፤ በእርሱ ቁስል እናንተ ተፈውሳችኋል። እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበር፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።