1 ነገሥት 6:1-38
1 ነገሥት 6:1-38 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ አራት መቶ ሰማንያ አራት ዓመት በሆነ ጊዜ፥ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ዚፍ በሚባለው በሁለተኛው ወር የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመረ። ንጉሡ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር የሠራው ቤት ርዝመቱ ስድሳ ክንድ፥ ወርዱም ሃያ ክንድ፥ ቁመቱም ሠላሳ ክንድ ነበረ። በመቅደሱም ፊት ወለል ነበረ፤ ርዝመቱም እንደ መቅደሱ ወርድ ሃያ ክንድ፥ ወርዱም ከቤቱ ወደ ፊት ዐሥር ክንድ ነበረ፤ ቤቱንም ሠርቶ ጨረሰ። ለቤቱም በዐይነ ርግብ የተዘጉ መስኮቶችን አደረገ። በቤቱም ግንብ ዙሪያ፥ በመቅደሱና በቅድስተ ቅዱሳኑ ግንብ ዙሪያ ደርብ ሠራ፤ በዙሪያውም ጓዳዎች አደረገ። የታችኛውም ደርብ ወርዱ አምስት ክንድ፥ የመካከለኛውም ደርብ ወርዱ ስድስት ክንድ፥ የሦስተኛውም ደርብ ወርዱ ሰባት ክንድ ነበረ። ሰረገሎቹ በቤቱ ግንብ ውስጥ እንዳይገቡ ከቤቱ ግንብ ውጭ አረፍቶችን አደረገ። ቤቱም በተሠራ ጊዜ ፈጽመው በተወቀሩ ድንጋዮች ተሠራ፤ ሲሠሩትም መራጃና መጥረቢያ፥ የብረትም ዕቃ ሁሉ በቤቱ ውስጥ አልተሰማም። የታችኛውም ደርብ ጓዳዎች በር በቤቱ ቀኝ አጠገብ ነበረ። ከዚያም ወደ መካከለኛው ደርብ፥ ከመካከለኛውም ወደ ሦስተኛው ደርብ የሚወጡበት መውጫ ነበረው። ቤቱንም ሠርቶ ፈጸመው፤ የቤቱንም ጠፈር በዝግባ ሳንቃዎች አደረገ። በቤቱም ዙሪያ ሁሉ ቁመታቸው አምስት አምስት ክንድ የሆኑ ደርቦችን ሠራ፤ ከቤቱም ጋር በዝግባ እንጨት አጋጠማቸው። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ሰሎሞን እንዲህ ሲል መጣ፦ “ስለዚህ ስለምትሠራልኝ ቤት በሥርዐቴ ብትሄድ፥ ፍርዴንም ብታደርግ፥ ትመላለስባቸውም ዘንድ ትእዛዞቼን ሁሉ ብትጠብቅ፥ ለአባትህ ለዳዊት የነገርሁትን ቃል ከአንተ ጋር አጸናለሁ። በእስራኤልም ልጆች መካከል እኖራለሁ፤ ሕዝቤንም እስራኤልን አልጥልም።” ሰሎሞንም ቤቱን ሠራው፤ ፈጸመውም። የቤቱንም ግንብ ውስጡን በዝግባ ሳንቃ ለበጠ፤ ከቤቱም መሠረት ጀምሮ እስከ ጣራው ድረስ የውስጡን ግንብ በእንጨት ለበጠው፤ ደግሞም የቤቱን ወለል በጥድ እንጨት አነጠፈው። ከቤተ መቅደሱ አያይዞ ከመሠረቱ ጀምሮ እስከ ጣራው ድረስ ሃያውን ክንድ በዝግባ ጠርብ ሠራ፤ ከመቅደሱም ከፍሎ ቅድስተ ቅዱሳኑን አደረገ። በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ያለውም መቅደስ ርዝመቱ አርባ ክንድ ነበረ። የቤቱንም ውስጥ በተጐበጐበና በፈነዳ አበባ፥ በተቀረጸ ዝግባ ለበጠው፤ ሁሉም ዝግባ ነበረ፤ ድንጋዩም አልታየም ነበር። በዚያም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ያኖር ዘንድ በቤቱ ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳኑን አበጀ። የቅድስተ ቅዱሳኑም ርዝመት ሃያ ክንድ፥ ስፋቱም ሃያ ክንድ፥ ቁመቱም ሃያ ክንድ ነበረ፤ በጥሩም ወርቅ ለበጠው። በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት ከዝግባ መሠዊያን ሠራ፤ በጥሩ ወርቅም ለበጠው። የሠራው ቤት ሁሉ እስከ ተፈጸመ ድረስ ቤቱን ሁሉ በወርቅ ለበጠው፤ በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት የነበረውን መሠዊያ ሁሉ በወርቅ ለበጠው። በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ ቁመታቸው ዐሥር ክንድ የሆነ ከወይራ እንጨት ሁለት ኪሩቤልን ሠራ። የኪሩብም አንደኛው ክንፍ አምስት ክንድ፥ የኪሩብም ሁለተኛው ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፤ ከአንደኛው ክንፍ ጫፍ ጀምሮ እስከ ሁለተኛው ክንፍ ጫፍ ድረስ ዐሥር ክንድ ነበረ። እንደዚሁም ሁለተኛው ኪሩብ ዐሥር ክንድ ነበረ፤ ሁለቱም ኪሩቤል አንድ ልክና አንድ መልክ ነበሩ። የአንዱ ኪሩብ ቁመት ዐሥር ክንድ ነበረ፤ የሁለተኛውም ኪሩብ እንዲሁ ነበረ። ሁለቱም ኪሩቤል በውስጠኛው ቤት መካከል ነበሩ። የኪሩቤልም ክንፎቻቸው ተዘርግተው ነበር፤ የአንዱም ኪሩብ ክንፍ አንደኛውን ግንብ ይነካ ነበር፤ የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ ሁለተኛውን ግንብ ይነካ ነበር፤ የሁለቱም ክንፎች በቤቱ መካከል እርስ በርሳቸው ይነካኩ ነበር። ኪሩቤልንም በወርቅ ለበጣቸው። በቤቱም ግንብ ሁሉ ዙሪያ በውስጥና በውጭ የኪሩቤልና የዘንባባ ዛፍ፥ የፈነዳም አበባ ሥዕል ቀረጸ። የቤቱንም ወለል በውስጥና በውጭ በወርቅ ለበጠ። ለቅድስተ ቅዱሳኑም መግቢያ ከወይራ እንጨት ሳንቃዎችን ሠራ፤ መድረኩንና መቃኖቹን፥ ደፉንም አምስት ማዕዘን አደረገ። ሁለቱንም ሣንቃዎች ከወይራ እንጨት ሠራ፤ የኪሩቤልንና የዘንባባ ዛፍ፥ የፈነዳም አበባ ሥዕል ቀረጸባቸው፤ በወርቅም ለበጣቸው፤ ኪሩቤልንና የዘንባባውን ዛፍ በወርቅ ለበጠ። እንዲሁም ለመቅደሱ መግቢያ ከወይራ እንጨት አራት ማዕዘን መቃን አደረገ። ሁለቱንም ደጆች ከጥድ እንጨት ሠራ፤ አንዱ ደጅ በማጠፊያ ከተያያዙ ከሁለት ሣንቃዎች ተሠራ፤ ሁለተኛውም ደጅ በማጠፊያ ከተያያዙ ከሁለት ሣንቃዎች ተሠራ። የኪሩቤልንና የዘንባባ ዛፍ፥ የፈነዳም አበባ ሥዕል ቀረጸባቸው፤ በተቀረጸውም ሥራ ላይ በወርቅ ለበጣቸው፤ እስከ መድረካቸውም የተያያዙ ነበሩ። የውስጠኛውንም አደባባይ ቅጥር ሦስቱን ተራ በተጠረበ ድንጋይ፥ አንዱንም ተራ በዝግባ ሣንቃ ሠራው፤ በመቅደሱ ፊት ለፊት ላለው ቤት ወለልም መጋረጃ ሠራ። በአራተኛው ዓመት ከሚያዝያ በሁለተኛው ወር የእግዚአብሔርን ቤት መሠረተ። በዐሥራ አንደኛውም ዓመት ቡል በሚባል በስምንተኛው ወር ቤቱ እንደ ክፍሎቹና እንደ ሥርዐቱ ሁሉ ተጨረሰ። በሰባት ዓመትም ሠራው።
1 ነገሥት 6:1-38 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡ በአራት መቶ ሰማንያ ዓመት፣ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ ዚፍ በተባለው በሁለተኛው ወር ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመረ። ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር የሠራው ቤተ መቅደስ ርዝመቱ ስድሳ ክንድ፣ ወርዱ ሃያ ክንድ፣ ቁመቱ ሠላሳ ክንድ ነበር። በቤተ መቅደሱ አዳራሽ ፊት ለፊት ያለው በረንዳ ወርዱ እንደ ቤተ መቅደሱ ወርድ ሁሉ ሃያ ክንድ ሲሆን፣ ርዝመቱ ዐሥር ክንድ ወደ ውጭ የወጣ ነበር። ለቤተ መቅደሱም ባለዐይነ ርግብ መስኮቶች አበጀ። በዋናው ቤተ መቅደስና በቅድስተ ቅዱሳኑ ግድግዳ ዙሪያ ልዩ ክፍሎች ያሉት ተቀጥላ ግንብ ሠራ። የምድር ቤቱ ወርድ ዐምስት ክንድ፣ የመካከለኛው ፎቅ ስድስት ክንድ፣ የሦስተኛው ፎቅ ሰባት ክንድ ነበር፤ የቤተ መቅደሱን ግድግዳ ዘልቆ እንዳይገባም፣ ከቤተ መቅደሱ ግንብ ውጭ ዙሪያውን እርከኖች አደረገ። ቤተ መቅደሱ የተሠራው እዚያው ድንጋዩ ተቈፍሮ ከወጣበት ቦታ በተዘጋጀ ድንጋይ በመሆኑ የመራጃ፣ የመሮ ወይም የሌላ ብረት ነክ መሣሪያ ድምፅ በቤተ መቅደሱ አካባቢ አልተሰማም ነበር። የምድር ቤቱ መግቢያ በስተ ደቡብ በኩል ባለው የቤተ መቅደሱ ጐን ሲሆን፣ ወደ መካከለኛውና ከዚያም ወደ መጨረሻው ፎቅ የሚያስወጣ ደረጃ ነበረው። ቤተ መቅደሱንም በዚሁ ሁኔታ ሠርቶ ጨረሰ፤ ለጣራው ተሸካሚ አደረገለት፤ በዝግባ ሳንቃም ከደነው። በቤተ መቅደሱም ዙሪያ በሙሉ፣ ቁመታቸው ዐምስት ዐምስት ክንድ የሆነ ክፍሎች ሠራ፤ እነዚህንም ከቤተ መቅደሱ ጋራ በዝግባ አግዳሚ ዕንጨቶች አያያዛቸው። የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሰሎሞን መጣ፤ “ስለምትሠራው ስለዚህ ቤተ መቅደስ ሥርዐቴን ብትከተል፣ ፍርዴን በተግባር ብትገልጸው፣ ትእዛዞቼን ብትጠብቅና ብትመላለስባቸው ለአባትህ ለዳዊት የሰጠሁትን ተስፋ በአንተ እፈጽመዋለሁ፤ በእስራኤላውያን መካከል እኖራለሁ፤ ሕዝቤን እስራኤልንም አልተወውም።” ስለዚህ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ሠርቶ ፈጸመ፤ የውስጡን ግድግዳ ከቤተ መቅደሱ ወለል እስከ ጣራው ድረስ በዝግባ ሳንቃ ለበጠ፤ የቤተ መቅደሱንም ወለል የጥድ ሳንቃ አለበሰው። በቤተ መቅደሱም ውስጥ በስተኋላ በኩል፣ ሃያውን ክንድ ቅድስተ ቅዱሳን እንዲሆን፣ ከወለሉ አንሥቶ እስከ ጣራው ድረስ በዝግባ ሳንቃዎች ጋረደው፤ በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ያለው ዋና አዳራሽ ርዝመቱ አርባ ክንድ ነበር። የቤተ መቅደሱም፣ ውስጡ በሙሉ በዝግባ የተለበጠ ሲሆን፣ ይህም በእንቡጥ አበቦችና በፈኩ አበቦች ቅርጽ የተጌጠ ነበር፤ በሙሉ ዝግባ እንጂ የሚታይ ድንጋይ አልነበረም። በቤተ መቅደሱም ውስጠኛ ክፍል የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት የሚቀመጥበትን ቅድስተ ቅዱሳን ሠራ። ቅድስተ ቅዱሳኑም ርዝመቱ ሃያ ክንድ፣ ወርዱ ሃያ ክንድ፣ ቁመቱም ሃያ ክንድ ነበር፤ ውስጡን በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ ከዝግባ የተሠራውንም መሠዊያ በወርቅ ለበጠው። ሰሎሞንም ቤተ መቅደሱን በውስጥ በኩል በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ በወርቅ በተለበጠው ቅድስተ ቅዱሳን ፊት ለፊትም የወርቅ ሰንሰለቶች ዘረጋ። ስለዚህ ውስጡን በሙሉ በወርቅ ለበጠው፤ በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ያለውን መሠዊያም እንደዚሁ በወርቅ ለበጠው። በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ ቁመታቸው ዐሥር ክንድ የሆነ ሁለት የኪሩቤል ቅርጽ ከወይራ ዕንጨት ሠራ፤ የአንደኛው ኪሩብ አንዱ ክንፍ ዐምስት ክንድ ሲሆን፣ ሌላውም ክንፉ እንደዚሁ ዐምስት ክንድ ነበር፤ ይህም ከአንዱ ክንፍ ጫፍ እስከ ሌላው ክንፍ ጫፍ ዐሥር ክንድ ማለት ነው። የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ እንደዚሁ ዐሥር ክንድ ሆነ፤ ሁለቱ ኪሩቤል በመጠንና በቅርጽ አንድ ዐይነት ነበሩና። የእያንዳንዱም ኪሩብ ቁመት ዐሥር ክንድ ነበር። ክንፎቻቸው እንደ ተዘረጋ፣ ኪሩቤልን ወስዶ በቅድስተ ቅዱሳኑ አኖራቸው፤ የአንዱ ኪሩብ ክንፍ አንዱን ግድግዳ ሲነካ፣ የሌላው ኪሩብ ክንፍ ደግሞ ሌላውን ግድግዳ ይነካ ነበር፤ ሌሎቹ ክንፎቻቸውም በቅድስተ ቅዱሳኑ መካከል እርስ በርሳቸው ይነካኩ ነበር። ኪሩቤልንም በወርቅ ለበጣቸው። በመቅደሱ ግድግዳ ዙሪያ ላይ ሁሉ በውስጥም በውጭም ኪሩቤልን፣ ከዘንባባ ዛፎችና ከፈነዱ አበቦች ጋራ ቀረጸ። እንዲሁም የቅድስተ ቅዱሳኑንና የመቅደሱን ወለል በሙሉ በወርቅ ለበጠ። ለቅድስተ ቅዱሳኑም መግቢያ የወይራ ዕንጨት ደጃፎች ሠራ፤ መቃኖቻቸውንና መድረኮቻቸውን ባለዐምስት ማእዘን አደረገ። በሁለቱ የወይራ ዕንጨት መዝጊያዎችም ላይ ኪሩቤልን፣ የዘንባባ ዛፎችንና የፈነዱ አበቦችን ቀረጸ፤ በወርቅም ለበጣቸው። እንዲሁም ለዋናው አዳራሽ መግቢያ ባለአራት ማእዘን የወይራ ዕንጨት መቃን ሠራ፤ እያንዳንዳቸው በማጠፊያ የተያያዙ ሁለት ሁለት ሳንቃዎች ያሏቸው ሁለት መዝጊያዎች አበጀ። ኪሩቤልን፣ የዘንባባ ዛፎችንና የፈኩ አበቦችንም ቀረጸባቸው፤ ቅርጹን ሠራ፤ ጥሩ አድርጎም በወርቅ ለበጠው። የውስጠኛውን አደባባይ በሦስት ረድፍ ጥርብ ድንጋይና በአንድ ረድፍ የዝግባ ሳንቃ ሠራው። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም በአራተኛው ዓመት ዚፍ በተባለው ወር መሠረቱ ተጣለ፤ በዐሥራ አንደኛው ዓመት ቡል በተባለውም በስምንተኛው ወር ቤተ መቅደሱ በዝርዝር ጥናቱ መሠረት እንደ ታቀደው ተፈጸመ፤ ሠርቶ የጨረሰውም በሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ ነበር።
1 ነገሥት 6:1-38 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር ከወጡ አራት መቶ ሰማንያ ዓመት በሆነ ጊዜ፥ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ዚፍ በሚባለው በሁለተኛው ወር የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመረ። ንጉሡ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር የሠራው ቤት ርዝመቱ ስድሳ ክንድ፥ ወርዱም ሃያ ክንድ፥ ቁመቱም ሠላሳ ክንድ ነበረ። በመቅደሱም ፊት ወለል ነበረ፤ ርዝመቱም እንደ መቅደሱ ወርድ ሃያ ክንድ፥ ወርዱም ከቤቱ ወደፊት ዐሥር ክንድ ነበረ። ለቤቱም በዐይነ ርግብ የተዘጉ መስኮቶች አደረገ። በቤቱም ግንብ ዙሪያ፥ በመቅደሱና በቅድስተ ቅዱሳኑ ግንብ ዙሪያ፥ ደርብ ሠራ፤ በዙሪያውም ጓዳዎች አደረገ። የታችኛውም ደርብ ወርዱ አምስት ክንድ፥ የመካከለኛው ደርብ ወርዱ ስድስት ክንድ፥ የሦስተኛውም ደርብ ወርዱ ሰባት ክንድ ነበረ። ሰረገሎቹ በቤቱ ግንብ ውስጥ እንዳይገቡ ከቤቱ ግንብ ውጭ ዓረፍቶች አደረገ። ቤቱም በተሠራ ጊዜ ፈጽመው በተወቀሩ ድንጋዮች ተሠራ፤ በተሠራም ጊዜ መራጃና መጥረቢያም የብረትም ዕቃ ሁሉ በቤቱ ውስጥ አልተሰማም። የታችኛውም ደርብ ጓዳዎች በር በቤቱ ቀኝ አጠገብ ነበረ። ከዚያም ወደ መካከለኛው ደርብ፥ ከመካከለኛውም ወደ ሦስተኛው ደርብ በመውጫ ያስወጣ ነበር። ቤቱንም ሠርቶ ፈጸመው፤ በዝግባው ሰረገሎችና ሳንቃዎች ከደነው። በቤቱም ሁሉ ዙሪያ ቁመታቸው አምስት አምስት ክንድ የሆነ ደርቦች ሠራ፤ ከቤቱም ጋር በዝግባ እንጨት አጋጠማቸው። የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ሰሎሞን እንዲህ ሲል መጣ “ስለዚህ ስለምትሠራው ቤት በሥርዐቴ ብትሄድ፥ ፍርዴንም ብታደርግ፥ ትመላለስበትም ዘንድ ትእዛዜን ሁሉ ብትጠብቅ፥ ለአባትህ ለዳዊት የነገርሁትን ቃል ከአንተ ጋር አጸናለሁ። በእስራኤልም ልጆች መካከል እኖራለሁ፤ ሕዝቤንም እስራኤልን አልጥልም። ሰሎሞንም ቤቱን ሠራው፤ ፈጸመውም። የቤቱንም ግንብ ውስጡን በዝግባ ሳንቃ ለበጠ፤ ከቤቱም መሠረት ጀምሮ እስከ ጣራው ድረስ ውስጡን በእንጨት ለበጠው፤ ደግሞም የቤቱን ወለል በጥድ እንጨት ከደነው። በቤቱ ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳን ይሆን ዘንድ ኋለኛውን ሃያውን ክንድ በዝግባ እንጨት ጋረደው። በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ያለውም መቅደስ ርዝመቱ አርባ ክንድ ነበረ። የቤቱንም ውስጥ በተጎበጎበና በፈነዳ አበባ በተቀረጸ ዝግባ ለበጠው፤ ሁሉም ዝግባ ነበረ፤ ድንጋዩም አልታየም ነበር። በዚያም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ያኖር ዘንድ በቤቱ ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳኑን አበጀ። የቅድስተ ቅዱሳንም ርዝመት ሃያ ክንድ፥ ስፋቱም ሃያ ክንድ ቁመቱም ሀያ ክንድ ነበረ፤ በጥሩ ወርቅም ለበጠው። በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት ከዝግባ የተሠራ መሠዊያ አደረገ፤ በጥሩ ወርቅም ለበጠው። ቤቱንም ሁሉ ፈጽሞ በወርቅ ለበጠው፤ በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት የነበረውን መሠዊያ ሁሉ በወርቅ ለበጠው። በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ ቁመታቸው ዐሥር ክንድ የሆነ ከወይራ እንጨት ሁለት ኪሩቤል ሠራ። የኪሩብም አንደኛው ክንፍ አምስት ክንድ፥ የኪሩብም ሁለተኛው ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፤ ከአንደኛው ክንፍ ጫፍ ጀምሮ እስክ ሁለተኛው ክንፍ ጫፍ ድረስ ዐሥር ክንድ ነበረ። ሁለተኛውም ኪሩብ ዐሥር ክንድ ነበረ፤ ሁለቱም ኪሩቤል አንድ ልክና አንድ መልክ ነበረ። የአንዱ ኪሩብ ቁመት ዐሥር ክንድ ነበረ፤ የሁለተኛውም ኪሩብ እንዲሁ ነበረ። ኪሩቤልንም በውስጠኛው ቤት አኖራቸው፤ የኪሩቤልም ክንፎቻቸው ተዘርግተው ነበር፤ የአንዱም ኪሩብ ክንፍ አንደኛውን ግንብ ይነካ ነበር፤ የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ ሁለተኛውን ግንብ ይነካ ነበር፤ የሁለቱም ክንፎች በቤቱ መካከል እርስ በርሳቸው ይነካኩ ነበር። ኪሩቤልንም በወርቅ ለበጣቸው። በቤቱም ግንብ ሁሉ ዙሪያ በውስጥና በውጭ የኪሩቤልና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳ አበባ ምስል ቀረጸ። የቤቱንም ወለል በውስጥና በውጭ በወርቅ ለበጠ። ለቅዱስተ ቅዱሳኑም መግቢያ ከወይራ እንጨት ደጆች ሠራ፤ መድረኩንና መቃኖቹን ደፉንም አምስት ማዕዘን አደረገ። ሁለቱንም ደጆች ከወይራ እንጨት ሠራ፤ የኪሩቤልንና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸባቸው፤ በወርቅም ለበጣቸው፤ ኪሩቤልንና የዘንባባውን ዛፍ በወርቅ ለበጣቸው። እንዲሁም ለመቅደሱ መግቢያ ከወይራ እንጨት አራት ማዕዘን መቃን አደረገ። ሁለቱንም ደጆች ከጥድ እንጨት ሠራ፤ አንዱ ደጅ በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ፤ ሁለተኛውም ደጅ በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ። የኪሩቤልንና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸባቸው፤ በተቀረጸውም ሥራ ላይ በወርቅ ለበጣቸው። የውስጠኛውንም አደባባይ ቅጥር ሦስቱን ተራ በተጠረበ ድንጋይ፥ አንዱንም ተራ በዝግባ ሳንቃ ሠራው። በአራተኛው ዓመት ዚፍ በሚባል ወር የእግዚአብሔር ቤት ተመሠረተ። በዐሥራ አንደኛውም ዓመት ቡል በሚባል በስምንተኛው ወር ቤቱ እንደ ክፍሎቹና እንደ ሥርዐቱ ሁሉ ተጨረሰ። በሰባትም ዓመት ውስጥ ሠራው።
1 ነገሥት 6:1-38 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር ከወጡ ከአራት መቶ ሰማኒያ ዓመት በኋላ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ዚፍ ተብሎ በሚጠራው በሁለተኛው ወር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመረ፤ ቤተ መቅደሱ በውስጥ በኩል ርዝመቱ ኻያ ሰባት ሜትር፥ ወርዱ ዘጠኝ ሜትር፥ ቁመቱ ዐሥራ ሦስት ሜትር ተኩል ነበር፤ በመግቢያው በር የሚገኘው በረንዳ ቁመቱ አራት ሜትር ተኩል፥ ወርዱ ልክ እንደ ቤተ መቅደሱ ዘጠኝ ሜትር ነበር። ለቤተ መቅደሱም ሕንጻ ከውስጥ ሰፋ፥ ከውጪ ጠበብ ያሉ መስኮቶች ነበሩት፤ የቤተ መቅደሱን ሕንጻ አስጠግቶ በቅድስቱና በቅድስተ ቅዱሳኑ ዙሪያ ደርብ ሠራ፤ በዙሪያውም ክፍሎችን አደረገ። የታችኛው ፎቅ ክፍል ወርዱ ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር፥ የሁለተኛው ፎቅ ክፍል ወርድ ሁለት ሜትር ከሰባ ሳንቲ ሜትር፥ የመጨረሻው ፎቅ ክፍል ወርድ ሦስት ሜትር ከዐሥር ሳንቲ ሜትር ነበር፤ የእያንዳንዱ ወለል ግንብ ከታች በኩል ካለው የወለል ግንብ የሳሳ ነበር፤ ሠረገሎቹ ወደ ቤተ መቅደሱ ግድግዳ እንዳይገቡ ለማድረግ ከቤተ መቅደሱ ግድግዳ ውጪ ዐረፍቶችን አደረገ። ቤተ መቅደሱ የታነጸባቸው ድንጋዮች ተጠርበው የተዘጋጁት፤ በዚያው በተፈለጡበት ቦታ ነበር፤ ስለዚህም ቤተ መቅደሱ በሚሠራበት ጊዜ የመዶሻ፥ የመጥረቢያ ወይም የሌላ ብረት ነክ መሣሪያ ድምፅ አይሰማም ነበር። ተጨማሪ ሆኖ የተሠራው ሕንጻ የታችኛው ፎቅ መግቢያ በር የሚገኘው ከቤተ መቅደሱ በስተደቡብ በኩል ነበር፤ እርሱም ከሁለተኛውና ከሦስተኛው ፎቅ ጋር የሚያገናኙት ደረጃዎች ነበሩት። በዚህ አኳኋን ሰሎሞን የቤተ መቅደሱን ሕንጻ ሥራ ፈጸመ፤ ጣራውንም ከውስጥ በኩል ከሊባኖሱ ዛፍ እንጨት በተሠራ አግዳሚ ሠረገላና ጠርብ ለበደው። የእያንዳንዱ ፎቅ ቁመት ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ሆኖ ከውጪ በኩል ወደ ቤተ መቅደሱ ተጠግቶ የተሠራው ባለ ሦስት ፎቅ ተጨማሪ ሕንጻ ከዋናው ሕንጻዎች ከሊባኖስ ዛፍ በተሠሩት አግዳሚ ሠረገሎች የተያያዘ ነበር። እግዚአብሔር ሰሎሞንን እንዲህ አለው፦ “ሕጎቼን፥ ትእዛዞቼንና ሥርዓቴን ሁሉ ብትጠብቅ፥ ለአባትህ ለዳዊት የሰጠሁትን የተስፋ ቃል ለአንተ አጸናለሁ፤ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ሆኜ አንተ በምትሠራው በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ እኖራለሁ። ከቶም አልለያቸውም።” በዚህ ዐይነት ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ሠርቶ ፈጸመ። የቤተ መቅደሱ ግንብ ከውስጥ በኩል ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርበው በተሠሩ ሳንቃዎች ተለበደ፤ የወለሉም ጣውላ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት የተሠራ ነበር። ቅድስተ ቅዱሳን ተብሎ የሚጠራ አንድ ውስጣዊ ክፍል ከቤተ መቅደሱ በስተ ኋላ ገባ ብሎ ተሠራ፤ የእርሱም ርዝመት ዘጠኝ ሜትር ሲሆን ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርቦ በተሠራ ሳንቃ የተከፈለ ነበር፤ ከቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት የሚገኘውም የተቀደሰ ክፍል ርዝመት ዐሥራ ስምንት ሜትር ነበር፤ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ሳንቃዎች በአበባ እንቡጦችና በፈኩ አበባዎች ቅርጽ አጊጠው ነበር፤ ውስጡም ሁሉ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርቦ በተሠራ ሳንቃ ስለ ተለበደ የግንቡ ድንጋዮች አይታዩም ነበር። ከቤተ መቅደሱ ውስጥ በስተ ኋላ በኩል የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት የሚቀመጥበት ውስጣዊ ክፍል ተሠራ። ይህም ውስጣዊ ክፍል ርዝመቱ ዘጠኝ ሜትር፥ ወርዱ ዘጠኝ ሜትር፥ ቁመቱ ዘጠኝ ሜትር፥ ሲሆን በሙሉ በንጹሕ ወርቅ የተለበጠ ነበር፤ መሠዊያውም ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርቦ በተሠራ ሳንቃ የተለበደ ነበር። ሰሎሞንም ቤተ መቅደሱን በውስጥ በኩል በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ እርሱም በወርቅ በተለበጠው ውስጠኛ ክፍል መግቢያ በር ክፈፉንም በተሸጋገሩ የወርቅ ሰንሰለቶች አስጌጠው። በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ የሚገኘውን መሠዊያ ጭምር መላውን ቤተ መቅደስ ከውስጥ በኩል በወርቅ ለበጠው። የእያንዳንዳቸው ቁመት አራት ሜትር ከአርባ ሳንቲ ሜትር የሆነ፥ ከወይራ እንጨት በሁለት ኪሩቤል አምሳል የተቀረጹ ሥዕሎች በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ሠራ። የሁለቱም ኪሩቤል ቅርጽና መጠን ተመሳሳይ ነበር፤ እያንዳንዱም ኪሩቤል ሁለት ክንፎች ነበሩት፤ የእያንዳንዱ ክንፍ ርዝመት ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ሲሆን፥ ከአንዱ ክንፍ ጫፍ እስከ ሌላው ክንፍ ጫፍ ድረስ ያለው ርዝመት አራት ሜትር ከአርባ ሳንቲ ሜትር ነበር፤ የየአንዳንዱ ኪሩብ ቁመት አራት ሜትር ከአርባ ሳንቲ ሜትር ነበር። ኪሩቤልንም በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ እንዲቆሙ አደረገ፤ ስለዚህም የተዘረጉ ሁለቱ ክንፎቻቸው በክፍሉ መካከለኛ ቦታ ላይ ተገናኝተው ሌሎቹ ሁለቱ ክንፎቻቸው ደግሞ በተዘረጉበት አቅጣጫ ግንቦቹን ይነኩ ነበር። ሁለቱንም ኪሩቤል በወርቅ ለበጣቸው። የዋናውን ክፍልና የውስጠኛውን ክፍል ግንቦች በሙሉ በኪሩቤል፥ በዘንባባ ዛፎችና በፈኩ የአበባ ቅርጾች አስጌጣቸው፤ እርሱም ከውስጥና ከውጪ በኩል ያሉትን ክፍሎች ወለል እንኳ በወርቅ ለበጣቸው። ከወይራ እንጨት የተሠራ ሁለት ተከፋች በር በቅድስተ ቅዱሳኑ መግቢያ እንዲቆም አደረገ፤ በሩም አምስት ማእዘን ያለው ሆኖ አናቱ ላይ ቀጥ ብሎ የተሠራ ቅስት ነበር። ሁለቱን በሮች በኪሩቤል፥ በዘንባባ ዛፎችና በፈኩ የአበባ ቅርጾች አስጌጣቸው፤ እርሱም በሮቹን፥ ኪሩቤልን፥ የዘንባባ ዛፎቹን፥ ቅርጾቹንም በወርቅ ለበጣቸው። እንዲሁም ወደ ዋናው ክፍል ለሚያደርሰው መግቢያ በር ከወይራ እንጨት የተሠራ ባለ አራት ማእዘን ክፈፍ አበጀለት። ሁለቱንም በሮች ከዝግባ እንጨት ሠራ፤ አንዱ በር በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ፤ ሁለተኛውም በር በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ። እነርሱንም ሙሉ በሙሉ በወርቅ በተለበጡ በኪሩቤል፥ በዘንባባ ዛፎችና በፈኩ የአበባ ቅርጾች አስጌጣቸው። በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት አንድ የውስጥ አደባባይ ሠራ፤ በዚህም አደባባይ ዙሪያ በየሦስቱ ዙር የድንጋይ ረድፍ አንድ የሊባኖስ ዛፍ ሠረገላ ሳንቃ የተጋደመበት ግንብ አደረገ። ይህም ቤተ መቅደስ መሠረቱ የተጣለው ሰሎሞን በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ዚፍ ተብሎ በሚጠራው በሁለተኛው ወር ነበር። ሰሎሞን በነገሠ በዐሥራ አንደኛ ዓመቱ፥ ቡል ተብሎ በሚጠራው በስምንተኛው ወር ላይ የቤተ መቅደሱ ሥራ ልክ በታቀደው መሠረት ሙሉ በሙሉ ተጠናቀቀ፤ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የፈጀበት ጊዜ ሰባት ዓመት ነበር።
1 ነገሥት 6:1-38 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ ምድር ከወጡ ከአራት መቶ ሰማኒያ ዓመት በኋላ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ዚፍ ተብሎ በሚጠራው በሁለተኛው ወር የጌታን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመረ። ለጌታ የሠራው ቤተ መቅደስ ርዝመቱ ኻያ ሰባት ሜትር፥ ወርዱ ዘጠኝ ሜትር፥ ቁመቱ ዐሥራ ሦስት ሜትር ተኩል ነበር። በመግቢያው በር የሚገኘው በረንዳ ቁመቱ አራት ሜትር ተኩል፥ ወርዱ ልክ እንደ ቤተ መቅደሱ ዘጠኝ ሜትር ነበር። ለቤተ መቅደሱም ሕንጻ ከውስጥ ሰፋ፥ ከውጪ ጠበብ ያሉ መስኮቶች ነበሩት። የቤተ መቅደሱን ሕንጻ አስጠግቶ በቅድስቱና በቅድስተ ቅዱሳኑ ዙሪያ ደርብ ሠራ፤ በዙሪያውም ክፍሎችን አደረገ። የታችኛው ፎቅ ክፍል ወርዱ ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር፥ የሁለተኛው ፎቅ ክፍል ወርዱ ሁለት ሜትር ከሰባ ሳንቲ ሜትር፥ የመጨረሻው ፎቅ ክፍል ወርዱ ሦስት ሜትር ከዐሥር ሳንቲ ሜትር ነበር፤ የእያንዳንዱም ወለል ግንብ ከታች በኩል ካለው የወለል ግንብ የሳሳ ነበር፤ ሠረገሎቹ ወደ ቤተ መቅደሱ ግድግዳ እንዳይገቡ ለማድረግ ከቤተ መቅደሱ ግድግዳ ውጪ ዐረፍቶችን አደረገ። ቤተ መቅደሱ የታነጸባቸው ድንጋዮች ተጠርበው የተዘጋጁት፤ በዚያው በተፈለጡበት ቦታ ነበር፤ ስለዚህም ቤተ መቅደሱ በሚሠራበት ጊዜ የመዶሻ፥ የመጥረቢያ ወይም የሌላ ብረት ነክ መሣሪያ ድምፅ አይሰማም ነበር። ተጨማሪ ሆኖ የተሠራው ሕንጻ የታችኛው ፎቅ መግቢያ በር የሚገኘው ከቤተ መቅደሱ በስተ ደቡብ በኩል ነበር፤ እርሱም ከሁለተኛውና ከሦስተኛው ፎቅ ጋር የሚያገናኙት ደረጃዎች ነበሩት። በዚህ አኳኋን ሰሎሞን የቤተ መቅደሱን ሕንጻ ሥራ ፈጸመ፤ ጣራውንም ከውስጥ በኩል ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት በተሠራ አግዳሚ ሠረገላና ጠርብ ለበደው። የእያንዳንዱ ፎቅ ቁመት ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ሆኖ ከውጪ በኩል ወደ ቤተ መቅደሱ ተጠግቶ የተሠራው ባለ ሦስት ፎቅ ተጨማሪ ሕንጻ ከዋናው ሕንጻዎች ከሊባኖስ ዛፍ በተሠሩት አግዳሚ ሠረገሎች የተያያዘ ነበር። የጌታ ቃል ወደ ሰሎሞንን እንዲህ ሲል መጣ፦ “ስለዚህ ስለምትሠራው ቤት ሕጎቼን፥ ትእዛዞቼንና ሥርዓቴን ሁሉ ብትጠብቅ፥ ለአባትህ ለዳዊት የሰጠሁትን የተስፋ ቃል ለአንተ አጸናለሁ። በእስራኤል ልጆች መካከል አድራለሁ፤ ሕዝቤን እስራኤልንም ከቶ አልለያቸውም።” በዚህ ዓይነት ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ሠርቶ ፈጸመ። የቤተ መቅደሱ ግንብ ከውስጥ በኩል ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርበው በተሠሩ ሳንቃዎች ተለበደ፤ የወለሉም ጣውላ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት የተሠራ ነበር። ቅድስተ ቅዱሳን ተብሎ የሚጠራ አንድ ውስጣዊ ክፍል ከቤተ መቅደሱ በስተ ኋላ ገባ ብሎ ተሠራ፤ የእርሱም ርዝመት ዘጠኝ ሜትር ሲሆን ከወለሉ እስከ ጣራው ድረስ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርቦ በተሠራ ሳንቃ የተከፈለ ነበር። ከቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት የሚገኘውም የተቀደሰ ክፍል ርዝመቱ ዐሥራ ስምንት ሜትር ነበር። የሊባኖስ ዛፍ እንጨት ሳንቃዎች በአበባ እንቡጦችና በፈኩ አበባዎች ቅርጽ አጊጠው ነበር፤ ውስጡም ሁሉ ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርቦ በተሠራ ሳንቃ ስለ ተለበደ የግንቡ ድንጋዮች አይታዩም ነበር። ከቤተ መቅደሱ ውስጥ በስተ ኋላ በኩል የጌታ የቃል ኪዳን ታቦት የሚቀመጥበት ውስጣዊ ክፍል ተሠራ። ይህም ውስጣዊ ክፍል ርዝመቱ ዘጠኝ ሜትር፥ ወርዱ ዘጠኝ ሜትር፥ ቁመቱ ዘጠኝ ሜትር፥ ሲሆን በሙሉ በንጹሕ ወርቅ የተለበጠ ነበር፤ መሠዊያውም ከሊባኖስ ዛፍ እንጨት ተጠርቦ በተሠራ ሳንቃ የተለበደ ነበር። ሰሎሞንም ቤተ መቅደሱን በውስጥ በኩል በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ እርሱም በወርቅ በተለበጠው ውስጠኛ ክፍል መግቢያ በር ክፈፉንም በተሸጋገሩ የወርቅ ሰንሰለቶች አስጌጠው። በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ የሚገኘውን መሠዊያ ጭምር መላውን ቤተ መቅደስ ከውስጥ በኩል በወርቅ ለበጠው። የእያንዳንዳቸው ቁመት አራት ሜትር ከአርባ ሳንቲ ሜትር የሆነ፥ ከወይራ እንጨት በሁለት ኪሩቤል አምሳል የተቀረጹ ሥዕሎች በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ሠራ። የአንደኛው ኪሩብ አንዱ ክንፍ አምስት ክንድ ሲሆን፥ ሌላውም ክንፉ እንደዚሁ አምስት ክንድ ነበር፤ ይህም ከአንዱ ክንፍ ጫፍ እስከ ሌላው ክንፍ ጫፍ ዐሥር ክንድ ማለት ነው። የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ እንደዚሁ ዐሥር ክንድ ሆነ፥ ሁለቱ ኪሩቤል በመጠንና በቅርጽ አንድ ዓይነት ነበሩና። የየአንዳንዱ ኪሩብ ቁመት አራት ሜትር ከአርባ ሳንቲ ሜትር ነበር። ኪሩቤልንም በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ እንዲቆሙ አደረገ፤ ስለዚህም የተዘረጉ ሁለቱ ክንፎቻቸው በክፍሉ መካከለኛ ቦታ ላይ ተገናኝተው ሌሎቹ ሁለቱ ክንፎቻቸው ደግሞ በተዘረጉበት አቅጣጫ ግንቦቹን ይነኩ ነበር። ሁለቱንም ኪሩቤል በወርቅ ለበጣቸው። የዋናውን ክፍልና የውስጠኛውን ክፍል ግንቦች በሙሉ በኪሩቤል፥ በዘንባባ ዛፎችና በፈኩ የአበባ ቅርጾች አስጌጣቸው። እርሱም ከውስጥና ከውጪ በኩል ያሉትን ክፍሎች ወለል እንኳ በወርቅ ለበጣቸው። ከወይራ እንጨት የተሠራ ሁለት ተከፋች በር በቅድስተ ቅዱሳኑ መግቢያ እንዲቆም አደረገ፤ በሩም አምስት ማእዘን ያለው ሆኖ አናቱ ላይ ቀጥ ብሎ የተሠራ ቅስት ነበር። ሁለቱን በሮች በኪሩቤል፥ በዘንባባ ዛፎችና በፈኩ የአበባ ቅርጾች አስጌጣቸው፤ እርሱም በሮቹን፥ ኪሩቤልን፥ የዘንባባ ዛፎቹን፥ ቅርጾቹንም በወርቅ ለበጣቸው። እንዲሁም ወደ ዋናው ክፍል ለሚያደርሰው መግቢያ በር ከወይራ እንጨት የተሠራ ባለ አራት ማእዘን ክፈፍ አበጀለት። ሁለቱንም በሮች ከዝግባ እንጨት ሠራ፤ አንዱ በር በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ፤ ሁለተኛውም በር በማጠፊያ ከተያያዘ ከሁለት ሳንቃ ተደረገ። እነርሱንም ሙሉ በሙሉ በወርቅ በተለበጡ በኪሩቤል፥ በዘንባባ ዛፎችና በፈኩ የአበባ ቅርጾች አስጌጣቸው። በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት አንድ የውስጥ አደባባይ ሠራ፤ በዚህም አደባባይ ዙሪያ በየሦስቱ ዙር የድንጋይ ረድፍ አንድ የሊባኖስ ዛፍ ሠረገላ ሳንቃ የተጋደመበት ግንብ አደረገ። የጌታ ቤት መሠረት የተጣለው በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ዚፍ ተብሎ በሚጠራው ወር ነበር። ሰሎሞን በነገሠ በዐሥራ አንደኛ ዓመቱ፥ ቡል ተብሎ በሚጠራው በስምንተኛው ወር ላይ የቤተ መቅደሱ ሥራ ልክ በታቀደው መሠረት ሙሉ በሙሉ ተጠናቀቀ፤ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የፈጀበት ጊዜ ሰባት ዓመት ነበር።