1 ነገሥት 18:30-39

1 ነገሥት 18:30-39 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ኤል​ያ​ስም ሕዝ​ቡን ሁሉ፥ “ወደ እኔ ቅረቡ” አላ​ቸው። ሕዝ​ቡም ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ። ኤል​ያ​ስም፦ ስምህ እስ​ራ​ኤል ይሆ​ናል የሚል የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቃል እንደ ደረ​ሰ​ለት እንደ እስ​ራ​ኤል ልጆች ነገድ ቍጥር ዐሥራ ሁለት ድን​ጋ​ዮ​ችን ወሰደ። ድን​ጋ​ዮ​ች​ንም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ስም መሠ​ዊያ አድ​ርጎ ሠራ​ቸው፤ የፈ​ረ​ሰ​ው​ንም መሠ​ዊያ አደሰ፤ በመ​ሠ​ዊ​ያ​ውም ዙሪያ ሁለት መስ​ፈ​ሪያ እህል የሚ​ይዝ ጕድ​ጓድ ቈፈረ። በሠ​ራ​ውም መሠ​ዊያ ላይ እን​ጨ​ቱን ደረ​ደረ፤ ወይ​ፈ​ኑ​ንም በብ​ልት በብ​ልቱ ቈረጠ፤ በእ​ን​ጨ​ቱም ላይ አኖረ፤ “አራት ጋን ውኃ አም​ጡ​ልኝ፤ በሚ​ቃ​ጠ​ለው መሥ​ዋ​ዕ​ትና በእ​ን​ጨቱ ላይም አፍ​ስሱ” አለ፤ እነ​ር​ሱም እን​ዲሁ አደ​ረጉ። ደግ​ሞም፥ “ድገሙ” አለ፤ እነ​ር​ሱም ደገሙ። እር​ሱም፥ “ሦስ​ተኛ አድ​ርጉ” አለ፤ ሦስ​ተ​ኛም አደ​ረጉ። ውኃ​ውም በመ​ሠ​ዊ​ያው ዙሪያ ፈሰሰ። ደግ​ሞም ጕድ​ጓ​ዱን በውኃ ሞላው። ነቢዩ ኤል​ያ​ስም ወደ ሰማይ አቅ​ንቶ ጮኸ፤ እን​ዲ​ህም አለ፥ “አቤቱ፥ የአ​ብ​ር​ሃ​ምና የይ​ስ​ሐቅ የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም አም​ላክ ሆይ፥ ስማኝ፤ ጌታዬ ሆይ፥ ዛሬ በእ​ሳት ስማኝ፤ አንተ በእ​ስ​ራ​ኤል ላይ አም​ላክ እንደ ሆንህ፥ እኔም ባሪ​ያህ እንደ ሆንሁ፤ ይህ​ንም ሥራ ስለ አንተ እን​ዳ​ደ​ረ​ግሁ እነ​ዚህ ሕዝ​ቦች ይወቁ። አንተ፥ አቤቱ፥ አም​ላክ እንደ ሆንህ፥ ልባ​ቸ​ው​ንም ደግሞ እንደ መለ​ስህ፤ ይህ ሕዝብ ያውቅ ዘንድ ስማኝ፤ አቤቱ፥ ስማኝ” አለ። እሳ​ትም ከሰ​ማይ ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ወረ​ደች፤ የሚ​ቃ​ጠ​ለ​ውን መሥ​ዋ​ዕት፥ እን​ጨ​ቱ​ንም፥ ድን​ጋ​ዮ​ቹ​ንም በላች፤ በጕ​ድ​ጓ​ዱም ውስጥ ያለ​ውን ውኃ፥ አፈ​ሩ​ንም ላሰች። ሕዝ​ቡም ሁሉ ያን ባዩ ጊዜ በግ​ን​ባ​ራ​ቸው ተደ​ፍ​ተው፥ “እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በእ​ው​ነት እርሱ አም​ላክ ነው፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እርሱ አም​ላክ ነው” አሉ።

1 ነገሥት 18:30-39 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚያም ኤልያስ ሕዝቡን በሙሉ፣ “ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እርሱም ፈርሶ የነበረውን የእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ። ከዚያም ኤልያስ፣ “ስምህ እስራኤል ይባላል” ተብሎ የእግዚአብሔር ቃል በመጣለት በያዕቆብ ልጆች ነገድ ቍጥር ልክ ዐሥራ ሁለት ድንጋይ ወስዶ፤ በድንጋዮቹም ለእግዚአብሔር ስም መሠዊያ ሠራ፤ በመሠዊያውም ዙሪያ ዐሥራ ዐምስት ሊትር ውሃ የሚይዝ ጕድጓድ ቈፈረ፤ ዕንጨቱን ረበረበ፤ የወይፈኑንም ሥጋ በየብልቱ ከቈረጠ በኋላ፣ በዕንጨቱ ላይ አኖረው። ከዚያም፣ “ውሃ በአራት ጋን ሞልታችሁ፣ በመሥዋዕቱና በዕንጨቱ ላይ አፍስሱ” አላቸው። ደግሞም፣ “እንደ ገና ጨምሩበት” አላቸው፤ እነርሱም ጨመሩበት። “ሦስተኛም ጨምሩበት” ሲል አዘዛቸው፤ እነርሱም ለሦስተኛ ጊዜ ጨመሩበት። ውሃውም በመሠዊያው ዙሪያ ፈሰሰ፤ ጕድጓዱንም ሞላው። የሠርክ መሥዋዕት በሚቀርብበትም ጊዜ፣ ኤልያስ ወደ መሠዊያው ቀረብ ብሎ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የአብርሃም፣ የይሥሐቅና የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የእስራኤል አምላክ መሆንህ፣ እኔም የአንተ አገልጋይ መሆኔና ይህን ሁሉ በትእዛዝህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይታወቅ። ይህ ሕዝብ፣ አንተ አምላክ እግዚአብሔር እውነተኛ መሆንህንና ልባቸውን የመለስኸው አንተ መሆንህን ያውቁ ዘንድ እባክህ ስማኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህ መልስልኝ።” ከዚያም የእግዚአብሔር እሳት ወርዳ መሥዋዕቱን፣ ዕንጨቱን፣ ድንጋዩንና ዐፈሩን ፈጽማ በላች፤ በጕድጓዱ ውስጥ ያለውንም ውሃ ላሰች። ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲያዩ፣ በግንባራቸው ተደፍተው፣ “አምላክ እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ ነው! እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው!” አሉ።

1 ነገሥት 18:30-39 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኤልያስም ሕዝቡን ሁሉ “ወደ እኔ ቅረቡ፤” አላቸው። ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ። ፈርሶ የነበረውንም የእግዚአብሔርን መሠዊያ አበጀ። ኤልያስም “ስምህ እስራኤል ይሆናል፤” የሚል የእግዚአብሔር ቃል እንደ ደረሰለት እንደ ያዕቆብ ልጆች ነገድ ቁጥር ዐሥራ ሁለቱን ድንጋዮች ወሰደ። ከድንጋዮችም ለእግዚአብሔር ስም መሠዊያ ሠራ፤ በመሠዊያውም ዙሪያ ሁለት መስፈሪያ እህል የሚይዝ ጕድጓድ ቆፈረ። እንጨቱንም በተርታ አደረገ፤ ወይፈኑንም በብልት በብልቱ ቆረጠ፤ በእንጨቱም ላይ አኖረና “አራት ጋን ውሃ ሙሉ በሚቃጠለው መሥዋዕትና በእንጨቱ ላይ አፍስሱ፤” አለ። ደግሞም “ድገሙ” አለ፤ እነርሱም ደገሙ። እርሱም “ሦስተኛ አድርጉ፤” አለ፤ ሦስተኛም አደረጉ። ውሃውም በመሠዊያው ዙሪያ ፈሰሰ፤ ደግሞም ጕድጓዱን ውሃ ሞላው። የሠርክ መሥዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ ነቢዩ ኤልያስ ቀርቦ “አቤቱ፥ የአብርሃምና የይስሐቅ የእስራኤልም አምላክ ሆይ! አንተ በእስራኤል ላይ አምላክ እንደ ሆንህ፥ እኔም ባሪያህ እንደ ሆንሁ፥ ይህንም ሁሉ በቃልህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይገለጥ። አቤቱ፥ አንተ አምላክ እንደ ሆንህ፥ ልባቸውንም ደግሞ እንደ መለስህ ይህ ሕዝብ ያውቅ ዘንድ ስማኝ፤ አቤቱ፥ ስማኝ፤” አለ። የእግዚአብሔርም እሳት ወደቀች፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕቱንም፥ እንጨቱንም፥ ድንጋዮቹንም፥ አፈሩንም በላች፤ በጕድጓዱም ውስጥ ያለውን ውሃ ላሰች። ሕዝቡም ሁሉ ያንን ባዩ ጊዜ በግምባራቸው ተደፍተው “እግዚአብሔር እርሱ አምላክ ነው! እግዚአብሔር እርሱ አምላክ ነው!” አሉ።

1 ነገሥት 18:30-39 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ ኤልያስ ሰዎቹን “ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው፤ ሁሉም በዙሪያው ተሰበሰቡ፤ እርሱም ፈርሶ የነበረውን የእግዚአብሔር መሠዊያ በማደስ ሠራው። እግዚአብሔር ከዚያ በፊት “እስራኤል” ብሎ ከሰየመው ከያዕቆብ በተወለዱት በዐሥራ ሁለቱ ነገዶች ስም ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች ወሰደ፤ እነዚህንም ድንጋዮች ረብርቦ በእግዚአብሔር ስም መሠዊያ ሠራ፤ በዙሪያውም ዐሥራ አራት ሊትር ውሃ የሚይዝ ጒድጓድ ማሰ፤ እንጨቱንም በመሠዊያው ላይ በመረብረብ ኰርማውን በብልት በብልቱ ቈራርጦ በእንጨቱ ላይ ካኖረ በኋላ፥ “በአራት ጋን ውሃ ሞልታችሁ በመሥዋዕቱና በእንጨቱ ላይ አፍስሱት!” አላቸው፤ እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፤ “አሁንም ጨምሩበት!” አላቸው፤ እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፤ እርሱም “አሁንም እንደገና አንድ ጊዜ ጨምሩ!” አላቸው፤ እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፤ ውሃውም በመሠዊያው ዙሪያ ፈሰሰ፤ ጒድጓዱንም ሞላው። ከቀትር በኋላ የሠርክ መሥዋዕት በሚቀርብበት ሰዓት ነቢዩ ኤልያስ ወደ መሠዊያው ቀርቦ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የአብርሃም፥ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! አንተ የእስራኤል አምላክ መሆንክን፥ እኔም የአንተ አገልጋይ መሆኔን፥ እኔም ይህን ሁሉ ያደረግኹት በቃልህ መሠረት መሆኑን አንተ ራስህ ግለጥ፤ አምላኬ ሆይ! ይህ ሕዝብ አንተ እውነተኛ አምላክ መሆንህንና ወደ አንተም ያቀረብከው አንተ ራስህ መሆንህን እንዲያውቅ እባክህ መልስ ስጠኝ፤ አምላክ ሆይ፥ ስማኝ!” ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እሳትን ላከ፤ ያም እሳት መሥዋዕቱን፥ እንጨቱንና ድንጋዩን አቃጠለ፤ ምድሩንም ለበለበ፤ በጒድጓዱ የነበረውንም ውሃ አደረቀ፤ ሰዎቹም ይህን ባዩ ጊዜ በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፍተው በመደነቅ “እግዚአብሔር አምላክ ነው! እውነተኛ አምላክ እርሱ ብቻ ነው!” አሉ።

1 ነገሥት 18:30-39 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከዚህ በኋላ ኤልያስ ሰዎቹን “ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው፤ ሁሉም በዙሪያው ተሰበሰቡ፤ እርሱም ፈርሶ የነበረውን የጌታ መሠዊያ በማደስ ሠራው። ጌታ ከዚያ በፊት “እስራኤል” ብሎ ከሰየመው ከያዕቆብ በተወለዱት በዐሥራ ሁለቱ ነገዶች ስም ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች ወሰደ። እነዚህንም ድንጋዮች ረብርቦ በጌታ ስም መሠዊያ ሠራ፤ በዙሪያውም ዐሥራ አራት ሊትር ውሃ የሚይዝ ጉድጓድ ማሰ። እንጨቱንም በመሠዊያው ላይ በመረብረብ ኰርማውን በብልት በብልቱ ቆራርጦ በእንጨቱ ላይ ካኖረ በኋላ፥ “በአራት ጋን ውሃ ሞልታችሁ በመሥዋዕቱና በእንጨቱ ላይ አፍስሱት!” አላቸው፤ እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፤ “አሁንም ጨምሩበት!” አላቸው፤ እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፤ እርሱም “አሁንም እንደገና አንድ ጊዜ ጨምሩ!” አላቸው፤ እነርሱም እንዲሁ አደረጉ። ውሃውም በመሠዊያው ዙሪያ ፈሰሰ፤ ጉድጓዱንም ሞላው። ከቀትር በኋላ የሠርክ መሥዋዕት በሚቀርብበት ሰዓት ነቢዩ ኤልያስ ወደ መሠዊያው ቀርቦ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የአብርሃም፥ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ጌታ ሆይ! አንተ የእስራኤል አምላክ መሆንክን፥ እኔም የአንተ አገልጋይ መሆኔን፥ እኔም ይህን ሁሉ ያደረግኹት በቃልህ መሠረት መሆኑን አንተ ራስህ ግለጥ፤ አምላኬ ሆይ! ይህ ሕዝብ አንተ እውነተኛ አምላክ መሆንህንና ወደ አንተም ያቀረብከው አንተ ራስህ መሆንህን እንዲያውቅ እባክህ መልስ ስጠኝ፤ አምላክ ሆይ፥ ስማኝ!” ከዚህ በኋላ ጌታ እሳትን ላከ፤ ያም እሳት መሥዋዕቱን፥ እንጨቱንና ድንጋዩን አቃጠለ፤ ምድሩንም ለበለበ፤ በጉድጓዱ የነበረውንም ውሃ አደረቀ፤ ሰዎቹም ይህን ባዩ ጊዜ በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፍተው በመደነቅ “ጌታ አምላክ ነው! እውነተኛ አምላክ እርሱ ብቻ ነው!” አሉ።