1 ነገሥት 13:16-18
1 ነገሥት 13:16-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እርሱም፥ “ከአንተ ጋር እመለስና እገባ ዘንድ አይቻለኝም፤ በዚህም ስፍራ ከአንተ ጋር እንጀራ አልበላም፤ ውኃም አልጠጣም፤ በዚያ እንጀራ አትብላ፥ ውኃም አትጠጣ፤ በመጣህበት መንገድም አትመለስ ብሎ እግዚአብሔር በቃሉ አዝዞኛልና” አለው። እርሱም፥ “እኔ ደግሞ እንዳንተ ነቢይ ነኝ፤ መልአክም፦ እንጀራ ይበላ ዘንድ ውኃም ይጠጣ ዘንድ ከአንተ ጋር ወደ ቤትህ መልሰው ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ተናገረኝ” አለው። ዋሽቶም ተናገረው።
1 ነገሥት 13:16-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የእግዚአብሔርም ሰው እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ተመልሼ ከአንተ ጋራ አልሄድም፤ በዚህ ቦታም ዐብሬህ እንጀራ አልበላም፤ ውሃም አልጠጣም፤ ‘እዚያ እንጀራ እንዳትበላ፣ ውሃም እንዳትጠጣ፣ በሄድህበትም መንገድ እንዳትመለስ’ ተብዬ በእግዚአብሔር ቃል ታዝዣለሁና” አለው። ሽማግሌው ነቢይ ግን፣ “እኔም እኮ እንደ አንተው ነቢይ ነኝ፤ መልአክ በእግዚአብሔር ቃል፣ ‘እንጀራ እንዲበላና ውሃ እንዲጠጣ መልሰህ ወደ ቤትህ አምጣው’ ብሎኝ ነው” አለው፤ ነገር ግን ውሸቱን ነበር።
1 ነገሥት 13:16-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እርሱም “ከአንተ ጋር እመለስና እገባ ዘንድ አይቻለኝም፤ በዚህም ስፍራ ከአንተ ጋር እንጀራ አልበላም፤ ውሃም አልጠጣም፤ ‘በዚያ እንጀራ አትብላ፤ ውሃም አትጠጣ፤ በመጣህበትም መንገድ አትመለስ፤’ በሚል በእግዚአብሔር ቃል ተብሎልኛልና፤” አለ። እርሱም “እኔ ደግሞ እንደ አንተ ነቢይ ነኝ፤ መልአክም ‘እንጀራ ይበላ ዘንድ ውሃም ይጠጣ ዘንድ ከአንተ ጋር ወደ ቤትህ መልሰው፤’ ብሎ በእግዚአብሔር ቃል ተናገረኝ፤” አለው። ዋሽቶም ተናገረው።
1 ነገሥት 13:16-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከይሁዳ የመጣው የእግዚአብሔር ነቢይ ግን እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ከአንተ ጋር አብሬ ወደ ቤት መሄድም ሆነ ግብዣህን መቀበል አልችልም፤ በዚህም ከአንተ ጋር ምንም ዐይነት እህል ውሃ አልቀምስም፤ በዚህ ቦታ ምንም ዐይነት እህል ውሃ እንዳልቀምስ በመጣሁበት መንገድ እንኳ ተመልሼ እንዳልሄድ እግዚአብሔር አዞኛል።” ከዚህ በኋላ ከቤትኤል የመጣው ሽማግሌ ነቢይ “እኔም እንዳንተው ነቢይ ነኝ፤ ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ወስጄ እንዳስተናግድህ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ነግሮኛል” አለው፤ ሽማግሌው ነቢይ የተናገረው ግን በመዋሸት ነበር።
1 ነገሥት 13:16-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እርሱም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ከአንተ ጋር አብሬ መመለስ አልችልም፤ በዚህም ከአንተ ጋር ምንም ዓይነት እህልም ውሃም አልቀምስም። በዚህ ቦታ ምንም ዓይነት እህል ውሃ እንዳልቀምስ በመጣሁበት መንገድ እንኳ ተመልሼ እንዳልሄድ ጌታ አዞኛል።” ከዚህ በኋላ ከቤትኤል የመጣው ሽማግሌ ነቢይ “እኔም እንዳንተው ነቢይ ነኝ፤ ከእኔ ጋር ወደ ቤቴ ወስጄ እንዳስተናግድህ ከጌታ የታዘዘ መልአክ ነግሮኛል” አለው፤ ነገር ግን ዋሽቶ ነበር።