1 ቆሮንቶስ 7:1-9
1 ቆሮንቶስ 7:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ስለ ጻፋችሁልኝስ ለሰው ወደ ሴት አለመቅረብ ይሻለዋል። ነገር ግን እንዳትሴስኑ ሰው ሁሉ በሚስቱ ይወሰን፤ ሴትም ሁላ በባልዋ ትወሰን። ለሚስትም ባልዋ የሚገባትን ያድርግላት፤ እንዲሁ ሚስትም ለባልዋ የሚገባውን ታድርግለት። ሚስት በራስዋ አካል ሥልጣን የላትም፤ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ባል በራሱ አካል ሥልጣን የለውም፤ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ። ለጸሎት እንድትተጉ ከምትስማሙበት ጊዜ ብቻ በቀር፥ ባልና ሚስት አትለያዩ፤ ዳግመኛ ሰይጣን ድል እንዳያደርጋችሁ በአንድነት ኑሩ፤ ሰውነታችሁ ደካማ ነውና ። ይህንም የምላችሁ እንደ ፈቃድ ነው እንጂ፥ ላዝዛችሁ አይደለም። ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁና፤ ነገር ግን ሰው ሁሉ እግዚአብሔር እንደ አደለው ጸጋ ይኑር፤ ግብሩ እንዲህ የሆነ አለና፤ ግብሩ ሌላ የሆነም አለና። ነገር ግን ያላገቡትንና አግብተው የፈቱትን እንደ እኔ ሆነው ቢኖሩ ይሻላቸዋል እላለሁ። መታገሥ ባይችሉ ግን ያግቡ፤ በፍትወት ከመቃጠል ማግባት ይሻላልና።
1 ቆሮንቶስ 7:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለ ጻፋችሁልኝ ጕዳይ፣ ሰው ወደ ሴት ባይደርስ መልካም ነው፤ ነገር ግን ከዝሙት ለመጠበቅ፣ እያንዳንዱ ሰው የራሱ ሚስት ትኑረው፤ እያንዳንዷም ሴት የራሷ ባል ይኑራት። ባል ለሚስቱ የሚገባትን ሁሉ ያድርግላት፤ ሚስትም ለባሏ እንዲሁ። ሚስት በራሷ አካል ላይ ሥልጣን የላትም፤ ባሏ እንጂ። እንዲሁም ባል በራሱ አካል ላይ ሥልጣን የለውም፤ ሚስቱ እንጂ። በጸሎት ለመትጋት ተስማምታችሁ ለተወሰነ ጊዜ ካልሆነ በቀር፣ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ ራሳችሁን ባለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ እንደ ገና ዐብራችሁ ሁኑ። ይህን የምለው ግን እንደ ትእዛዝ ሳይሆን እንደ ምክር ነው። ሰው ሁሉ እንደ እኔ ቢሆን ምኞቴ ነው። ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው ከእግዚአብሔር የተቀበለው የራሱ የሆነ ስጦታ አለው፤ አንዱ አንድ ዐይነት ስጦታ ሲኖረው፣ ሌላው ደግሞ ሌላ ዐይነት ስጦታ አለው። ላላገቡና ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች ግን እንዲህ እላለሁ፤ ሳያገቡ እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው። ነገር ግን ራሳቸውን መግዛት ካልቻሉ ያግቡ፤ በምኞት ከመቃጠል ማግባት ይሻላልና።
1 ቆሮንቶስ 7:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ስለ ጻፋችሁልኝስ ነገር፥ ከሴት ጋር አለመገናኘት ለሰው መልካም ነው። ነገር ግን ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት። ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፥ እንደዚሁም ደግሞ ሚስቲቱ ለባልዋ። ሚስት በገዛ ሥጋዋ ላይ ሥልጣን የላትም፥ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ደግሞ ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም፥ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ። ለጸሎት ትተጉ ዘንድ ተስማምታችሁ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፥ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ ደግሞ አብራችሁ ሁኑ። ዳሩ ግን ይህን እንደ ፈቃድ እላለሁ እንጂ እንደ ትእዛዝ አይደለም። ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁና፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ለራሱ የጸጋ ስጦታ አለው፥ አንዱ እንደዚህ ሁለተኛውም እንደዚያ። ላላገቡና ለመበለቶች ግን እላለሁ፦ እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው፤ ነገር ግን በምኞት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና ራሳቸውን መግዛት ባይችሉ ያግቡ።
1 ቆሮንቶስ 7:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለ ጻፋችሁልኝ ጥያቄ ሰው ከሴት ጋር ግንኙነት ባያደርግ መልካም ነው። ነገር ግን ከዝሙት ለመራቅ እያንዳንዱ ወንድ የራሱ ሚስት ትኑረው፤ እያንዳንዱዋም ሴት የራስዋ ባል ይኑራት። ባል ለሚስቱ ማድረግ የሚገባውን የጋብቻ መብትዋን አይከልክላት፤ እንዲሁም ሚስት ለባልዋ ማድረግ የሚገባትን የጋብቻ መብቱን አትከልክለው። ሚስት በሰውነቷ ላይ ሥልጣን የላትም፤ በእርስዋ ሰውነት ላይ ሥልጣን ያለው ባልዋ ነው። እንዲሁም ባል በሰውነቱ ላይ ሥልጣን የለውም፤ በእርሱ ሰውነት ላይ ሥልጣን ያላት ሚስቱ ነች። በጸሎት ለመትጋት ሁለታችሁም ተስማምታችሁ ለተወሰነ ጊዜ ካልሆነ በቀር በመለያየት አንዱ የሌላውን የጋብቻ መብት አይከልክል። በዚህም ምክንያት ራሳችሁን መቈጣጠር አቅቶአችሁ ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ እንደገና አብራችሁ ሁኑ። ይህን ግን የምላችሁ እንደምክር ነው እንጂ እንደ ትእዛዝ አይደለም። ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሚስት ሳያገባ ቢኖር በወደድኩ ነበር፤ ነገር ግን ለእያንዳንዱ እግዚአብሔር የተለየ ስጦታ ሰጥቶታል፤ አንዱ አንድ ዐይነት ስጦታ፥ ሌላውም ሌላ ዐይነት ስጦታ አለው። ላላገቡና እንዲሁም ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች የምለው እንዲህ ነው፤ ሳያገቡ እንደ እኔ ሆነው ቢኖሩ መልካም ነው። ነገር ግን በሥጋ ምኞት ከመቃጠል ይልቅ ማግባት የተሻለ ነውና ራሳቸውን መቈጣጠር ቢያቅታቸው ያግቡ።
1 ቆሮንቶስ 7:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የጻፋችሁልኝን ነገር በተመለከተ፥ ከሴት ጋር አለመገናኘት ለሰው መልካም ነው። ነገር ግን ከዝሙት ለመራቅ እያንዳንዱ ወንድ ለራሱ ሚስት ትኑረው፤ እያንዳንዱዋም ሴት ለራስዋ ባል ይኑራት። ባል ለሚስቱ የሚገባትን ያድርግላት፤ እንደዚሁም ደግሞ ሚስት ለባሏ። ሚስት በገዛ ሰውነቷ ላይ ሥልጣን የላትም፤ ሥልጣን ለባሏ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ደግሞ ባል በገዛ ሰውነቱ ላይ ሥልጣን የለውም፤ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ። ለጸሎት ለመትጋት ተስማምታችሁ ለተወሰነ ጊዜ ካልሆነ በቀር፥ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ እንዲሁም ራሳችሁን ስለ አለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ አብራችሁ ሁኑ። ዳሩ ግን ይህን እንደ ፈቃድ እላለሁ እንጂ እንደ ትእዛዝ አይደለም። ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁ፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ከእግዚአብሔር ለራሱ የጸጋ ስጦታ አለው፤ አንዱ እንደዚህ ሌላውም እንደዚያ ዓይነት። ላላገቡና ለመበለቶች ግን እላለሁ እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው፤ ነገር ግን በመሻት ከመቃጠል መጋባት ይሻላልና ራሳቸውን መግዛት ካልቻሉ ያግቡ።