1 ቆሮንቶስ 5:9-13
1 ቆሮንቶስ 5:9-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዘማውያን ጋር አንድ እንዳትሆኑ በዚህ መልእክት ጻፍሁላችሁ። የዚህ ዓለም ዝሙት ብቻ አይደለም፤ ቀማኞችና ዘራፊዎች፥ ጣዖትን የሚያመልኩ ደግሞ አሉ፤ ያለዚያስ ከዚህ ዓለም ልትለዩ ይገባል። አሁንም ከወንድሞች መካከል ዘማዊ፥ ወይም ገንዘብን የሚመኝ፥ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ፥ ወይም ዐመፀኛ፥ ወይም ተራጋሚ፥ ወይም ሰካራም፥ ወይም የሚቀማ ቢኖር እንደዚህ ካለ ሰው ጋር አንድ እንዳትሆኑ ጻፍሁላችሁ፥ እንደዚህ ካለው ሰው ጋር መብልም እንኳ አትብሉ፤ ምን አግዶኝ፥ በውጭ ባለው ላይ እፈርድበታለሁ? እናንተስ በውስጥ ከእናንተ ጋር የሚኖሩትን ፈርዳችሁ ቅጡአቸው። በውጭ ያሉትን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል፤ ይቀጣቸዋልም፤ ክፉውን ከእናንተ አርቁ።
1 ቆሮንቶስ 5:9-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከሴሰኞች ጋራ እንዳትተባበሩ በመልእክቴ ጽፌላችሁ ነበር፤ እንዲህም ስል በጠቅላላው ከዚህ ዓለም ሴሰኞች ወይም ስግብግቦችና ቀማኞች ወይም ከጣዖት አምላኪዎች ጋራ አትተባበሩ ለማለት አይደለም፤ እንደዚያማ ቢሆን ከዚህ ዓለም ጨርሶ መለየት ያስፈልጋችሁ ነበር። ነገር ግን አሁን የጻፍሁላችሁ፣ “ወንድም ነኝ” እያለ ከሚሴስን ወይም ከሚስገበገብ ወይም ጣዖትን ከሚያመልክ ወይም ከሚሳደብ ወይም ከሚሰክር ወይም ከሚቀማ ጋራ እንዳትተባበሩ ነው፤ ከእንደዚህ ዐይነቱ ሰው ጋራ ምግብ እንኳ አትብሉ። ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ባሉት ሰዎች ላይ ለመፍረድ እኔን ምን አግብቶኝ? በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባሉት ሰዎች ላይ እናንተ አትፈርዱምን? ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ባሉት ላይ የሚፈርድ ግን እግዚአብሔር ነው፤ እንግዲህ፣ “ክፉውን ሰው ከመካከላችሁ አስወግዱት።”
1 ቆሮንቶስ 5:9-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከሴሰኞች ጋር እንዳትተባበሩ በመልእክቴ ጻፍሁላችሁ። በጠቅላላው የዚህን ዓለም ሴሰኞችን፥ ወይም ገንዘብን የሚመኙትን ነጣቂዎችንም፥ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩትን አላልሁም፤ ይህስ ቢሆን ከዓለም ልትወጡ ይገባችሁ ነበር። አሁን ግን ወንድሞች ከሚባሉት አንዱ ሴሰኛ ወይም ገንዘብን የሚመኝ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካር ወይም ነጣቂ ቢሆን ከእርሱ ጋር እንዳትተባበሩ እጽፍላችኋለሁ፤ እንደነዚህ ካለው ጋር መብል እንኳን አትብሉ። በውጭ ባሉ ሰዎች ላይ መፍረድ ምን አግዶኝ? በውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ እናንተ አትፈርዱምን? በውጭ ባሉቱ ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት።
1 ቆሮንቶስ 5:9-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በፊት በጻፍኩላችሁ መልእክት ከአመንዝራዎች ጋር አትተባበሩ ብያችሁ ነበር። ይህንንም ስል በአጠቃላይ ከዚህ ዓለም አመንዝራዎች ወይም ከስግብግብ ግለሰቦች ወይም ከሌቦች ወይም ከጣዖት አምላኪዎች ጋር አትተባበሩ ማለቴ አይደለም፤ እንዲህማ ከሆነ ከዓለም መውጣት ያስፈልጋችሁ ነበር ማለት ነው። እኔ ግን የጻፍኩላችሁ ክርስቲያኖች ተብለው ከሚያመነዝሩ፥ ወይም ከሚስገበገቡ፥ ወይም ጣዖት ከሚያመልኩ፥ ወይም የሰውን ስም ከሚያጠፉ፥ ወይም ከሚሰክሩ፥ ወይም ከቀማኞች ጋር አትተባበሩ ብዬ ነው። እንደእነዚህ ካሉት ሰዎች ጋር፥ መብል አብራችሁ አትብሉ። ከክርስቲያናዊ ማኅበር ውጪ ባሉት ሰዎች ላይ ለመፍረድ እኔ ማን ነኝ? በክርስቲያናዊ ማኅበር ውስጥ ስላሉት ሰዎች ጉዳይ እናንተስ መፍረድ ትችሉ የለምን? በውጪ ስላሉት ሰዎች ጉዳይ የሚፈርድ እግዚአብሔር ነው፤ እንግዲህ መጽሐፍ እንደሚል “ክፉውን ሰው ከመካከላችሁ አስወግዱ።”
1 ቆሮንቶስ 5:9-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በመልእክቴ ከሴሰኞች ጋር እንዳትተባበሩ ጻፍሁላችሁ። ይህም በጠቅላላው የዚህን ዓለም ሴሰኞችን፥ ወይም ገንዘብን የሚመኙትን ነጣቂዎችንም፥ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩትን ማለቴ አይደለም፤ እንዲህማ ቢሆን ከዓለም ልትወጡ ይገባችሁ ነበር። አሁን ግን ወንድሞች ከሚባሉት አንዱ ሴሰኛ ወይም ስግብግብ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ ወይም ተሳዳቢ ወይም ሰካራም ወይም ነጣቂ ቢሆን ከእርሱ ጋር እንዳትተባበሩ እጽፍላችኋለሁ፤ እንደዚህ ካለው ጋር መብል እንኳን አትብሉ። በውጭ ባሉ ሰዎች ላይ መፍረድ ምን አግዶኝ? በውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ እናንተ አትፈርዱምን? በውጭ ባሉት ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል። ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት።