1 ቆሮንቶስ 3:1-9

1 ቆሮንቶስ 3:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ወድ​ሞች ሆይ፥ እኔስ የሥ​ጋና የደም እንደ መሆ​ና​ችሁ፥ ክር​ስ​ቶ​ስ​ንም በማ​መን ሕፃ​ናት እንደ መሆ​ና​ችሁ እንጂ እንደ መን​ፈ​ሳ​ው​ያን ላስ​ተ​ም​ራ​ችሁ አል​ቻ​ል​ሁም። ወተ​ትን ጋት​ኋ​ችሁ፤ ጽኑ መብ​ልም ያበ​ላ​ኋ​ችሁ አይ​ደ​ለም፤ ገና አል​ጠ​ነ​ከ​ራ​ች​ሁ​ምና፤ በሥ​ጋዊ ሕግም ትኖ​ራ​ላ​ች​ሁና እርስ በር​ሳ​ችሁ የም​ት​ቃ​ኑና የም​ት​ከ​ራ​ከሩ ከሆነ ግን ሥጋ​ው​ያን መሆ​ና​ችሁ አይ​ደ​ለ​ምን? እንደ ሰው ልማ​ድስ የም​ት​ኖሩ መሆ​ና​ችሁ አይ​ደ​ለ​ምን? ከመ​ካ​ከ​ላ​ችሁ፥ “እኔ የጳ​ው​ሎስ ነኝ” የሚል አለና፤ ሌላ​ውም፥ “እኔ የአ​ጵ​ሎስ ነኝ” ቢል እና​ንተ ሥጋ​ው​ያን መሆ​ና​ችሁ አይ​ደ​ለ​ምን? እን​ግ​ዲህ ጳው​ሎስ ምን​ድን ነው? አጵ​ሎ​ስስ ምን​ድን ነው? እነ​ር​ሱስ በቃ​ላ​ቸው የአ​መ​ና​ችሁ አገ​ል​ጋ​ዮች ናቸው፤ ለእ​ያ​ን​ዳ​ን​ዱም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እንደ ሰጠው ነው። እኔ ተከ​ልሁ፤ አጵ​ሎ​ስም አጠጣ፤ ነገር ግን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አሳ​ደገ። አሁ​ንም የሚ​ተ​ክ​ልም ቢሆን፥ የሚ​ያ​ጠ​ጣም ቢሆን የሚ​ጠ​ቅ​መው ነገር የለም፤ የሚ​ያ​ሳ​ድግ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ነው እንጂ። የሚ​ተ​ክ​ልም፥ የሚ​ያ​ጠ​ጣም አንድ ናቸው፤ ሁሉም እንደ ድካ​ማ​ቸው ዋጋ​ቸ​ውን ይቀ​በ​ላሉ። በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሥራ እን​ተ​ባ​በ​ራ​ለ​ንና፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም አገ​ል​ጋ​ዮች ነንና፤ እና​ን​ተም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሕንፃ ናችሁ።

1 ቆሮንቶስ 3:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ወንድሞች ሆይ፤ በክርስቶስ ገና ሕፃናት እንደ መሆናችሁ፣ እንደ ሥጋውያን እንጂ እንደ መንፈሳውያን ልናገራችሁ አልቻልሁም። ገና ስላልጠነከራችሁ ወተት እንጂ ጠንካራ ምግብ አልመገብኋችሁም፤ አሁንም ቢሆን ገና ናችሁ። አሁንም ሥጋውያን ናችሁ፤ በመካከላችሁ ቅናትና ክርክር አለ። ታዲያ፣ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደለምን? ተግባራችሁስ እንደ ማንኛውም ሰው ተግባር መሆኑ አይደለምን? ምክንያቱም አንዱ፣ “እኔ የጳውሎስ ነኝ”፣ ሌላው ደግሞ፣ “እኔ የአጵሎስ ነኝ” ቢል፣ ሥጋ ለባሽ ብቻ መሆናችሁ አይደለምን? ለመሆኑ አጵሎስ ምንድን ነው? ጳውሎስስ ምንድን ነው? ጌታ ለእያንዳንዳቸው በሰጣቸው መጠን የሚሠሩ አገልጋዮች ናቸው፤ እናንተም ወደ እምነት የመጣችሁት በእነርሱ አማካይነት ነው። እኔ ተከልሁ፤ አጵሎስ ውሃ አጠጣ፤ ያሳደገው ግን እግዚአብሔር ነው። ስለዚህ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ፣ የሚተክልም ሆነ ውሃ የሚያጠጣ ምንም አይደለም። የሚተክልም ሆነ የሚያጠጣ አንድ ናቸው፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን የራሱን ሽልማት ይቀበላል። እኛ የእግዚአብሔር የሆንን ዐብሮ ሠራተኞች ነንና፤ እናንተም የእግዚአብሔር ዕርሻ፣ የእግዚአብሔር ሕንጻ ናችሁ።

1 ቆሮንቶስ 3:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ የሥጋ እንደ መሆናችሁ፥ በክርስቶስም ሕፃናት እንደ መሆናችሁ እንጂ መንፈሳውያን እንደ መሆናችሁ ልናገራችሁ አልቻልሁም። ገና ጽኑ መብል ለመብላት አትችሉም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ፤ ገና ሥጋውያን ናችሁና እስከ አሁን ድረስ ገና አትችሉም። ቅናትና ክርክር ስለሚገኝባችሁ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደላችሁምን? እንደ ሰው ልማድስ አትመላለሱምን? አንዱ፦ እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ ሁለተኛውም፦ እኔ የአጵሎስ ነኝ ቢል ሰዎች ብቻ መሆናችሁ አይደለምን? አጵሎስ እንግዲህ ምንድር ነው? ጳውሎስስ ምንድር ነው? በእነርሱ እጅ ያመናችሁ አገልጋዮች ናቸው፤ ለእያንዳንዳቸውም ጌታ እንደ ሰጣቸው ያገለግላሉ። እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፤ እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም። የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው፥ ነገር ግን እያንዳንዱ እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል። የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና።

1 ቆሮንቶስ 3:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ወንድሞቼ ሆይ! እኔ ሳስተምራችሁ ሥጋውያንና በክርስቶስ ገና ያልጠነከራችሁ ሕፃናት እንደ መሆናችሁ መጠን ነው እንጂ መንፈሳውያን እንደ መሆናችሁ መጠን አይደለም። ጠንካራ ምግብ መብላት እንደማይችሉ ሕፃናት ስለ ሆናችሁ እኔ የመገብኳችሁ ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም፤ አሁንም ቢሆን ጠንካራ ምግብ መመገብ ገና የማትችሉ ናችሁ። እናንተ አሁንም ገና ሥጋውያን ናችሁ፤ እርስ በርሳችሁ ስለምትቀናኑና ስለምትከራከሩ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደለምን? የምትሠሩትስ እንደ ተራ ሰው አይደለምን? አንዱ “እኔ የጳውሎስ ነኝ” ሌላው ደግሞ “እኔ የአጵሎስ ነኝ” ሲል ተራ የዓለም ሰዎች ብቻ መሆናችሁ አይደለምን? ለመሆኑ አጵሎስ ምንድን ነው? ጳውሎስስ ምንድን ነው? እነርሱ እናንተ እንድታምኑ ያደረጉአችሁ አገልጋዮች ናቸው፤ እያንዳንዳቸው የሚያገለግሉትም ጌታ ለያንዳንዳቸው በመደበላቸው ሥራ ነው፤ እኔ ተከልኩ፤ አጵሎስ ውሃ አጠጣ፤ ያሳደገው ግን እግዚአብሔር ነው። ስለዚህ ለሥራው ዋና የሆነው ተክሉን ያሳደገው እግዚአብሔር ነው እንጂ የተከለም ሆነ ውሃ ያጠጣ ምንም አይደለም። የተከለም ሆነ ውሃ ያጠጣ እኩል ናቸው፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ዋጋውን ይቀበላል። እኛ ለእግዚአብሔር አብረን የምንሠራ አገልጋዮች ነን፤ እናንተም የእግዚአብሔር እርሻና የእግዚአብሔር ሕንጻ ናችሁ።

1 ቆሮንቶስ 3:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ወንድሞች ሆይ! እኔም፥ የሥጋ እንደ መሆናችሁ፥ በክርስቶስም ሕፃናት እንደ መሆናችሁ እንጂ መንፈሳውያን እንደ መሆናችሁ ልናገራችሁ አልቻልሁም። ገና ጠንካራ መብል ለመብላት አልቻላችሁም ነበርና ወተት ጋትኋችሁ፤ ነገር ግን አሁንም ቢሆን ገና አትችሉም፤ እናንተ ገና ሥጋውያን ናችሁ፤ ቅናትና ጭቅጭቅ እስከተገኘባችሁ፥ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደለምን? እንደ ሰው ልማድስ አትመላለሱምን? አንዱ “እኔ የጳውሎስ ነኝ፤” ሌላው ደግሞ “እኔ የአጵሎስ ነኝ፤” ቢል ሰዎች ብቻ መሆናችሁ አይደለምን? አጵሎስ እንግዲህ ምንድነው? ጳውሎስስ ምንድነው? በእነርሱ በኩል ያመናችሁ፥ ለእያንዳንዳቸውም ጌታ እንደሰጣቸው፥ አገልጋዮች ናቸው፤ እኔ ተከልሁ፤ አጵሎስም አጠጣ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፤ እንግዲህ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ሆነ ወይም የሚያጠጣ ቢሆን ምንም አይደለም። የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው፤ እያንዳንዱም እንደ ራሱ ድካም መጠን የራሱን ክፍያ ይቀበላል። ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሠራ ነንና፤ የእግዚአብሔር እርሻ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ።