1 ቆሮንቶስ 15:1-6
1 ቆሮንቶስ 15:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወንድሞቻችን ሆይ፥ ያስተማርኋችሁንና የተቀበላችሁትን ያላችሁበትን፥ በእርሱም የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ። ያስተማርኋችሁን ታስቡ እንደ ሆነ በቃሌ አስተምሬአችኋለሁ፤ ያለዚያ ግን ማመናችሁ ከንቱ ነው። እኔ የተማርሁትን አስቀድሜ መጽሐፍ እንደሚል እንዲህ ብዬ አስተማርኋችሁ፥ “ክርስቶስ ስለ ኀጢአታችን ሞተ። ተቀበረ፤ እንደ ተጻፈም በሦስተኛው ቀን ተነሣ።” ለጴጥሮስ ታየው፤ ከዚህም በኋላ ለዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርቱ ታያቸው። ከዚህም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታያቸው፤ ከእነርሱ ብዙዎቹ እስከ ዛሬ አሉ፤ አንዳንዶቹ ግን አንቀላፍተዋል።
1 ቆሮንቶስ 15:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አሁንም ወንድሞች ሆይ፤ የሰበክሁላችሁንና የተቀበላችሁትን፣ ደግሞም ጸንታችሁ የቆማችሁበትን ወንጌል ላሳስባችሁ እወድዳለሁ፤ የሰበክሁላችሁን ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ፣ በዚህ ወንጌል ትድናላችሁ፤ አለዚያ ያመናችሁት በከንቱ ነው። እኔ የተቀበልሁትንና ከሁሉ በላይ የሆነውን ለእናንተ አስተላልፌአለሁ፤ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚሉት ክርስቶስ ስለ ኀጢአታችን ሞተ፤ ተቀበረ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተጻፈውም በሦስተኛው ቀን ተነሣ፤ ከዚያም ለኬፋ ታየ፤ ቀጥሎም ለዐሥራ ሁለቱ ታየ፤ ከዚያም በኋላ ከዐምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነዚህም አብዛኛዎቹ በሕይወት አሉ፤ አንዳንዶቹ ግን አንቀላፍተዋል።
1 ቆሮንቶስ 15:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ወንድሞች ሆይ፥ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤ በከንቱ ካላመናችሁ በቀር፥ ብታስቡት፥ በምን ቃል እንደ ሰበክሁላችሁ አሳስባችኋለሁ። እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ፦ መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤
1 ቆሮንቶስ 15:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አሁን ደግሞ ወንድሞች ሆይ! ያስተማርኳችሁን የወንጌል ቃል ላስታውሳችሁ እፈልጋለሁ፤ ይህም የወንጌል ቃል እናንተ የተቀበላችሁትና ጸንታችሁ የቆማችሁበት ነው። እኔ ያስተማርኳችሁን የወንጌል ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ በእርሱ ትድናላችሁ፤ አለበለዚያ ግን ያመናችሁት በከንቱ ነው። እኔ የተቀበልኩትን በመጀመሪያ ደረጃ ያለውን ነገር ለእናንተ አስተላለፍኩላችሁ፤ ያስተላለፍኩላችሁም ነገር በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተጻፈው ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፤ ተቀበረ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተጻፈውም በሦስተኛው ቀን ከሞት ተነሣ የሚል ነው። እርሱ ለጴጥሮስ ታየ፤ ኋላም ለዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ታየ፤ ከአምስት መቶ ለሚበልጡ ተከታዮቹም በአንድ ጊዜ ታያቸው፤ ከእነርሱ አብዛኞቹ እስከ አሁን በሕይወት አሉ፤ አንዳንዶቹ ግን ሞተዋል።
1 ቆሮንቶስ 15:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወንድሞች ሆይ! አሁን የሰበክሁላችሁንና የተቀበላችሁትን ደግሞም ጸንታችሁ የቆማችሁበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤ የሰበክሁላችሁን ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ፥ ያመናችሁት በከንቱ ካልሆነ በስተቀር፥ የምትድኑበትን ወንጌል ነው። እኔ የተቀበልሁትንና ከሁሉ በላይ የሆነውን ለእናንተ አስተላልፌአለሁ፤ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚሉት ክርስቶስ ለኀጢአታችን ሞተ፤ ተቀበረ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈውም በሦስተኛው ቀን ተነሣ፤ ከዚያም ለኬፋ ታየ፤ ቀጥሎም ለዐሥራ ሁለቱ ታየ፤ ከዚያም በኋላም ከአምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነዚህም አብዛኛዎቹ እስካሁን በሕይወት አሉ፤ አንዳንዶቹ ግን አንቀላፍተዋል።