1 ቆሮንቶስ 13:1-13

1 ቆሮንቶስ 13:1-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የሰ​ውን ሁሉ ቋንቋ ባውቅ፥ የመ​ላ​እ​ክ​ት​ንም ሁሉ ቋንቋ ባውቅ፥ ነገር ግን ፍቅር ከሌ​ለኝ እን​ደ​ሚ​ጮህ ነሐስ፥ ወይም እን​ደ​ሚ​መታ ከበሮ መሆኔ ነው። ትን​ቢት ብና​ገር፥ የተ​ሰ​ው​ረ​ውን ሁሉ፥ ጥበ​ብ​ንም ሁሉ ባውቅ፥ ተራራ እስከ ማፍ​ለስ የሚ​ያ​ደ​ርስ ፍጹም እም​ነ​ትም ቢኖ​ረኝ ፍቅር ከሌ​ለኝ ከንቱ ነኝ። ገን​ዘ​ቤን ሁሉ ለም​ጽ​ዋት ብሰጥ፥ ሥጋ​ዬ​ንም ለእ​ሳት መቃ​ጠል ብሰጥ፥ ነገር ግን ፍቅር ከሌ​ለኝ ምንም አይ​ጠ​ቅ​መ​ኝም። ፍቅር ያስ​ታ​ግ​ሣል፤ ፍቅር ያስ​ተ​ዛ​ዝ​ናል፤ ፍቅር አያ​ቀ​ና​ናም፤ ፍቅር አያ​ስ​መ​ካም፤ ፍቅር ልቡ​ናን አያ​ስ​ታ​ብ​ይም። ብቻ​ዬን ይድ​ላኝ አያ​ሰ​ኝም፤ አያ​በ​ሳ​ጭም፤ ክፉ ነገ​ር​ንም አያ​ሳ​ስ​ብም። ጽድ​ቅን በመ​ሥ​ራት ደስ ያሰ​ኛል እንጂ፥ ግፍን በመ​ሥ​ራት ደስ አያ​ሰ​ኝም። በሁሉ ያቻ​ች​ላል፤ በሁ​ሉም ያስ​ተ​ማ​ም​ናል፤ በሁ​ሉም ተስፋ ያስ​ደ​ር​ጋል፥ በሁ​ሉም ያስ​ታ​ግ​ሣል። ፍቅር ለዘ​ወ​ትር አይ​ጥ​ልም፤ ትን​ቢት የሚ​ና​ገ​ርም ያል​ፋል፤ ይሻ​ራ​ልም፤ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚ​ና​ገ​ርም ያል​ፋል፤ ይቀ​ራል፤ የሚ​ራ​ቀ​ቅም ያል​ፋል፤ ይጠ​ፋል። በየ​ገጹ ጥቂት ጥቂት እና​ው​ቃ​ለ​ንና፤ ጥቂት ጥቂት ትን​ቢ​ትም እን​ና​ገ​ራ​ለ​ንና። ፍጹም የሆነ ሲመጣ ግን ያ ተከ​ፍሎ የነ​በ​ረው ይሻ​ራል። እኔ ልጅ በነ​በ​ርሁ ጊዜ እንደ ልጅ እና​ገር ነበር፤ እንደ ልጅም አስብ ነበር፤ እንደ ልጅም እመ​ክር ነበር፤ በአ​ደ​ግሁ ጊዜ ግን የል​ጅ​ነ​ትን ጠባይ ሁሉ ሻርሁ። አሁን ግን ታወ​ቀኝ፤ በግ​ል​ጥም ተረ​ዳኝ፤ በመ​ስ​ታ​ወ​ትም እን​ደ​ሚ​ያይ ሰው ዛሬ በድ​ን​ግ​ዝ​ግ​ዝታ እና​ያ​ለን፤ ያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እና​ያ​ለን፤ አሁን በከ​ፊል፥ ኋላ ግን እንደ ተገ​ለ​ጠ​ልኝ መጠን ሁሉን አው​ቃ​ለሁ። አሁ​ንም እነ​ዚህ ሦስቱ እም​ነት፥ ተስ​ፋና ፍቅር ጸን​ተው ይኖ​ራሉ፤ ከሁሉ ግን ፍቅር ይበ​ል​ጣል።

1 ቆሮንቶስ 13:1-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሿሿ ጸናጽል ነኝ። የትንቢት ስጦታ ቢኖረኝ፣ ምስጢርን ሁሉና ዕውቀትን ሁሉ ባውቅ፣ ተራራንም ከቦታው የሚነቅል እምነት ቢኖረኝ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ያለኝን ሁሉ ለድኾች ብሰጥ፣ ሰውነቴንም እንዲቃጠል ለእሳት ብዳርግ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። ፍቅር ታጋሽ ነው፤ ደግሞም ቸር ነው። ፍቅር አይመቀኝም፤ አይመካም፤ አይታበይም፤ ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፤ ራስ ወዳድ አይደለም፤ አይበሳጭም፤ በደልን አይቈጥርም። ፍቅር ከእውነት ጋራ እንጂ በዐመፅ ደስ አይሰኝም። ፍቅር ሁልጊዜ ይታገሣል፤ ሁልጊዜ ያምናል፤ ሁልጊዜ ተስፋ ያደርጋል፤ ሁልጊዜ ጸንቶ ይቆማል። ፍቅር ከቶ አይወድቅም፤ ነገር ግን ትንቢት ቢሆን ይሻራል፤ ልሳንም ቢሆን ይቀራል፤ ዕውቀትም ቢሆን ይሻራል። ምክንያቱም የምናውቀው በከፊል ነው፤ ትንቢት የምንናገረውም በከፊል ነው። ነገር ግን ፍጹም የሆነው ሲመጣ በከፊል የነበረው ይሻራል። ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፤ እንደ ልጅ ዐስብ ነበር፤ እንደ ልጅም አሰላ ነበር። ከጐለመስሁ በኋላ ግን የልጅነትን ነገር እርግፍ አድርጌ ትቻለሁ። አሁን የምናየው በመስተዋት ውስጥ እንደሚታይ በድንግዝግዝ ነው፤ በዚያ ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን። አሁን የማውቀው በከፊል ነው፤ በዚያ ጊዜ እኔ ራሴ ሙሉ በሙሉ የታወቅሁትን ያህል ዐውቃለሁ። እንግዲህ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።

1 ቆሮንቶስ 13:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ። ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። ፍቅር ይታገሣል፥ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፥ አይታበይም፤ የማይገባውን አያደርግም፥ የራሱንም አይፈልግም፥ አይበሳጭም፥ በደልን አይቆጥርም፤ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም፤ ሁሉን ይታገሣል፥ ሁሉን ያምናል፥ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ይጸናል። ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል። ከእውቀት ከፍለን እናውቃለንና፥ ከትንቢትም ከፍለን እንናገራለንና፤ ፍጹም የሆነ ሲመጣ ግን ተከፍሎ የነበረው ይሻራል። ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፥ እንደ ልጅም አስብ ነበር፥ እንደ ልጅም እቍኦጥር ነበር፤ ጎልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬአለሁ። ዛሬስ በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደ ታወቅሁ አውቃለሁ። እንዲህም ከሆነ፥ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።

1 ቆሮንቶስ 13:1-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በሰዎችም ሆነ በመላእክት ቋንቋ የመናገር ችሎታ ቢኖረኝ እንኳ ፍቅር ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሿሿ ጸናጽል መሆኔ ነው። ትንቢት የመናገር ስጦታ ቢኖረኝና ምሥጢርንም ሁሉ ብረዳ፥ ዕውቀትም ሁሉ ቢኖረኝ፥ ተራራን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚያፈልስ እምነትም ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ያለኝን ሁሉ ለድኾች ባካፍል፥ ሥጋዬም እንኳ ሳይቀር በእሳት እንዲቃጠል አሳልፌ ብሰጥ፥ ፍቅር ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። ፍቅር ያስታግሣል፤ ፍቅር ደግ ያደርጋል፤ ፍቅር ቀናተኛ አያደርግም፤ ፍቅር ያለው ሰው አይመካም፤ ፍቅር ያለው ሰው አይታበይም፤ ፍቅር ሥርዓተቢስ አያደርግም፤ ፍቅር ያለው ሰው የራሱን ጥቅም ብቻ አይፈልግም፤ ፍቅር ያለው ሰው አይበሳጭም፤ ፍቅር ያለው ሰው ቢበደልም በደልን እንደ በደል አይቈጥርም፤ ፍቅር ያለው ሰው እውነት በሆነ ነገር ይደሰታል እንጂ ትክክል ባልሆነ ነገር አይደሰትም፤ ፍቅር ያለው ሰው ሁሉን ይችላል፤ በሁሉም ላይ እምነቱን ይጥላል፤ በሁሉም ላይ ተስፋ ያደርጋል፤ በሁሉ ነገር ይጸናል። ፍቅር ያለው ሰው ምንጊዜም አይወድቅም፤ ትንቢትን የመናገር ስጦታ ያልፋል፤ በተለያዩ ቋንቋዎች የመናገር ችሎታ ያልፋል፤ ዕውቀትም ቢሆን ያልፋል። የምናውቀውም ሆነ ትንቢት የምንናገረው በከፊል ነው። ነገር ግን ፍጹም የሆነው ነገር ሲመጣ ከፊል የሆነው ነገር ይሻራል። ሕፃን በነበርኩ ጊዜ እንደ ሕፃን እናገር ነበር፤ እንደ ሕፃን አስብ ነበር፤ እንደ ሕፃን እመራመር ነበር፤ ሙሉ ሰው በሆንኩ ጊዜ ግን የሕፃንነቴን ጠባይ ተውኩ። አሁን በመስተዋት እንደምናየው ዐይነት በድንግዝግዝ እናያለን፤ በዚያን ጊዜ ግን በግልጥ እናያለን፤ አሁን የማውቀው በከፊል ነው፤ በዚያን ጊዜ ግን እግዚአብሔር እኔን የሚያውቀኝን ያኽል ሙሉ ዕውቀት ይኖረኛል። እንግዲህ እምነት፥ ተስፋ፥ ፍቅር፥ እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ነገር ግን ከእነዚህ መካከል የሚበልጠው ፍቅር ነው።

1 ቆሮንቶስ 13:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር፥ ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሿሿ ጸናጽል ነኝ። ትንቢት የመናገር ስጦታ ቢኖረኝ፥ ምስጢርን ሁሉ ባውቅ፥ ዕውቀትን ሁሉ ብረዳ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ። ያለኝን ሁሉ ለድኾች ባካፍል፥ ሰውነቴንም እንዲቃጠል ለእሳት አሳልፌ ብሰጥ፥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም። ፍቅር ይታገሳል፤ ቸርነትንም ያደርጋል። ፍቅር አይቀናም፤ አይመካም፤ አይታበይም፤ ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፤ ራስ ወዳድ አይደለም፤ አይበሳጭም፥ በደልን አይቆጥርም። ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ በዐመፅ ደስ አይሰኝም። ፍቅር ሁሉን ይታገሣል፤ ሁሉን ያምናል፤ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፤ በሁሉ ነገር ይጸናል። ፍቅር ከቶ አይወድቅም፤ ትንቢት የመናገር ስጦታም ቢሆን ይሻራል፤ ልሳንም ቢሆን ይቀራል፤ ዕውቀትም ቢሆን ያልፋል። ምክንያቱም የምናውቀው በከፊል ነው፤ ትንቢት የምንናገረውም በከፊል ነው። ነገር ግን ፍጹም የሆነው ሲመጣ በከፊል የነበረው ይሻራል። ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፤ እንደ ልጅ አስብ ነበር፤ እንደ ልጅም አሰላስል ነበር። ሙሉ ሰው በሆንኩ ጊዜ ግን የልጅነትን ጠባይ ትቻለሁ። አሁን የምናየው በመስተዋት ውስጥ እንደሚታይ በድንግዝግዝ ነው፤ በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን። አሁን የማውቀው በከፊል ነው፤ በዚያን ጊዜ እኔ ራሴ ሙሉ በሙሉ የታወቅሁትን ያህል ዐውቃለሁ። እንግዲህ እምነት፥ ተስፋ፥ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።

1 ቆሮንቶስ 13:1-13

1 ቆሮንቶስ 13:1-13 NASV1 ቆሮንቶስ 13:1-13 NASV1 ቆሮንቶስ 13:1-13 NASV1 ቆሮንቶስ 13:1-13 NASV