1 ዜና መዋዕል 13:1-14

1 ዜና መዋዕል 13:1-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ዳዊ​ትም ከሻ​ለ​ቆ​ችና ከመቶ አለ​ቆች፥ ከአ​ለ​ቆ​ቹም ሁሉ ጋር ተማ​ከረ። ዳዊ​ትም የእ​ስ​ራ​ኤ​ልን ጉባኤ ሁሉ፥ “መል​ካም መስሎ የታ​ያ​ችሁ እንደ ሆነ፥ አም​ላ​ካ​ችን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ፈቅዶ እንደ ሆነ፥ በእ​ስ​ራ​ኤል ሀገር ሁሉ ለቀ​ሩት ወን​ድ​ሞ​ቻ​ችን በከ​ተ​ሞ​ቻ​ቸ​ውና በመ​ሰ​ማ​ሪ​ያ​ዎ​ቻ​ቸው ለሚ​ቀ​መጡ ካህ​ና​ትና ሌዋ​ው​ያን ወደ እኛ ይሰ​በ​ሰቡ ዘንድ እን​ላክ። ከሳ​ኦ​ልም ዘመን ጀምሮ አል​ፈ​ለ​ጓ​ት​ምና የአ​ም​ላ​ካ​ችን የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ታቦት ወደ እኛ እን​መ​ል​ሳት” አላ​ቸው። ነገ​ሩም በሕ​ዝቡ ሁሉ ዐይን ዘንድ ቅን ነበ​ረና የእ​ስ​ራ​ኤል ጉባኤ ሁሉ፥ “እን​ዲሁ እና​ደ​ር​ጋ​ለን” አሉ። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም ታቦት ከቂ​ር​ያ​ት​ይ​ዓ​ሪም ያመጡ ዘንድ ዳዊት እስ​ራ​ኤ​ልን ሁሉ ከግ​ብፅ ዳርቻ ጀምሮ እስከ ኤማት መግ​ቢያ ድረስ ሰበ​ሰበ። ዳዊ​ትም፥ እስ​ራ​ኤ​ልም ሁሉ በኪ​ሩ​ቤል ላይ የተ​ቀ​መ​ጠ​ውን፥ ስሙም በእ​ር​ስዋ የተ​ጠ​ራ​ባ​ትን የአ​ም​ላ​ክን የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ታቦት ከዚያ ያወጡ ዘንድ በይ​ሁዳ ወዳ​ለ​ችው ቂር​ያ​ት​ይ​ዓ​ሪም ሄዱ። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም ታቦት ከአ​ሚ​ና​ዳብ ቤት በተ​ገኘ በአ​ዲስ ሰረ​ገላ ላይ አኖ​ሩ​አት። ዖዛና ወን​ድ​ሞ​ቹም ሰረ​ገ​ላ​ውን ይነዱ ነበር። ዳዊ​ትና እስ​ራ​ኤል ሁሉ ከመ​ዘ​ም​ራን ጋር በበ​ገና፥ በመ​ሰ​ን​ቆና በከ​በሮ፥ በጸ​ና​ጽ​ልና በመ​ለ​ከት በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት በሙሉ ኀይ​ላ​ቸው ይዘ​ምሩ ነበር። ወደ አው​ድማ ዳርም በደ​ረሱ ጊዜ ላሞቹ ሰረ​ገ​ላ​ውን ሲስቡ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ታቦት ዘን​በል ብላ​ለ​ችና ታቦ​ቷን ሊይዝ ዖዛ እጁን ዘረጋ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በዖዛ ላይ ተቈጣ። እጁ​ንም ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ታቦት ስለ ዘረጋ ቀሠ​ፈው፤ በዚ​ያም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ሞተ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ዖዛን ስለ ሰበ​ረው ዳዊት አዘነ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የዚ​ያን ስፍራ ስም “የዖዛ ስብ​ራት” ብሎ ጠራው። በዚ​ያም ቀን ዳዊት፥ “የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ታቦት ወደ እኔ እን​ዴት አመ​ጣ​ለሁ?” ብሎ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ፈራ። ዳዊ​ትም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ታቦት ወደ ጌት ሰው ወደ አቢ​ዳራ ቤት አሳ​ለ​ፋት እንጂ ወደ እርሱ ወደ ዳዊት ከተማ አላ​መ​ጣ​ትም። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ታቦት በጌት ሰው በአ​ቢ​ዳራ ቤት ውስጥ ሦስት ወር ተቀ​መ​ጠች፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም አቢ​ዳ​ራ​ንና ቤተ ሰቡን ሁሉ ባረከ።

1 ዜና መዋዕል 13:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ዳዊትም ሻለቆችና መቶ አለቆች ከሆኑት የጦር ሹማምቱ ሁሉ ጋራ ተማከረ። ከዚያም ለመላው የእስራኤል ማኅበር እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ ነገሩ መልካም መስሎ ከታያችሁና የአምላካችን የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነ፣ በእስራኤል ግዛት ሁሉ ለሚኖሩ በሩቅም ሆነ በቅርብ ላሉት ለቀሩት ወንድሞቻችን እንዲሁም በየራሳቸው ከተሞችና መሰማሪያዎች የሚኖሩ ካህናትና ሌዋውያን መጥተው ከእኛ ጋራ እንዲሰባሰቡ እንላክባቸው። በሳኦል ዘመነ መንግሥት ሳንፈልገው የነበረውን የአምላካችንን ታቦት መልሰን ወደ እኛ እናምጣ”። ነገሩም በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ ተቀባይነት ስላገኘ መላው ማኅበር ይህንኑ ለማድረግ ተስማማ። ስለዚህ ዳዊት የእግዚአብሔርን ታቦት ከቂርያትይዓይሪም ለማምጣት ከግብጽ ወንዝ ከሺሖር ጀምሮ እስከ ለቦ ሐማት ድረስ የሰፈሩትን እስራኤላውያን ሁሉ ሰበሰበ። ዳዊትና እስራኤላውያን ሁሉ በኪሩብና በኪሩብ መካከል የተቀመጠውን ስሙም በርሱ የተጠራውን፣ የእግዚአብሔር አምላክን ታቦት ከዚያ ለማምጣት በይሁዳ ወዳለችው ቂርያትይዓይሪም ወደተባለችው ወደ በኣላ ሄዱ። የእግዚአብሔርንም ታቦት ከአሚናዳብ ቤት በአዲስ ሠረገላ ላይ አድርገው አመጡት፤ ሠረገላውን ይነዱ የነበሩትም ዖዛና አሒዮ ነበሩ። ዳዊትና እስራኤላውያን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ሆነው በቅኔና በበገና፣ በመሰንቆና በከበሮ፣ በጸናጽልና በመለከት በሙሉ ኀይላቸው በዓሉን በደስታ ያከብሩ ነበር። ወደ ኪዶን ዐውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ አደናቅፏቸው ስለ ነበር፣ ዖዛ ታቦቱን ለመደገፍ እጁን ዘረጋ። ታቦቱን በእጁ ስለ ነካ፣ የእግዚአብሔር ቍጣ በዖዛ ላይ ነደደ፤ ስለዚህም በዚያው በእግዚአብሔር ፊት ሞተ። የእግዚአብሔር ቍጣ ዖዛን በድንገት ስለ ቀሠፈው ዳዊት ዐዘነ፤ ያም ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ የፔሬዝ ዖዛ ስብራት ተብሎ ይጠራል። ዳዊት በዚያ ዕለት እግዚአብሔርን ስለ ፈራ፣ “ታዲያ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እኔ እንዴት ማምጣት እችላለሁ?” አለ። ስለዚህ ታቦቱን ወደ ዳዊት ከተማ በመውሰድ ፈንታ የጋት ሰው ወደ ሆነው ወደ አቢዳራ ቤት ወሰደው። የእግዚአብሔርንም ታቦት በአቢዳራ ቤት ከቤተ ሰቡ ጋራ ሦስት ወር ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርም ቤተ ሰቡንና ያለውንም ሁሉ ባረከ።

1 ዜና መዋዕል 13:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ዳዊትም ከሻለቆችና ከመቶ አለቆች ከአለቆቹም ሁሉ ጋር ተማከረ። ዳዊትም የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ “መልካም መስሎ የታያችሁ እንደ ሆነ፥ ከአምላካችን ከእግዚአብሔርም ወጥቶ እንደ ሆነ፥ በእስራኤል አገር ሁሉ ለቀሩት ወንድሞቻችን በከተሞቻቸውና በመሰማርያዎቻቸውም ለሚቀመጡ ካህናትና ሌዋውያን ወደ እኛ ይሰበሰቡ ዘንድ እንላክ፤ በሳኦልም ዘመን አልፈለግነውምና የአምላካችንን ታቦት ወደ እኛ እንመልስ፤” አላቸው። ነገሩም በሕዝቡ ሁሉ ዐይን ዘንድ ቅን ነበረና ጉባኤው ሁሉ “እንዲሁ እናደርጋለን፤” አሉ። የእግዚአብሔርንም ታቦት ከቂርያትይዓሪም ያመጡ ዘንድ ዳዊት እስራኤልን ሁሉ ከግብጽ ወንዝ ከሺሆር ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ ሰበሰበ። ዳዊትም እስራኤልም ሁሉ በኪሩቤል ላይ የተቀመጠውን ስሙም በእርሱ የተጠራውን የአምላክን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ያወጡ ዘንድ በይሁዳ ወዳለችው ቂርያትይዓሪም ወደ ተባለች ወደ በኣላ ሄዱ። የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሠረገላ ላይ ጫኑት፤ ከአሚናዳብም ቤት አመጡት፤ ዖዛና አሒዮም ሠረገላውን ይነዱ ነበር። ዳዊትና እስራኤል ሁሉ በቅኔና በበገና በመሰንቆና በከበሮ በጸናጸልና በመለከት በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኀይላቸው ይጫወቱ ነበር። ወደ ኪዶንም አውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ ይፋንኑ ነበርና ታቦቱን ሊይዝ ዖዛ እጁን ዘረጋ። የእግዚአብሔርም ቍጣ በዖዛ ላይ ነደደ፤ እጁንም ወደ ታቦቱ ስለዘረጋ ቀሠፈው፤ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ሞተ። እግዚአብሔርም ዖዛን ስለ ቀሠፈው ዳዊት አዘነ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የዚያን ስፍራ ስም “የዖዛ ስብራት” ብሎ ጠራው። በዚያም ቀን ዳዊት “የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እኔ እንዴት አመጣለሁ?” ብሎ እግዚአብሔርን ፈራ። ዳዊትም ታቦቱን ወደ ጌት ሰው ወደ አቢዳራ ቤት አሳለፈው እንጂ ወደ እርሱ ወደ ዳዊት ከተማ አላመጣውም። የእግዚአብሔርም ታቦት በአቢዳራ ቤተ ሰብ ዘንድ በቤቱ ውስጥ ሦስት ወር ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርም የአቢዳራን ቤትና ያለውን ሁሉ ባረከ።

1 ዜና መዋዕል 13:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ንጉሥ ዳዊት የሻለቅነትና የመቶ አለቅነት ማዕርግ ካላቸው የጦር አለቆች ጋር ተመካከረ፤ ከዚያም በኋላ ለመላው የእስራኤል ሕዝብ እንዲህ ሲል አስታወቀ፥ “እናንተ ከተስማማችሁበትና የአምላካችን የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነ፥ የቀሩት የአገራችን ሰዎች፥ ካህናትና ሌዋውያን ወደሚኖሩባቸው ታናናሽ ከተማዎች መልእክተኞች ልከን ወደዚህ መጥተው ከእኛ ጋር እንዲሰበሰቡ እንንገራቸው፤ በሳኦል ዘመነ መንግሥት ችላ ብለነው የነበረውንም የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ሄደን እናመጣለን።” ሕዝቡም በሐሳቡ ደስ በመሰኘት ተስማሙ። ስለዚህም ዳዊት የቃል ኪዳኑን ታቦት ከቂርያትይዓሪም ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት በደቡብ በኩል እስከ ግብጽ ግዛት ድንበር፥ በሰሜን እስከ ሐማት መተላለፊያ ድረስ በመላው እስራኤል የሚገኘውን ሕዝብ በአንድነት ሰበሰበ። ዳዊትና ሕዝቡ ሁሉ በኪሩቤል ክንፎች ላይ የተቀመጠውን፥ በእግዚአብሔር ስም የተጠራውን የአምላካቸውን የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ያመጡ ዘንድ በይሁዳ ግዛት ባዓላ ተብላ ወደምትጠራው ወደ ቂርያትይዓሪም ከተማ ሄዱ፤ የቃል ኪዳኑን ታቦት ከአቢናዳብ ቤት አውጥተው በአዲስ ሠረገላ ላይ ጫኑት፤ ዑዛና አሕዮም ሠረገላውን ይነዱ ነበር፤ ዳዊትና እስራኤላውያን ሁሉ መሰንቆና በገና እየደረደሩ፥ አታሞ እየመቱ፥ ጸናጽል እያንሿሹና እምቢልታ እየነፉ በመዘመር በሙሉ ኀይላቸው ለእግዚአብሔር ክብር ያሸበሽቡ ነበር። ወደ ኪዶንም አውድማ በደረሱ ጊዜ ሠረገላውን የሚጐትቱት በሬዎች ሲፋንኑ አደናቀፋቸው፤ ዑዛም እጆቹን ዘርግቶ የቃል ኪዳኑን ታቦት በመደገፍ ያዘ፤ ዑዛ ታቦቱን በመንካቱ እግዚአብሔር ተቈጥቶ ወዲያውኑ በሞት ቀሠፈው፤ ስለዚህም ዑዛ በዚያው በእግዚአብሔር ፊት ሞተ፤ ያም ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ “ፔሬጽ ዑዛ” ተብሎ ይጠራል፤ እግዚአብሔር ተቈጥቶ ዑዛን ስለ ገደለው ዳዊት እጅግ ተበሳጨ። ከዚህ በኋላ ዳዊት እግዚአብሔርን እጅግ ስለ ፈራ “እንግዲህ ይህን የቃል ኪዳን ታቦት ወደ ቤቴ እንዴት መውሰድ እችላለሁ?” አለ፤ ስለዚህም ዳዊት ታቦቱን ወደ ኢየሩሳሌም በመውሰድ ፈንታ የጋት ከተማ ነዋሪ በሆነው፥ ዖቤድኤዶም ተብሎ በሚጠራው ሰው ቤት ተወው። ታቦቱም በዚያ ሦስት ወር ቈየ፤ እግዚአብሔርም የዖቤድኤዶምን ቤተሰብና የእርሱ የሆነውን ነገር ሁሉ ባረከ።

1 ዜና መዋዕል 13:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ዳዊትም ከሻለቆችና ከመቶ አለቆች ከሹማምንቱም ሁሉ ጋር ተማከረ። ዳዊትም የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ እንዲህ አላቸው፦ “መልካም መስሎ ቢታያችሁ፥ የጌታም የአምላካችን ፈቃድ ቢሆን፥ በእስራኤል አገር ሁሉ ለቀሩት ወንድሞቻችን በከተሞቻቸውና በመሰማሪያዎቻቸውም ለተቀመጡት ካህናትና ሌዋውያን ወደ እኛ እንዲሰበሰቡ እንላክባቸው፤ በሳኦልም ዘመን አልፈለግነውምና የአምላካችንን ታቦት ወደ እኛ እንመልስ።” ነገሩም በሕዝቡ ሁሉ ዐይን ዘንድ ቅን ነበረና ጉባኤው ሁሉ፦ “እንዲሁ እናደርጋለን” አሉ። የእግዚአብሔርንም ታቦት ከቂርያት-ይዓሪም ለማምጣት ዳዊት እስራኤልን ሁሉ ከግብጽ ወንዝ ከሺሆር ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ ሰበሰበ። ዳዊትም እስራኤልም ሁሉ በኪሩቤል ላይ የተቀመጠውን ስሙም በእርሱ የተጠራውን የጌታን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ለማምጣት በይሁዳ ወዳለችው ቂርያት-ይዓሪም ወደተባለች ወደ በኣላ ሄዱ። የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሠረገላ ላይ ጫኑት፥ ከአሚናዳብም ቤት አመጡት፤ ዖዛና አሒዮም ሠረገላውን ይነዱ ነበር። ዳዊትና እስራኤል ሁሉ በዝማሬና በበገና በመሰንቆና በከበሮ በጸናጸልና በመለከት በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ያሸበሽቡ ነበር። ወደ ኪዶንም አውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ ይፋንኑ ነበርና ታቦቱን ሊይዝ ዖዛ እጁን ዘረጋ። የጌታም ቁጣ በዖዛ ላይ ነደደ፥ እጁንም ወደ ታቦቱ ስለዘረጋ ቀሠፈው፤ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ሞተ። ጌታም ዖዛን ስለ ቀሠፈው ዳዊት አዘነ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የዚያን ስፍራ ስም የዖዛ-ስብራት ብሎ ጠራው። በዚያም ቀን ዳዊት፦ “የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እኔ እንዴት አመጣለሁ?” ብሎ እግዚአብሔርን ፈራ። ዳዊትም ታቦቱን ወደ ጌት ሰው ወደ አቢ-ዳራ ቤት ወሰደው እንጂ ወደ እርሱ ወደ ዳዊት ከተማ አላመጣውም። የእግዚአብሔርም ታቦት በአቢ-ዳራ ቤተሰብ ዘንድ በቤቱ ውስጥ ሦስት ወር ተቀመጠ፤ ጌታም የአቢ-ዳራን ቤትና ያለውን ሁሉ ባረከ።