የማቴዎስ ወንጌል 15:22-37

የማቴዎስ ወንጌል 15:22-37 አማ54

እነሆም፥ ከነናዊት ሴት ከዚያ አገር ወጥታ፦ ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረኝ፤ ልጄን ጋኔን ክፉኛ ይዞአታል ብላ ጮኸች። እርሱ ግን አንዳች አልመለሰላትም። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፦ በኋላችን ትጮኻለችና አሰናብታት እያሉ ለመኑት። እርሱም መልሶ፦ ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በቀር አልተላክሁም አለ። እርስዋ ግን መጥታ፦ ጌታ ሆይ፥ እርዳኝ እያለች ሰገደችለት። እርሱ ግን መልሶ፦ የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባም አለ። እርስዋም፦ አዎን ጌታ ሆይ፤ ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ አለች። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ፦ አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደወደድሽ ይሁንልሽ አላት። ልጅዋም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች። ኢየሱስም ከዚያ አልፎ ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ መጣ፥ ወደ ተራራም ወጥቶ በዚያ ተቀመጠ። ብዙ ሕዝብም አንካሶችን፥ ዕውሮችንም፥ ዲዳዎችንም፥ ጉንድሾችንም፥ ሌሎችንም ብዙ ይዘው ወደ እርሱ ቀረቡ፥ በኢየሱስም እግር አጠገብ ጣሉአቸው፤ ፈወሳቸውም፤ ስለዚህም ሕዝቡ ዲዳዎች ሲናገሩ፥ ጉንድሾችም ሲድኑ፥ አንካሶችም ሲሄዱ፥ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ፦ ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለ ሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤ በመንገድም እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልወድም አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም፦ ይህን ያህል ሕዝብ የሚያጠግብ ይህን ያህል እንጀራ በምድረ በዳ ከወዴት እናገኛለን? አሉት። ኢየሱስም፦ ስንት እንጀራ አላችሁ? አላቸው። እነርሱም፦ ሰባት፥ ጥቂትም ትንሽ ዓሣ አሉት። ሕዝቡም በምድር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ ሰባቱንም እንጀራ ዓሣውንም ይዞ አመሰገነ ቍኦርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ። ሁሉም በሉና ጠገቡ፥ የተረፈውንም ቁርስራሽ ሰባት ቅርጫት ሙሉ አነሡ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች