በዚያን ዘመን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ለእስራኤል ወገኖች ሁሉ አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እስራኤል ማረፊያ ሊሻ በሄደ ጊዜ ከሰይፍ የተረፈው ሕዝብ በምድረ በዳ ሞገስ አገኘ። እግዚአብሔርም ከሩቅ ተገለጠልኝ እንዲህም አለኝ፦ በዘላለም ፍቅር ወድጄሻለሁ፥ ስለዚህ በቸርነት ሳብሁሽ። የእስራኤል ድንግል ሆይ፥ እንደ ገና እሠራሻለሁ አንቺም ትሠሪያለሽ፥ እንደ ገናም ከበሮሽን አንሥተሽ ከዘፋኞች ጋር ወደ ዘፈን ትወጫለሽ። እንደ ገናም በሰማርያ ተራሮች ላይ የወይን ቦታዎችን ትተክሊአለሽ፥ አትክልተኞች ይተክላሉ በፍሬውም ደስ ይላቸዋል። በኤፍሬምም ተራሮች ላይ ያሉ ጠባቆች፦ ተነሡ፥ ወደ ጽዮን ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር እንውጣ ብለው የሚጮኹበት ቀን ይመጣልና። እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ስለ ያዕቆብ ደስ ይበላችሁ ስለ አሕዛብም አለቆች እልል በሉ፥ አውሩ፥ አመስግኑ፦ እግዚአብሔር ሕዝቡን የእስራኤልን ቅሬታ አድኖአል በሉ። እነሆ፥ ከሰሜን አገር አመጣቸዋለሁ፥ ከምድርም ዳርቻ እሰበስባቸዋለሁ፥ በመካከላቸውም ዕውሩና አንካሳው ያረገዘችና የወለደችም በአንድነት፥ ታላቅ ጉባኤ ሆነው ወደዚህ ይመለሳሉ። በልቅሶ ወጡ እኔም በማጽናናት አመጣቸዋለሁ፥ በወንዝ ዳር በቅን መንገድ አስኬዳቸዋለሁ፥ በእርሱም አይሰናከሉም፥ እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና፥ ኤፍሬምም በኵሬ ነውና። አሕዛብ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፥ በሩቅም ላሉ ደሴቶች አውሩና፦ እስራኤልን የበተነ እርሱ ይሰበስበዋል፥ እረኛም መንጋውን እንደሚጠብቅ ይጠብቀዋል በሉ። እግዚአብሔር ያዕቆብን ተቤዥቶታል፥ ከበረቱበትም እጅ አድኖታል። ይመጣሉ በጽዮንም ተራራ እልል ይላሉ፥ ወደ እግዚአብሔርም በጎነት፥ ወደ እህልና ወደ ወይን ጠጅ ወደ ዘይትም፥ ወደ በጎችና ወደ ላሞች ይሰበሰባሉ፥ ነፍሳቸውም እንደ ረካች ገነት ትሆናለች፥ ከእንግዲህም ወዲህ አያዝኑም። በዚያን ጊዜም ድንግሊቱ በዘፈን ደስ ይላታል፥ ጐበዛዝቱና ሽማግሌዎቹም በአንድ ላይ ደስ ይላቸዋል፥ ልቅሶአቸውንም ወደ ደስታ እመልሳለሁ፥ አጽናናቸውማለሁ፥ ከኅዘናቸውም ደስ አሰኛቸዋለሁ። የካህናቱንም ነፍስ በብዛት አረካታለሁ ሕዝቤም በጎነቴን ይጠግባል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የዋይታና የመራራ ልቅሶ ድምፅ በራማ ተሰማ፥ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፥ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ድምፅሽን ከልቅሶ ዓይንሽንም ከእንባ ከልክዪ፥ ለሥራሽ ዋጋ ይሆናልና፥ ከጠላትም ምድር ይመለሳሉ። ለፍጻሜሽም ተስፋ አለ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ልጆችሽም ወደ ዳርቻቸው ይመለሳሉ። ኤፍሬም፦ ቀጣኸኝ እኔም እንዳልተገራ ወይፈን ተቀጣሁ፥ አንተ እግዚአብሔር አምላኬ ነህና መልሰኝ እኔም እመለሳለሁ። ከተመለስሁ በኋላ ተጸጸትሁ፥ ከተገሠጽሁም በኋላ ጭኔን ጸፋሁ፥ የብላቴንነቴንም ስድብ ተሸክሜአለሁና አፈርሁ፥ ተዋረድሁም ብሎ ሲያለቅስ ሰማሁ። በእውነት ኤፍሬም ለእኔ የከበረ ልጅ ነውን? ወይስ የተወደደ ሕፃን ነውን? በእርሱ ላይ በተናገርሁ ቍጥር አስበዋለሁ፥ ስለዚህ አንጀቴ ታወከችለት ርኅራኄም እራራለታለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። ለራስሽ የመንገድ ምልክት አድርጊ፥ መንገድንም የሚመሩ ዓምዶችን ትከዪ፥ ልብሽንም ወደ ሄድሽበት መንገድ ወደ ጥርጊያው አቅኚ፥ አንቺ የእስራኤል ድንግል ሆይ፥ ተመለሺ፥ ወደ እነዚህም ወደ ከተሞችሽ ተመለሺ። አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ፥ እስከ መቼ ትቅበዘበዣለሽ? እግዚአብሔር በምድር ላይ አዲስ ነገር ፈጥሮአልና ሴት ወንድን ትከብባለች።
ትንቢተ ኤርምያስ 31 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኤርምያስ 31:1-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች