እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ሣራን አሰበ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ለሣራ አደረገላት። ሣራም ፀነሰች እግዚአብሔርም በተናገረው ወራት ለአብርሃም በእርጅናው ወንድ ልጅን ወለደችለት። አብርሃምም የተወለደለትን ሣራ የወለደችለትን የልጁን ስም ይስሐቅ ብሎ ጠራው። አብርሃምም ልጁን ይስሐቅን እግዚአብሔር እንዳዘዘው በስምንተኛ ቀን ገረዘው። አብርሃምም ልጁ ይስሐቅ በተወለደለት ጊዜ የመቶ ዓመት ዕድሜ ነበረ። ሣራም እግዚአብሔር ሳቅ አድርጎልኛል፤ ይህንንም የሚሰማ ሁሉ በእኔ ምክንያት ይስቃል አለች። ደግሞም፥ ሣራ ልጆችን እንድታጠባ ለአብርሃም ማን በነገረው? በእርጅናው ልጅን ወልጄለታለሁና አለች። ሕፃኑም አደገ ጡትንም ከመጥባት ተቋረጠ፤ አብርሃምም ይስሐቅን ጡት ባስጣለበት ቀን ትልቅ ግብዣን አደረገ። ሣራም ግብፃዊቱ አጋር ለአብርሃም የወለደችለትን ልጅ ሲስቅ አየችው። አብርህምንም፤ ይህችን ባሪያ ከነልጅዋ አሳድድ የዚህች ባሪያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር አይወርስምና አለችው። ይህም ነገር በአብርሃም ዘንድ ስለ ልጁ እጅግ ችግር ሆነበት። እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው ስለ ባሪያህና ስለ ብላቴናው አትዘን፤ ሣራም የምትነግርህን ቃል ሁሉ ስማ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃልና። የባሪያይቱን ልጅ ደግሞ ሕዝብ አደርገዋለሁ ዘርህ ነውና። አብርሃምም ማልዶ ተነሣ እንጀራንም ወሰደ የውኃ አቁማዳንም ለአጋር በትክሻው አሸከማት ብላቴናውንም ሰጥቶ አስወጣት እርስዋም ሄደች በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ተቀበዘበዘች። ውኃውም ከአቁማዳው አለቀ፤ ብላቴናውንም ከአንድ ቍጥቋጦ በታች ጣለችው እርስዋም ሄደች፥ ብላቴናው ሲሞት አልየው ብላ ቀስት ተወርውሮ የሚደርስበትን ያህል ርቃ በአንጻሩ ተቀመጠች። ፊት ለፊትም ተቀመጠች ቃልዋንም አሰምታ አለቀሰች። እግዚአብሔርም የብላቴናውን ድምፅ ሰማ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ ሲል ጠራት፥ አጋር ሆይ ምን ሆንሽ? እግዚአብሔር የብላቴናውን ድምፅ ባለበት ስፍራ ሰምቶአልና አትፍሪ። ተነሺ፥ ብላቴናውንም አንሺ፥ እጅሽንም በእርሱ አጽኚው ትልቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና። እግዚአብሔርም ዓይንዋን ከፈተላት የውኃ ጕድጓድንም አየች ሄዳም አቁማዳውን በውኃ ሞላች ብላቴናውንም አጠጣች። እግዚአብሔርም ከብላቴናው ጋር ነበረ፤ አደገም በምድረ በዳም ተቀመጠ፥ ቀስተኛም ሆነ። በፋራን ምድረ በዳም ተቀመጠ፤ እናቱም ከምድረ ግብፅ ሚስት ወሰደችለት። በዚያም ዘመን አቢሜሌክ ከሙሽራው ወዳጅ ከአኮዘትና ከሠራዊቱ አለቃ ከፊኮል ጋር አብርሃምን አለው፤ በምታደርገው ሁሉ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፤ አሁንም በእኔም በልጄም በልጅ ልጄም ክፉ እንዳታደርግብኝ በእግዚአብሔር ማልልኝ፤ ነገር ግን ለአንተ ቸርነትን እንዳደረግሁ አንተም ለእኔ ለተቀመጥህባትም ምድር ቸርነትን ታደርጋለህ። አብርሃምም፦ እኔ እምላለሁ አለ። አቢሜሌክንም ባሪያዎቹ በነጠቁት በውኃ ጕድጓድ ምክንያት አብርሃም ወቀሰው። አቢሜሌክም አለ፦ ይህን ነገር ያደረገውን አላውቅሁም፤ አንተም ደግሞ ምንም አልነገርኸኝም፥ እኔም ከዛሬ በቀር አልሰማሁም። አብረሃምም በጎችንና ላሞችን አምጥቶ ለአቤሜሌክ ሰጠው፤ ሁለቱም ቃል ኪዳን አደረጉ። አብረሃምም ሰባት ቄቦች በጎችን ለብቻቸው አቆመ። አቢሜሌክም አብረሃምን፦ ለብቻቸው ያቆምሃቸው እነዚህ ስባት ቄቦች በጎች ምንድር ናቸው? አለው። እርሱም፦ እኔ ይህችን የውኃ ጕድጓድ እንደቆፈርሁ ምስክር ይሆንልኝ ዘንድ እነዚህን ሰባት ቄቦች በጎች ከእጄ ትወስዳለህ አለው። ስለዚህ የዚያን ስፍራ ስም ቤርሳቤህ ብሎ ጠራው፤ ከዚያ ሁለቱ ተማምልዋልና። በቤርሳቤህም ቃል ኪዳንን አደረጉ። አቢሜሌክና የሙሽራው ወዳጅ አኮዘት የሠራዊቱ አለቃ ፊኮልም ተነስተው ወደ ፍልስጥኤም ምድር ተመለሱ። አብረሃምም በቤርሳቤህ የተምር ዛፍን ተከለ፤ በዚያም የዘላለሙን አምላክ የእግዚአብሔርን ስም ጠራ። አብርሃምም በፍልስጥኤም ምድር ብዙ ቀን እንግዳ ሆኖ ተቀመጠ።
ኦሪት ዘፍጥረት 21 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 21:1-34
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች