መጽሐፈ ዕዝራ 6:13-22

መጽሐፈ ዕዝራ 6:13-22 አማ54

ንጉሡም ዳርዮስ እንደ ላከው ቃል፥ በዚያን ጊዜ በወንዝ ማዶ ያለ ገዥ ተንትናይ፥ ደግሞ ሰተርቡዝናይ እና ተባባሪዎቻቸው እንዲሁ ተግተው አደረጉ። የአይሁድም ሽማግሌዎች በነቢዩ በሐጌና በአዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት ሠሩ፤ ተከናወነላቸውም። እንደ እስራኤል አምላክ ትእዛዝ፥ እንደ ፋርስም ነገሥታት እንደ ቂሮስ፥ እንደ ዳርዮስና እንደ አርጤክስስ ትእዛዝ ሠርተው ፈጸሙ። ይህም ቤት በንጉሡ በዳርዮስ መንግሥት በስድስተኛው ዓመት አዳር በሚባል ወር በሦስተኛው ቀን ተፈጸመ። የእስራኤልም ልጆች፥ ካህናትና ሌዋውያን፥ የቀሩትም ምርኮኞች፥ የዚህን የእግዚአብሔርን ቤት ቅዳሴ በደስታ አደረጉ። በዚህም በእግዚአብሔር ቤት ቅዳሴ መቶ ወይፈኖችና ሁለት መቶ አውራ በጎች፥ አራት መቶም ጠቦቶች አቀረቡ፤ ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት እንደ እስራኤል ነገዶች ቍጥር ለእስራኤል ሁሉ አሥራ ሁለት አውራ ፍየሎች አቀረቡ። በሙሴም መጽሐፍ እንደ ተጻፈው በኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር አገልግሎት ላይ ካህናቱን በየማዕርጋቸው፥ ሌዋውያኑንም በየክፍላቸው አቆሙ። ምርኮኞቹም በመጀመሪያው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አደረጉ። ካህናቱና ሌዋውያኑም አንድ ሆነው ነጽተው ነበር፤ ሁሉም ንጹሐን ነበሩ፤ ለምርኮኞቹም ሁሉ፥ ለወንድሞቻቸውም ለካህናቱ፥ ለራሳቸውም የፋሲካውን በግ አረዱ። ከምርኮም ተመልሰው የመጡት የእስራኤል ልጆች፥ የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ ራሳቸውን ከምድር አሕዛብ ርኵሰት ለይተው ወደ እነርሱ መጥተው የነበሩት ሁሉ በሉ፤ እግዚአብሔር ደስ አሰኝቶአቸዋልና፥ የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት እጃቸውን ያጸና ዘንድ የአሦርን ንጉሥ ልብ ወደ እነርሱ መልሶአልና የቂጣውን በዓል ሰባት ቀን በደስታ አደረጉ።