ኦሪት ዘጸአት 35:4-29

ኦሪት ዘጸአት 35:4-29 አማ54

ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ማህበር ሁሉ አላቸው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ያዘዘው ነገር ይህ ነው፤ ከእናንተ ዘንድ ለእግዚአብሔር ቁርባንን አቅርቡ፤ የልብ ፈቃድ ያለው የእግዚአብሔርን ቁርባን ያምጣ፤ ወርቅና ብርም ናስም፤ ሰማያዊም ሐምራዊም ቀይ ግምጃም፥ ጥሩ በፍታም፥ የፍየል ጠጉርም፤ ቀይም የአውራ በግ ቁርበት፥ የአቆስጣም ቁርበት፥ የግራርም እንጨት፤ ለመብራትም ዘይት፥ ለቅብዓት ዘይትና ለጣፋጭ ዕጣን ቅመም፤ መረግድ ለኤፉዱና ለደረት ኪስ የሚደረግ ፈርጥ ያምጣ። በእናንተም ዘንድ ያሉ በልባቸው ጥበበኞች ሁሉ መጥተው እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ያድርጉ። ማደሪያውን፥ ድንኳኑንም መደረቢያውንም፥ መያዣዎቹንም፥ ሳንቆቹንም፥ መወርወሪያዎቹንም፥ ምሰሶቹንም፥ እግሮቹንም፤ ታቦቱን መሎጊያዎቹንም፥ የስርየት መክደኛውንም በእርሱም ፊት የሚሸፍነውን መጋረጃ፤ ገበታውን መሎጊያዎቹንም ዕቃውንም ሁሉ፥ የገጹንም ኅብስት፤ መብራት የሚያበሩበትን መቅረዙን ዕቃውንም፥ ቀንዲሉንም፥ የመብራቱንም ዘይት፤ የዕጣኑን መሠዊያም መሎጊያዎቹንም፥ የቅብዓቱንም ዘይት፥ ጣፋጩንም ዕጣን፥ ለማደሪያውም ደጃፍ የሚሆን የደጃፉን መጋረጃ፤ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያውን፥ የናሱንም መከታ፥ መሎጊያዎቹንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፤ የመታጠቢያውን ሰንም መቀመጫውንም፤ የአደባባዩን መጋረጆች ምሰሶቹንም እግሮቻቸውንም፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ፤ የማደሪያውን ካስማዎች፥ የአደባባዩንም ካስማዎች አውታሮቻቸውንም፤ በመቅደስ ውስጥ ለማገልገል በብልሃት የተሠሩትን ልብሶች፥ በክህነት ያገለግሉበት ዘንድ የተቀደሱትን የካህኑን የአሮን ልብሶች፥ የልጆቹንም ልብሶች። የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ከሙሴ ፊት ወጡ። ከእነርሱም ሰው ሁሉ ልቡ እንዳነሣሣው መንፈሱም እሺ እንዳሰኘው ለመገናኛው ድንኳን ሥራ ለማገልገያውም ሁሉ ለተቀደሰውም ልብስ ለእግዚአብሔር ስጦታ አመጡ። ወንዶችና ሴቶችም ልባቸው እንደ ፈቀደ ማርዳዎችን፥ ሎቲዎችንም፥ ቀለበቶችንም፥ ድሪዎችንም፥ የወርቅ ጌጦችንም ሁሉ አመጡ፤ ሰዎችም ሁሉ የወርቅ ስጦታ ወደ እግዚአብሔር አቀረቡ። ሰማያዊም ሐምራዊም ቀይ ግምጃም፥ ጥሩ በፍታም፥ የፍየል ጠጉርም፥ ቀይ የአውራ በግ ቁርበትም፥ የአቆስጣ ቁርበትም ያላቸው ሰዎች ሁሉ አመጡ። ስእለት የተሳለ ሁሉ የብርንም የናስንም ስጦታ ለእግዚአብሔር ቁርባን አቀረበ፤ የግራርም እንጨት ያለው ሁሉ ለማገልገያ ሥራ አመጣ። በልባቸው ጥበበኞች የሆኑ ሴቶችም በእጃቸው ፈተሉ፥ የፈተሉትንም ሰማያዊውን ሐምራዊውንም ቀዩንም ግምጃ፥ ጥሩውንም በፍታ አመጡ። ልባቸውም በጥበብ ያስነሣቸው ሴቶች ሁሉ የፍየልን ጠጕር ፈተሉ። አለቆችም መረግድን፥ ለኤፉድና ለደረት ኪስ የሚገቡትንም ፈርጦችን፥ ለመብራትም ለቅብዓት ዘይትም ለጣፋጭ ዕጣንም ሽቱንና ዘይትን አመጡ። ከእስራኤል ልጆችም ያመጡ ዘንድ ልባቸው ያስነሣቸው ወንዶችና ሴቶች ሁሉ ሙሴ ይሠራ ዘንድ እግዚአብሔር ላዘዘው ሥራ ሁሉ ለእግዚአብሔር ስጦታ በፈቃዳቸው አመጡ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}