ኦሪት ዘዳግም 4:32-40

ኦሪት ዘዳግም 4:32-40 አማ54

እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ከፈጠረው ጀምሮ፥ ከሰማይ ዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ ከቶ እንዲህ ያለ ታላቃ ነገር ወይም እንደ እርሱ ያለ ተሰምቶ እንደሆነ ከአንተ በፊት የነበረውን የቀደመውን ዘመን ጠይቅ። አንተ ከእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር የእግዚአብሔርን ድምፅ እንደ ሰማህ፥ ሌላ ሕዝብ ሰምቶ በሕይወት ይኖራልን? አምላካችሁ እግዚአብሔር በዓይናችሁ ፊት በግብፅ ለእናንተ እንደ ሠራው ሁሉ፥ በፈተናና በተአምራት፥ በድንቅና በሰልፍ፥ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ በታላቅም ማስፈራት እግዚአብሔር ከሌላ ሕዝብ መካከል ገብቶ ለእርሱ ሕዝብን ይወስድ ዘንድ ሞክሮ ነበርን? እግዚአብሔርም አምላክ እንደ ሆነ ታውቅ ዘንድ ይህ ለአንተ ተገለጠ፤ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም። ያስተምርህ ዘንድ ከሰማይ ድምፁን አሰማህ፤ በምድርም ላይ ታላቁን እሳት አሳየህ፤ ከእሳትም ውስጥ ቃሉን ሰማህ። አባቶችህን ወድዶአልና ከእነርሱ በኋላ ዘራቸውን መረጠ፥ ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ከአንተ የጸኑትን ታላላቆችን አሕዛብ በፊትህ እንዲያወጣ፥ አንተንም እንዲያገባህ፥ ምድራቸውንም ርስት አድርጎ እንዲሰጥህ፥ ከአንተ ጋር ሆኖ በታላቅ ኃይሉ ከግብፅ አወጣህ። እንግዲህ እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታችም በምድር አምላክ እንደ ሆነ፥ ሌላም እንደሌለ ዛሬ እወቅ፥ በልብህም ያዝ። ለአንተ ከአንተም በኋላ ለልጆችህ መልካም ይሆን ዘንድ፥ አምላክህም እግዚአብሔር ለዘላለም በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ ይረዝም ዘንድ፥ እኔ ዛሬ የማዝዝህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ጠብቅ።