በዳዊትም ዘመን ሦስት ዓመት ያህል ቀጥሎ ቀጥሎ ራብ ሆነ፥ ዳዊትም የእግዚአብሔርን ፊት ጠየቀ። እግዚአብሔርም፦ የገባዖንን ሰዎች ስለ ገደለ በሳኦልና በቤቱ ላይ ደም አለበት አለ። ንጉሡም የገባዖንን ሰዎች ጠራ፥ የገባዖን ሰዎችም ከአሞራውያን የተረፉ ነበሩ እንጂ ከእስራኤል ልጆች ወገን አልነበሩም፥ የእስራኤልም ልጆች ምለውላቸው ነበር፥ ሳኦል ግን ለእስራኤል ልጆችና ለይሁዳ ስለ ቀና ሊገድላቸው ወድዶ ነበር። ዳዊትም የገባዖንን ሰዎች፦ የእግዚአብሔርን ርስት ትባርኩ ዘንድ ምን ላድርግላችሁ? ማስተሰረያውስ ምንድር ነው? አላቸው። የገባዖን ሰዎችም፦ በእኛና በሳኦል ወይም በእኛና በቤቱ መካከል ያለው የብርና የወርቅ ነገር አይደለም፥ ከእስራኤልም ወገን እኛ የምንገድለው የለም አሉት። እርሱም፦ የምትናገሩትን አደርግላችኋለሁ አለ። ንጉሡንም፦ እኛን ካጠፋ፥ ከእስራኤል ዳርቻ ሁሉ እንዳንቀመጥ መፍረሳችንን ካሰበው ሰው ልጆች ሰባት ሰዎች አሳልፈህ ስጠንና ከእግዚአብሔር በተመረጠው በሳኦል አገር በጊብዓ ለእግዚአብሔር እንሰቅላቸዋለን አሉት። ንጉሡም፦ እሰጣችኋለሁ አለ። ንጉሡም በሳኦል ልጅ በዮናታንና በዳዊት መካከል ስለ ነበረው ስለ እግዚአብሔር መሐላ የሳኦልን ልጅ የዮናታንን ልጅ ሜምፊቦስቴን አዳነ። ንጉሡም ለሳኦል የወለደቻቸውን የኢዮሄል ልጅ የሪጽፋን ሁለቱን ልጆች ሄርሞንንና ሜምፊቦስቴን ለመሓላታዊውም ለቤርዜሊ ልጅ ለኤስድሪኤል የወለደቻቸውን የሳኦልን ልጅ የሜሮብን አምስቱን ልጆች ወሰደ፥ ለገባዖንም ሰዎች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት በተራራው ላይ ሰቀሉአቸው፥ ሰባቱም በአንድነት ወደቁ፥ እህል በሚታጨድበት ወራት በገብሱ መከር መጀመሪያ ተገደሉ። የኢዮሄልም ልጅ ሪጽፋ ማቅ ወስዳ ከመከር ወራት ጀምሮ ዝናብ ከሰማይ እስኪዘንብ ድረስ በድንጋይ ላይ ዘረጋችው በቀንም ወፎች በሌሊትም አራዊት ያርፉባቸው ዘንድ አልተወችም። የሳኦልም ቁባት የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ያደረገችውን ለዳዊት ነገሩት። ዳዊትም ሄደ፥ ሳኦልንም በጊልቦዓ በገደሉ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን ከሰቀሉአቸው ስፍራ ከቤትሳን አደባባይ ከሰረቁት ከኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት ወሰደ፥ ከዚያም የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት ይዞ መጣ፥ የተሰቀሉትንም ሰዎች አጥንት ሰበሰቡ። የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት በብንያም አገር በጼላ በአባቱ በቂስ መቃብር ቀበሩት፥ ንጉሡም ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ። ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር ስለ አገሩ የተለመነውን ሰማ።
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 21 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 21:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች