ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 16:5-13

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 16:5-13 አማ54

ንጉሡ ዳዊትም ወደ ብራቂም መጣ፥ እነሆም፥ ሳሚ የሚባል የጌራ ልጅ ከሳኦል ቤተ ዘመድ የሆነ አንድ ሰው ከዚያ ወጣ፥ እየሄደም ይረግመው ነበር። ወደ ዳዊትና ወደ ንጉሡ ወደ ዳዊት ባሪያዎች ድንጋይ ይወረውር ነበር፥ በንጉሡም ቀኝና ግራ ሕዝቡ ሁሉና ኃያላኑ ሁሉ ነበሩ። ሳሚም ሲረግም፦ ሂድ፥ አንተ የደም ሰው፥ ምናምንቴ፥ ሂድ። በፋንታው ነግሠሃልና እግዚአብሔር የሳኦልን ቤት ደም ሁሉ መለሰብህ፥ እግዚአብሔርም መንግሥትን ለልጅህ ለአቤሴሎም እጅ አሳልፎ ሰጥቶታል፥ እነሆም፥ አንተ የደም ሰው ነህና በመከራ ተይዘሃል አለ። የጽሩያም ልጅ አቢሳ ንጉሡን፦ ይህ የሞተ ውሻ ጌታዬን ንጉሡን ስለምን ይረግማል? ልሂድና ራሱን ልቁረጠው አለው። ንጉሡም፦ እናንተ የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? እግዚአብሔር፦ ዳዊትን ስደበው ብሎ አዝዞታልና ይርገመኝ፥ ለምንስ እንዲህ ታደርጋለህ? የሚለው ማን ነው? አለ። ዳዊትም አቢሳንና ባሪያዎቹን ሁሉ፦ እነሆ፥ ከወገቤ የወጣው ልጄ ነፍሴን ይሻል፥ ይልቁንስ ይህ የብንያም ልጅ እንዴት ነዋ? እግዚአብሔር አዝዞታልና ተዉት፥ ይርገመኝ። ምናልባት በዚህ ቀን መከራዬን አይቶ ስለ እርግማኑ መልካም ይመልስልኛል አላቸው። ዳዊትና ሰዎቹም በመንገድ ይሄዱ ነበር፥ ሳሚም በተራራው አጠገብ በእርሱ ትይዩ እየሄደ ይራገም ድንጋይም ይወረውር፥ ትቢያም ይበትን ነበር።