ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 12:1-23

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 12:1-23 አማ54

እግዚአብሔርም ናታንን ወደ ዳዊት ላከ፥ ወደ እርሱም መጥቶ አለው፦ በአንድ ከተማ አንዱ ባለጠጋ አንዱም ድሀ የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ። ባለጠጋውም እጅግ ብዙ በግና ላም ነበረው። ለድሀው ግን ከገዛት አንዲት ታናሽ በግ በቀር አንዳች አልነበረውም፥ አሳደጋትም፥ ከልጆቹም ጋር በእርሱ ዘንድ አደገች፥ እንጀራውንም ትበላ፥ ከዋንጫውም ትጠጣ፥ በብብቱም ትተኛ ነበር፥ እንደ ልጁም ነበረች። ወደ ባለጠጋውም እንግዳ በመጣ ጊዜ ከበጉና ከላሙ ወስዶ ለዚያ ወደ እርሱ ለመጣው እንግዳ ያዘጋጅለት ዘንድ ሳሳ፥ የዚያንም የድሀውን ሰው በግ ወስዶ ለዚያ ለመጣው ሰው አዘጋጀ። ዳዊትም በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቆጥቶ ናታንን፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ያደረገ ሰው የሞት ልጅ ነው። ይህን አድርጎአልና፥ አላዘነምና ስለ አንዲቱ በግ አራት ይመልስ አለው። ናታንም ዳዊትን አለው፦ ያ ሰው አንተ ነህ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ልትሆን ቀባሁህ፥ ከሳኦልም እጅ አዳንሁህ፥ የጌታህን ቤት ሰጠሁህ፥ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ ጣልሁልህ፥ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ ይህም አንሶ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ እጨምርልህ ነበር። አሁንስ በፊቱ ክፉ ትሠራ ዘንድ የእግዚአብሔርን ነገር ለምን አቃለልህ? ኬጢያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መትተሃል፥ ሚስቱንም ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃል፥ እርሱንም በአሞን ልጆች ሰይፍ ገድለሃል። ስለዚህም አቃልለኽኛልና፥ የኬጢያዊውንም የኦርዮን ሚስት ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃልና ለዘላለም ከቤትህ ሰይፍ አይርቅም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ከቤትህ ክፉ ነገር አስነሣብሃለሁ፥ ሚስቶችህንም በዓይንህ ፊት እወስዳለሁ፥ ለዘመድህም እሰጣቸዋለሁ፥ በዚህችም ፀሐይ ዓይን ፊት ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል። አንተ ይህን በስውር አድርገኸዋል፥ እኔ ግን ይህን በእስራኤል ሁሉ ፊትና በፀሐይ ፊት አደርገዋለሁ። ዳዊትም ናታንን፦ እግዚአብሔርን በድያለሁ አለው። ናታንም ዳዊትን፦ እግዚአብሔር ደግሞ ኃጢአትህን አርቆልሃል፥ አትሞትም። ነገር ግን በዚህ ነገር ለእግዚአብሔር ጠላቶች ታላቅ የስድብ ምክንያት አድርገሃልና ስለዚህ ደግሞ የተወለደልህ ልጅ ፈጽሞ ይሞታል አለው። ናታንም ወደ ቤቱ ተመለሰ። እግዚአብሔርም የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችውን ሕፃን ቀሠፈ፥ እጅግም ታምሞ ነበር። ዳዊትም ስለ ሕፃኑ እግዚአብሔርን ለመነ፥ ዳዊትም ጾመ፥ ገብቶም በመሬት ላይ ተኛ። የቤቱም ሽማግሌዎች ተነሥተው ከምድር ያነሡት ዘንድ በአጠገቡ ቆሙ፥ እርሱ ግን እንቢ አለ፥ ከእነርሱም ጋር እንጀራ አልበላም። በሰባተኛውም ቀን ሕፃኑ ሞተ። የዳዊትም ባሪያዎች፦ ሕፃኑ በሕይወት ሳለ ብንነግረው አልሰማንም፥ ይልቁንስ ሕፃኑ እንደ ሞተ ብንነግረው እንዴት ይሆን? በነፍሱ ክፉ ያደርጋል ብለው ሕፃኑ እንደ ሞተ ይነግሩት ዘንድ ፈሩ። ዳዊትም ባሪያዎቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ ባየ ጊዜ ዳዊት ሕፃኑ እንደ ሞተ አወቀ፥ ዳዊትም ባሪያዎቹን፦ ሕፃኑ ሞቶአል? አላቸው። እነርሱም፦ ሞቶአል አሉት። ዳዊትም ከምድር ተነሥቶ ታጠበ፥ ተቀባም፥ ልብሱንም ለወጠ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገብቶ ሰገደ። ወደ ቤቱም መጣ፦ እንጀራ አምጡልኝ አለ፥ በፊቱም አቀረቡለት፥ በላም። ባሪያዎቹም፦ ይህ ያደረግኸው ነገር ምንድር ነው? በሕይወት ሳለ ስለ ሕፃኑ ጾምህና አለቀስህ፥ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ እንጀራ በላህ አሉት። እርሱም፦ ሕፃኑ ሕያው ሳለ፦ እግዚአብሔር ይምረኝ፥ ሕፃኑም በሕይወት ይኖር እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ብዬ ጾምሁ አለቀስሁም። አሁን ግን ሞቶአል፥ የምጾመው ስለ ምንድር ነው? በውኑ እንግዲህ እመልሰው ዘንድ ይቻለኛልን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ እርሱ ወደ እኔ አይመለስም አለ።