ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 5:20-27

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 5:20-27 አማ54

የእግዚአብሔርም ሰው ሎሌ ግያዝ “ጌታዬ ሶርያዊውን ይህን ንዕማንን ማረው፤ ካመጣለትም ነገር ምንም አልተቀበለም፤ ሕያው እግዚአብሔርን! በስተ ኋለው እሮጣለሁ፤ ከእርሱም አንዳች እወስዳለሁ፤” አለ። ግያዝም ንዕማንን ተከተለው፤ ንዕማንም ወደ እርሱ ሲሮጥ ባየው ጊዜ ሊገናኘው ከሠረገላው ወርዶ “ሁሉ ደኅና ነውን?” አለው። እርሱም “ደኅና ነው፤ ‘አሁን ከነቢያት ወገን የሆኑት ሁለት ጕልማሶች ከተራራማው ከኤፍሬም አገር ወደ እኔ መጥተዋል፤ አንድ መክሊት ብርና ሁለት መለወጫ ልብስ ትሰጣቸው ዘንድ እለምንሃለሁ፤’ ብሎ ጌታዬ ላከኝ፤” አለ። ንዕማንም “ሁለት መክሊት ትወስድ ዘንድ ይፈቀድልህ፤” አለ፤ ግድ አለውም፤ ሁለቱንም መክሊት ብር በሁለት ከረጢት ውስጥ አሰረና ከሁለት መለወጫ ልብስ ጋር ለሁለት ሎሌዎቹ አስያዘ፤ እነርሱም ተሸክመው በፊቱ ሄዱ። ወደ ኮረብታውም በመጣ ጊዜ ከእጃቸው ወስዶ በቤቱ ውስጥ አኖራቸው፤ ሰዎቹንም አሰናበተ፤ እነርሱም ሄዱ። እርሱ ግን ገብቶ በጌታው ፊት ቆመ፤ ኤልሳዕም “ግያዝ ሆይ! ከወዴት መጣህ?” አለው። እርሱም “እኔ ባሪያህ ወዴትም አልሄድሁም፤” አለ። እርሱም “ያ ሰው ከሠረገላው ወርዶ ሊቀበልህ በተመለሰ ጊዜ ልቤ ከአንተ ጋር አልሄደምን? ብሩንና ልብሱን፥ የወይራውንና የወይኑን ቦታ፥ በጎችንና በሬዎችን፥ ወንዶችንና ሴቶችን ባሪያዎች ትቀበል ዘንድ ይህ ጊዜው ነውን? እንግዲህስ የንዕማን ለምጽ በአንተ ላይ በዘርህም ላይ ለዘላለም ይጣበቃል፤” አለው። እንደ በረዶም ለምጻም ሆኖ ከእርሱ ዘንድ ወጣ።