ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 8

8
ሰሎሞን ያከናወናቸው ሌሎች ሥራዎች
(1ነገ. 9፥10-28)
1እንዲህም ሆነ፤ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤትና የራሱን ቤት የሠራበት ሃያ ዓመት በተፈጸመ ጊዜ፥ 2ኪራም ለሰሎሞን የሰጠውን ከተሞች ሰሎሞን ሠራቸው፤ የእስራኤልንም ልጆች አኖረባቸው።
3ሰሎሞንም ወደ ሐማትሱባ ሄደ፤ አሸነፋትም። 4በምድረ በዳም ያለውን ተድሞርን፥ በሐማትም የሠራቸውን የዕቃ ቤቱን ከተሞች ሁሉ ሠራ። 5ደግሞም ቅጥርና መዝጊያ መወርወሪያም የነበራቸውን የተመሸጉትን ከተሞች ላይኛውን ቤትሖሮን ታችኛውንም ቤትሖሮን ሠራ። 6ባዓላትንም፥ ለሰሎሞንም የነበሩትን የዕቃ ቤት ከተሞች ሁሉ፥ የሠረገላውንም ከተሞች ሁሉ፥ የፈረሰኞችንም ከተሞች፥ በኢየሩሳሌምም በሊባኖስም በመንግሥቱም ምድር ሁሉ ሰሎሞን ይሠራ ዘንድ የወደደውን ሁሉ ሠራ።
7ከኬጢያውያንም ከአሞራውያንም ከፌርዜያውያንም ከሒዋውያንም ከኢያቡሳውያንም የቀሩትን ከእስራኤል ወገን ያልሆኑትን ሕዝብ ሁሉ፥ 8የእስራኤልም ልጆች ያላጠፉአቸውን፥ በኋላቸው በምድር ላይ የቀሩትን ልጆቻቸውን ሰሎሞን እስከ ዛሬ ድረስ ገባሮች አድርጎ መለመላቸው። 9ሰሎሞንም ለሥራው ከእስራኤል ልጆች ማንንም ባሪያ አላደረገም፤ እነርሱ ግን ሰልፈኞች፥ የሹማምቶችም አለቆች፥ የሠረገሎችና የፈረሰኞች ባልደራሶች ነበሩ። 10እነዚህም በሕዝቡ ላይ ሠልጥነው የነበሩ የንጉሡ የሰሎሞን ዓይነተኞች አለቆች ሁለት መቶ አምሳ ነበሩ። 11ሰሎሞንም “የእግዚአብሔር ታቦት የገባበት ስፍራ ቅዱስ ነውና ሚስቴ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት ቤት አትቀመጥም፤” ሲል የፈርዖንን ልጅ ከዳዊት ከተማ ወደ ሠራላት ቤት አወጣት።
12በዚያን ጊዜም ሰሎሞን በወለሉ ፊት በሠራው በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ። 13ሙሴም እንዳዘዘ እንደ ሥርዓታቸው በየቀኑ ሁሉ፥ በየሰንበታቱም፥ በየመባቻዎቹም፥ በየተወሰኑትም በዓላት፥ በየዓመቱ ሦስት ጊዜ በየቂጣው በዓልና በየሰባቱ ሱባዔ በዓል በየዳሱም በዓል ቍርባን ያቀርቡ ነበር።
14የእግዚአብሔርም ሰው ዳዊት እንዲህ አዝዞ ነበርና ካህናቱን እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ሥርዓት በየአገልግሎታቸው ሰሞን ከፈላቸው፤ ሌዋውያንም እንደ ሥርዓታቸው ያመሰግኑ ዘንድ፥ በካህናቱም ፊት ያገለግሉ ዘንድ በየሰሞናቸው ከፈላቸው፤ በረኞቹንም ደግሞ በየበሩ ሁሉ በየሰሞናቸው ከፈላቸው። 15እነርሱም ንጉሡ ስለ ነገሩ ሁሉና ስለ መዝገቡ ካህናቱንና ሌዋውያኑን ያዘዘውን ነገር ሁሉ አልተላለፉም። 16የእግዚአብሔርም ቤት መሠረት ከተጣለ ጀምሮ እስከ ተጨረሰ ድረስ የሰሎሞን ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ነበረ። የእግዚአብሔርም ቤት ተፈጸመ።
17ሰሎሞንም የዚያን ጊዜ በኤዶምያስ ምድር በባሕር ዳር ወዳሉ ወደ ዔጽዮን ጋብርና ወደ ኤሎት ሄደ። 18ኪራምም መርከቦችንና የባሕርን ነገር የሚያውቁትን መርከበኞች በባሪያዎቹ እጅ ሰደደለት፤ እነርሱም ከሰሎሞን ባሪያዎች ጋር ወደ ኦፊር መጡ፤ ከዚያም አራት መቶ አምሳ መክሊት ወርቅ ወስደው ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን አመጡ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ