አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 19:7-13

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 19:7-13 አማ54

የእግዚአብሔር መልአክ ደግሞ ሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ዳሰሰውና “የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ነውና ተነሥተህ ብላ፤” አለው። ተነሥቶም በላ፤ ጠጣም፤ በዚያም ምግብ ኀይል እስከ እግዚአብሔር ተራራ እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሄደ። እዚያም ወዳለ ዋሻ መጣ፥ በዚያም አደረ። እነሆም “ኤልያስ ሆይ! በዚህ ምን ታደርጋለህ?” የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ። እርሱም “ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋል፤ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋል፤ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋል፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ፤” አለ። እርሱም “ውጣ፤ በተራራውም ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቁም፤” አለ። እነሆም፥ እግዚአብሔር አለፈ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጠቀ፤ ዐለቶቹንም ሰባበረ፤ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሆነ፤ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ ውስጥ አልነበረም። ከምድር መናወጥ በኋላ እሳት ሆነ፤ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱም በኋላ ትንሽ የዝምታ ድምፅ ሆነ። ኤልያስም ያን በሰማ ጊዜ ፊቱን በመጎናጸፊያው ሸፈነ፤ ወጥቶም በዋሻው ደጃፍ ቆመ። እነሆ “ኤልያስ ሆይ! በዚህ ምን ታደርጋለህ?” የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ።