ኤልያስም ፈርቶ ተነሣ፤ ነፍሱንም ሊያድን ሄደ፤ በይሁዳም ወዳለው ወደ ቤርሳቤህ መጥቶ ብላቴናውን በዚያ ተወ። እርሱም አንድ ቀን የሚያህል መንገድ በምድረ በዳ ሄደ፤ መጥቶም ከክትክታ ዛፍ በታች ተቀመጠና “ይበቃኛል፤ አሁንም፥ አቤቱ፥ እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ፤” ብሎ እንዲሞት ለመነ። በክትክታውም ዛፍ በታች ተጋደመ፤ እንቅልፍም አንቀላፋ፤ እነሆም፥ መልአክ ዳሰሰውና “ተነሥተህ ብላ፤” አለው። ሲመለከትም፥ እነሆ፥ በራሱ አጠገብ የተጋገረ እንጎቻና በማሰሮ ውሃ አገኘ። በላም፤ ጠጣም፤ ተመልሶም ተኛ። የእግዚአብሔር መልአክ ደግሞ ሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ዳሰሰውና “የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ነውና ተነሥተህ ብላ፤” አለው። ተነሥቶም በላ፤ ጠጣም፤ በዚያም ምግብ ኀይል እስከ እግዚአብሔር ተራራ እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሄደ። እዚያም ወዳለ ዋሻ መጣ፥ በዚያም አደረ። እነሆም “ኤልያስ ሆይ! በዚህ ምን ታደርጋለህ?” የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ። እርሱም “ለሠራዊት አምላክ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋል፤ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋል፤ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋል፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ፤” አለ። እርሱም “ውጣ፤ በተራራውም ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቁም፤” አለ። እነሆም፥ እግዚአብሔር አለፈ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጠቀ፤ ዐለቶቹንም ሰባበረ፤ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሆነ፤ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ ውስጥ አልነበረም። ከምድር መናወጥ በኋላ እሳት ሆነ፤ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱም በኋላ ትንሽ የዝምታ ድምፅ ሆነ።
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 19 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 19:3-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች