አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 17:18-24

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 17:18-24 አማ54

እርስዋም ኤልያስን “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! ከአንተ ጋር ምን አለኝ? ኀጢአቴንስ ታሳስብ ዘንድ፥ ልጄንስ ትገድል ዘንድ ወደ እኔ መጥተሃልን?” አለችው። ኤልያስም “ልጅሽን ስጪኝ፤” አላት። ከብብትዋም ወስዶ ተቀምጦበት ወደ ነበረው ሰገነት አወጣው፤ በአልጋውም ላይ አጋደመው። ወደ እግዚአብሔርም “አቤቱ አምላኬ ሆይ! ልጅዋን በመግደልህ ይህችን ትቀልበኝ የነበረቺቱን ባልቴት እንዲህ ደግሞ አስጨነቅኻትን?” ብሎ ጮኸ። በብላቴናውም ላይ ሦስት ጊዜ ተዘረጋበት፤ ወደ እግዚአብሔርም “አቤቱ አምላኬ ሆይ! የዚህ ብላቴና ነፍስ ወደ እርሱ ትመለስ ዘንድ እለምንሃለሁ፤” ብሎ ጮኸ። እግዚአብሔርም የኤልያስን ቃል ሰማ፤ የብላቴናውም ነፍስ ወደ እርሱ ተመለሰች፤ እርሱም ዳነ። ኤልያስም ብላቴናውን ይዞ ከሰገነቱ ወደ ቤት አወረደው፤ ኤልያስም “እነሆ፥ ልጅሽ በሕይወት ይኖራል፤” ብሎ ለእናቱ ሰጣት። ሴቲቱም ኤልያስን “የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንህ፥ የእግዚአብሔርም ቃል በአፍህ እውነት እንደ ሆነ አሁን አወቅሁ፤” አለችው።