ትን​ቢተ ዘካ​ር​ያስ 8:7-15

ትን​ቢተ ዘካ​ር​ያስ 8:7-15 አማ2000

የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ሕዝቤን ከምሥራቅ ምድርና ከምዕራብ ምድር አድነዋለሁ፣ አመጣቸዋለሁም፥ በኢየሩሳሌምም ውስጥ ይኖራሉ፣ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል፥ እኔም በእውነትና በጽድቅ አምላክ እሆናቸዋለሁ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ መቅደሱ ይሠራ ዘንድ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቤት ከተመሠረተበት ቀን ጀምሮ ከነቢያት አፍ ይህን ቃል በዚህ ዘመን የሰማችሁ እናንተ ሆይ፥ እጃችሁን አበርቱ። ከዚያ ወራት አስቀድሞ ለሰውና ለእንስሳ ዋጋ አልነበረምና፣ እኔም ሰውን ሁሉ በወንድሙ ላይ አስነሥቼ ነበርና ከአስጨናቂው የተነሣ ለሚገባውና ለሚወጣው ሰላም አልነበረም። አሁን ግን እንደ ቀደመው ዘመን በዚህ ሕዝብ ቅሬታ ላይ አልሆንም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ነገር ግን ሰላምን እዘራለሁ፣ ወይኑ ፍሬውን ይሰጣል፥ ምድርም አዝመራዋን ታወጣለች፥ ሰማያትም ጠላቸውን ይሰጣሉ፣ ለዚህም ሕዝብ ቅሬታ ይህን ነገር ሁሉ አወርሳለሁ። የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በአሕዛብ ዘንድ እርግማን እንደ ነበራችሁ፥ እንዲሁ አድናችኋለሁ፥ በረከትም ትሆናላችሁ፣ አትፍሩ፥ እጃችሁንም አበርቱ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ አባቶቻችሁ እጅግ ባስቈጡኝ ጊዜ ክፉ ለማድረግ እንዳሰብሁ፥ እንዳልተጸጸትሁም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ እንዲሁ ዳግመኛ ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ ቤት በዚህ ወራት በጎነትን አደርግ ዘንድ አስቤአለሁ፣ አትፍሩ።