መጽሐፈ ሲራክ 29
29
ስለ ማበደርና መበደር
1ምጽዋትን የሚመጸውት ሰው ለእግዚአብሔር#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ለባልንጀራው የሚያበድር” ይላል። ያበድራል፤
በእጁም የሚበቃ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “እጁን የሚዘረጋ” ይላል። ያለው ትእዛዙን ይፈጽማል።
2በደስታው ጊዜ ከእርሱ ጋር ደስ ይልህ ዘንድ፥
በተቸገረ ጊዜ ለባልንጀራህ አበድረው።
3ቃልህን ጠብቅ፤ ከእርሱም ጋራ ተማመን፤
በጊዜውም የሚያስፈልግህን ነገር ታገኛለህ።
4የብድርን ገንዘብ በምድር ላይ ወድቆ ያገኙት የሚመስላቸው ብዙዎች ናቸው፤
የረዷቸውንና ያበደሩአቸውንም ችግር ይፈጥሩባቸዋል።
5እስኪበደርህ ድረስ ራስህን ይስምሃል፤ ቃሉንም ያለሰልሳል፤
ገንዘብህንም እስኪወስድ ድረስ ያባብልሃል፤
በሚከፍልበት ጊዜ ግን ቀጠሮህን ያረዝምብሃል፤
በገንዘብህም ጠብና ክርክርን ይከፍልሃል፤
ያደክምሃል፤ ቀጠሮህንም ያሳልፋል።
6እኩሌታውን ቢከፍልህ በጭንቅ ነው፤
ዳግመኛም ያንኑ በምድር ላይ ወድቆ ያገኘኸው ይመስልሃል፤
ይህስ ካልሆነ ገንዘብህን ሁሉ ታጣለህ፤
ዳግመኛም ጠላት ይሆንሃል፤ ርግማንንና ስድብን ይከፍልሃል፤
ከሚያከብርህም ይልቅ ያዋርድሃል።
7ገንዘባቸውን እንዳያጡና እንዳይጣሉ በመፍራትና ጠብን ባለመውደድ ገንዘባቸውን የማያበድሩ ሰዎች ብዙ ናቸው።
ስለ ምጽዋት
8ድሃዉን ግን ታገሠው፤
ምጽዋቱንም ስጠው፤ አልፈኸውም አትሂድ።
9ችግረኛ ነውና በሕግ እንደ ታዘዘው ድኃዉን በምጽዋት ተቀበለው፤
ባዶውንም አትመልሰው።
10ባልንጀራህንና ወዳጅህን ከምታጣ፥
ተቀብሮ ከሚዝግና በድንጋይም ሥር ከሚጠፋ ወርቅህን እጣ።
11ስለ ልዑል ትእዛዝ በወርቅህ አስተዋፅኦ አድርግ፤
ከወርቅ ድልብ የበለጠም ያተርፍልሃል።
12ምጽዋትን በቤቶችህ አድልባት፤ እርስዋም ትሻላለች፤#“እርስዋም ትሻላለች” የሚለው በግሪኩ የለም።
ከመከራህም ሁሉ አንተን ማዳን ትችላለች።
ስለ ዋስትና
13ከጦርና ጋሻ ትሻላለች፤
ጠላትህን ድል ትነሣልሃለች፤ ታጠፋልሃለችም።
14ደግ ሰው ጎረቤቱን ይዋሰዋል፤
የማያፍር ሰው ግን ባልንጀራውን ቸል ይላል።
15ስለ አንተ ፋንታ ሰውነቱን አሳልፎ ሰጥትዋልና
የተዋሰህን ሰው ውለታ አትርሳ።
16ጠብን ለማጥፋት መዋስ ደግ ነገር ነው።
17ኀጢአተኛ ሰው ግን ያዳነውን ሰው ውለታ ይዘነጋል።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ኀጢአተኛ ሰው በዋስትና ምክንያት የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ያፈርሳል ትርፍንም ለመፈለግ በሚያደርገው ጥረት በፍርድ ላይ ይወድቃል” ይላል።
18መዋስ ብዙ ደጋግ ሰዎችን አሳዘነ፤
እንደ ባሕር ማዕበልም አወካቸው፤
አርበኞች ሰዎችንም አሳታቸው፤
ወደ ባዕድ ሕዝብም አሳደዳቸው።
19ኀጢአተኛ ሰው ግን በመዋስ ይጠፋል፤
ለትርፍም የሚሳሳ ሰው በመከራ ይወድቃል።
20በተቻለህ መጠን ባልንጀራህን ርዳው፤
ነገር ግን እንዳያስትህ ራስህን ጠብቅ።
21የሕይወትህ መጀመሪያ እህልና ውኃ፥ ልብስም ነው፤
ቤትህ ግን ኀፍረትህን የምትሰውርበት ነው።
22በሌላ ሰው ገንዘብ በባዕድ ቤት ፈጽመህ ደስ ከሚልህ፥
በራስህ ጎጆ ብትቸገር ይሻልሃል።
23ለታናሹም ለታላቁም ሥራህንና ቃልህን አሳምር።
24ካንዱ ቤት ወደ ሌላው ቤት የሚዞር ሰው ኑሮው ክፉ ነው፤
ባደርህበት ቦታ ክፉ ነገር እንዳትናገር ተጠንቀቅ።
25ያም ባይሆን ታበላለህ፤ ታጠጣለህም፤
ምስጋና ግን አይኖርህም፥ ከዚህም ሁሉ ጋር መራራ ነገርን ይመልሱልሃል።
26በተዘጋጀህ ጊዜ ግን እንዲህ ይሉሃል፥ “እንግዳችን ገብተህ ማዕድን ሥራ፤ ያለህንም አብላን።”
27ብትቸገር ግን፥ “እንግዳችን ውጣ፤
አማቻችን ደረሰ፤ ቤታችንን እንፈልገዋለን” ይሉሃል።
28ይህ ነገር በብልህ ሰው ዘንድ ጭንቅ ነው፤
ያሳደርኸው ሰው ያዋርድሃል፤ ያበደርኸውም ሰው ይሰድብሃል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 29: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ