መጽሐፈ ሲራክ 21
21
1ልጄ ሆይ፥ የበደልኸው በደል የሳትኸውም ነገር ቢኖር፥
እንዳትደግም ተጠንቀቅ፥ ስለ ቀደመው ኀጢአትህም ንስሓ ግባ።
2ከክፉ አውሬ እንደሚሸሽ እንዲሁ ከኀጢአት ሽሽ፥
ከአገኘችህ ግን አትለቅህም፤ ጥርሷ እንደ አንበሳ ጥርስ ነው፤
የሰውንም ነፍስ ታጠፋለች።
3ሁለት አፍ እንዳለው የተሳለ ሰይፍ ኀጢአት ሁሉ እንዲሁ ናት፤
ካቈሰለችም ለቍስሏ ፈውስ የለውም።
4መመካትና መኵራት፥ ትዕቢትም ባለጸግነትን ያጠፏታል፤
እንደዚሁም የትዕቢተኞችን ቤት ያጠፋሉ።
5ድሃ በሚለምንበት ጊዜ አፉን እስከ ዦሮው ይከፍታል፤
ጩኸቱም ፈጥኖ ወደ እግዚአብሔር ይደርሳል።
6ምክርን የሚጠላ ሰው ኀጢአተኞችን ይከተላቸዋል፤
እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ግን በመከሩት ጊዜ ልቡናውን ይመልሳል።
7ንግግርን የሚችል ሰው ከሩቁ ይታወቃል፤
ለብልህ ሰውም የተሳተው ኀጢአቱ ይታወቀዋል።
8በብድር ገንዘብ ቤቱን የሚሠራ ሰው፥
ሕንጻው እንደ ክረምት ግንብ ነው።
9የኀጢአተኞችም አንድነታቸው እንደ ገለባ ክምር ነው፤
ፍጻሜያቸውም ለእሳት ነበልባል ይሆናል።
10የኀጢአተኞች መንገድ ጐፃጕፅ ነው፤
መውጫዋም ገደል#ግሪኩ “ገሃነም” ይላል። ነው።
11ልቡናውን ያጸና ሰው የእግዚአብሔርን ሕግ ይጠብቃል።
እግዚአብሔርን የመፍራትም መጨረሻዋ ጥበብ ነው።
12ያልተማረ ሰው ጠቢብ አይሆንም፤
ተምሮም ውርደት የሚበዛበት አለ።
13የብልህ ሰው ዐሳቡ እንደ ክረምት ውኃ ብዙ ነው፤
ምክሩም እንደ ሕይወት ውኃ ይመነጫል፤
14ያላዋቂ ሰው ልብ እንደ ሰባራ ማድጋ ነው፤
የሰማውን ነገር ሁሉ መጠበቅ አይችልምና።
15አስተዋይ ሰው የጥበብን ነገር በሰማ ጊዜ ያደንቃታል፤
ዳግመኛም በእርስዋ ላይ ይጨምራል፤
አላዋቂ ልቡና ግን ከሰማ በኋላ ይተፋል፤
ወደ ኋላም ይመልሰዋል።
16የአላዋቂ ሰው ነገሩ በራቀ ጎዳና እንዳለ እንደሚከብድ ሸክም ነው፤
የብልህ ሰው አንደበት መወደድ ግን መልካም ነው።
17የብልህ ሰው ነገሩ በጉባኤ ይሰማል፤
ነገሩም ወደ ልብ ይገባል።
18ጥበብ በአላዋቂዎች ሰዎች ዘንድ እንደ ፈረሰች ቤት ናት።
ያላዋቂ ሰው ምክርም የማይወደድ ነገር ነው።
19ያላዋቂዎች ትምህርት እንደ ታሰረ እግር ነው።
ያላዋቂዎችም ልቡና ቀኝ እጁን እንደ ታሰረ ሰው ደካማ ነው።
20አላዋቂ ሰው በሳቀ ጊዜ ቃሉን ከፍ ያደርጋል፤
ብልህ ሰው ግን በጭንቅ ከንፈሩን ፈገግ ያደርጋል።
21ጥበብ በአስተዋይ ሰው ዘንድ እንደ ወርቅ ጌጥ ናት፥
በቀኝ እጅ እንዳለ አምባርም ናት።
22ያላዋቂ ሰው እግር ፈጥና ወደ ቤት ትገባለች፤
በትምህርት የተፈተነ ሰው ግን የሰውን ፊት ያፍራል።
23አላዋቂ ሰው በደጃፍ ሆኖ የሰው ቤትን ይመለከታል፤
ዐዋቂ ሰው ግን በውጭ ይቆማል።
24ለሰው በበር ተጠግቶ ማድመጥ አላዋቂነት ነው፤
በዐዋቂ ሰው ዘንድ ግን ይህን ነገር ማድረግ እጅግ አሳፋሪ ነው።
25የለፍላፊ ከንፈር የማይመለከተውን ይናገራል፤
የጠቢባን ቃል ግን በሚዛን የተመዘነች ናት።
26ያላዋቆች ልባቸው ባፋቸው ነው፤
የኣዋቂዎች አፍ ግን በልባቸው ነው።
27ኀጢአተኛ ሰው ሰይጣንን ቢረግመው ራሱን መርገሙ ነው።
28ሐሜተኛ ሰው ሰውነቱን ያረክሳል፤
ባደረበትም ቦታ ራሱን ያስጠላል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 21: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ