መጽሐፈ ሲራክ 12
12
1በጎ ሥራ በሠራህ ጊዜ የበጎነትህን ዋጋ ታገኝ ዘንድ፥
በጎ ሥራ የምትሠራለትን ዕወቅ።
2ለጻድቅ በጎ አድርግ፥ ዋጋህንም ታገኛለህ፤
በእርሱ ዘንድ ባታገኘው በፈጣሪው ዘንድ ታገኛለህ።
3ኀጢአትን በሚሠራና ምጽዋትን በማይመጸውት ዘንድ፥
በጎ ሥራ የለም።
4ኀጢአተኛ እንዳይወስድብህ ለጻድቁ ስጥ።
5ለድሃ መልካም አድርግ፥ ለክፉ ግን አትስጥ፤
እርሱ እንዳይወስድብህና በገንዘብህ ድል እንዳያደርግህ እንጀራህን ከልክለው፥
በጎ ነገር ስላደረግህለት ፋንታ በእርሱ ዘንድ ክፋትን እጥፍ ሆና ታገኛታለህና።
6እግዚአብሔር ኀጢአተኞች ሰዎችን ይጠላቸዋልና፤
ክፉ ሰዎችንም ይበቀላቸዋልና።
7ለኀጢአተኛ ከምትሰጥ ለጻድቅ ስጥ፤
በደስታም ጊዜ ወዳጅህ አያምልጥህ።
8በመከራህም ጊዜ ጠላትህ አይሰወርህ።
9ደስታህ ጠላቶችህን ያሳዝናቸዋል፤
ችግርህም ወዳጆችህን አስወጥቶ ይሰድዳቸዋል።
10የልቡናው ክፋት እንደ ብረት ዝገት ነውና፤
ጠላትህን ፈጽመህ አትመነው።
11በተቸገርህም ጊዜ እያመሰገነ ያገለግልሃል፤
ሰውነትህን አጽናት፤ ከእርሱም ተጠበቅ፤
እንደዛገ መስታወት ትሆንበታለህ፤ ፈጽሞም አይችልህም።
12እንዳይጎዳህ ባጠገብህ አታቁመው፥ በቦታህም አይቀመጥ፤
ሹመትህንም እንዳይወስድብህ በቀኝህ አታስቀምጠው።
በመጨረሻም ቃሌን ታውቀው ዘንድ አለህ፥ ምክሬንም ታስበዋለህ።
13በእባብ ለተነደፈ አስማተኛ፥
ወደ ክፉ አውሬም ለቀረበ ሁሉ ማን ያዝንለታል?
14ከኀጢአተኛም ሰው ጋር የሚሄድ፥
በኀጢአቱም የሚተባበር እንዲሁ ነው።
15ጠላትህ ከአንተ ጋር አንድ ጊዜ ይቆማል፥
ነገር ግን እስክትመለስ ድረስ#ግሪኩ “በተቸገርህ ጊዜ ግን” ይላል። አታየውም፥ ከአንተም ጋር አይታገሥም።
16ጠላትህ በከንፈሩ ቃሉን ያጣፍጥልሃል፥
በልቡ ግን በጕድጓድ ውስጥ ይጥልህ ዘንድ ይመክራል።
ጠላትህ በዐይኑ ያለቅስልሃል፥ ካሳተህ በኋላ ግን#ግሪኩ “ጊዜ ከአጋጠመው ግን” ይላል። ከደምህ አይጠግብም።
17ብትቸገርም ከሁሉ አስቀድሞ በፊትህ ታገኘዋለህ፤
እንደሚረዳህም ከጫማህ በታች ራሱን ዝቅ ያደርጋል።
18በእጁ ያጨበጭባል፤ ራሱንም ይነቀንቃል፤
ከዚህ በኋላ ግን ፊቱን መልሶ ይጠቃቀስብሃል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 12: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ