አንተ ሰው ሆይ፥ እውነት ለሚፈርደው ለእግዚአብሔር ምን ትመልስለታለህ? በወንድምህ ላይ የምትጠላውን ያን ሥራ አንተ ራስህ ከሠራኸው በራስህ የምትፈርድ አይደለምን? አንተ ራስህ ያን ሥራ ትሠራዋለህና። ይህም እንደዚህ በሚያደርጉ ሰዎች ላይ ቅጣት የሚያመጣ የእግዚአብሔር ፍርዱ እውነት እንደ ሆነ እናውቃለን። አንተ ሰው ሆይ፥ በሌላ ላይ አይተህ የምትጠላውንና የምትነቅፈውን ያን አንተ ራስህ የምትሠራው ከሆነ፥ ከእግዚአብሔር ፍርድ እንደምታመልጥ ታስባለህን? ወይስ በቸርነቱ ብዛት በመታገሡ፥ ለአንተም እሺ በማለቱ እግዚአብሔርን አላዋቂ ልታደርገው ታስባለህን? የእግዚአብሔርስ ቸርነቱ አንተን ወደ ንስሓ እንዲመልስህ አታውቅምን? ነገር ግን ልቡናህን እንደ ማጽናትህ፥ ንስሓም እንደ አለመግባትህ መጠን የእግዚአብሔር እውነተና ፍርድ በሚገለጥበት ቀን መቅሠፍትን ለራስህ ታከማቻለህ። እርሱ በእውነተና ፍርዱ ለሁሉ እንደ ሥራው ይከፍለዋልና። በበጎ ምግባር ጸንተው ለሚታገሡ፥ ምስጋናና ክብርን፥ የማይጠፋ ሕይወትንም ለሚሹ እርሱ የዘለዓለም ሕይወትን ይሰጣቸዋል። ለሚክዱና እውነትን ለሚለውጡ፥ ዐመፅንም ለሚወድዱ ሰዎች ዋጋቸው ቍጣና መቅሠፍት ነው። መከራና ጭንቀት አስቀድሞ በአይሁዳዊ፥ ደግሞም በአረማዊ፥ ሥራዉ ክፉ በሆነ ሰው ሁሉ ላይ ነው። ምስጋናና ክብር፥ ሰላምም አስቀድሞ ለአይሁዳዊ፥ ደግሞም ለአረማዊ፥ ሥራዉ መልካም ለሆነ ሁሉ ነው። እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላምና። ከሕግ ወጥተው የበደሉ በሕግ ይፈረድባቸዋል፤ ያለ ሕግ የበደሉ ሁሉም ያለ ሕግ ይፈረድባቸዋል። በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉ ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ አይጸድቁምና።
ወደ ሮሜ ሰዎች 2 ያንብቡ
ያዳምጡ ወደ ሮሜ ሰዎች 2
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ሮሜ ሰዎች 2:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች