መጽሐፈ ምሳሌ 6:1-35

መጽሐፈ ምሳሌ 6:1-35 አማ2000

ልጄ ሆይ፥ ለወዳጅህ ዋስ ብትሆን፥ እጅህን ለባላጋራህ ትሰጣለህ፤ የሰው ከንፈሩ ጽኑ ወጥመድ ነው፤ በአፉ ቃል ይጠፋል። ልጄ ሆይ፥ እኔ የማዝዝህን አድርግ፤ ራስህንም አድን፤ ስለ ወዳጅህ በክፉዎች እጅ ወድቀሃልና፤ ሰነፍ አትሁን፥ የተዋስኸውን ወዳጅህን አነሣሣው። ለዐይንህ እንቅልፍን፥ ለሽፋሽፍቶችህም ሸለብታን አትስጥ፤ እንደ ሚዳቋ ከወጥመድ፥ እንደ ወፍም ከጭራ ወጥመድ ትድን ዘንድ። አንተ ታካች፥ ወደ ገብረ ጕንዳን ሂድ፥ መንገዱንም ተመልክተህ ቅና። ከእርሱም ይልቅ ብልህ ሁን። ጌታ ሳይኖረው፥ መሰማርያ ሳይኖረው፥ የሚያሠራውም ሳይኖረው፥ መብሉን በበጋ ይሰበስባል፥ በመከርም ጊዜ በሰፊ ቦታ ያስቀምጣል። ወይም ወደ ንብ ሂድ፥ ሠራተኛ እንደ ሆነች፥ መልካም ሥራንም እንደምትሠራ ዕወቅ፥ የደከመችበትንም ነገሥታትና ሌሎች ሰዎች ለጤንነት ይወስዱታል። በሁሉም ዘንድ የተወደደች ናት፥ የከበረችም ናት። በአካሏ ደካማ ናት፥ በሥራዋ ግን የጸናች ናት፥ ጥበብን አክብራ አሳየች። አንተ ታካች እስከ መቼ ትተኛለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ? ጥቂት ትተኛለህ፥ ጥቂትም ትቀመጣለህ፥ ጥቂት ታሸልባለህ፥ ጥቂትም እጆችህን በደረትህ ታጥፋለህ፤ እንግዲህ ድህነት እንደ ክፉ መልእክተኛ፥ ችግርም እንደ ደኅና ርዋጭ ይመጣብሃል። ሰነፍ ባትሆን ግን ባለጸግነትህ እንደምንጭ ይመጣልሃል፤ ችግርም እንደ ክፉ ርዋጭ ከአንተ ይርቃል። ዓመፀኛና ሰነፍ የሆነ ሰው ቀና ያልሆኑ መንገዶችን ይሄዳል፤ በዐይኑ ይጠቅሳል፥ በእግሩ ይናገራል፥ በጣቱ ጥቅሻ ያመለክታል፤ ጠማማ ልቡ ሁልጊዜ ክፋትን ያስባል፤ እንደዚህም ያለ ሰው ጠብን በከተማ ላይ ይዘራል። ስለዚህ የማይድን ውድቀትና መመታት፥ ጥፋትም ድንገት ይደርስበታል፤ እግዚአብሔር በሚጠላቸው ሁሉ ደስ ይለዋልና፤ ስለ ነፍሱ ርኵሰትም ይደቅቃልና፥ እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ናቸው፥ ሰባተኛውንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፤ ትዕቢተኛ ዐይን፥ ሐሰተኛ ምላስ፥ የጻድቁን ደም የምታፈስስ እጅ፥ ክፉ ዐሳብን የሚያበቅል ልብ፥ ክፉዉን ለማድረግ ወዲህና ወዲያ የምትሮጥ እግር፥ ሐሰተኛ ምስክርን የሚያቀጣጥል፥ በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ። ልጄ ሆይ፥ የአባትህን ሕጎች ጠብቅ፥ የእናትህንም ትእዛዝ ቸል አትበል፤ ሁልጊዜ በልብህ አኑረው፥ በአንገትህም እሰረው። ስትሄድም ይመራሃል፤ ከአንተም ጋር ይኖር ዘንድ ውሰደው። ስትተኛ ይጠብቅሃል፤ ስትነሣም ያነጋግርሃል። ትእዛዝ መብራት፥ ሕግም ብርሃን ነውና፥ ትምህርትና ተግሣጽም የሕይወት መንገድ ነውና፥ ከጐልማሳ ሚስት፥ ከሌላዪቱም አንደበት ነገረ ሠሪነት ትጠብቅህ ዘንድ ትእዛዜን ጠብቅ፥ ውበቷ ድል አይንሣህ። በዐይኖችዋ አትጠመድ፥ በቅንድቧም አትማረክ። የአመንዝራ ሴት ክብር እስከ አንዲት እንጀራ ነው፤ አመንዝራ ሴትም የተከበሩ ወንዶች ነፍስን ታጠምዳለች። በጕያው እሳትን የሚታቀፍ፥ ልብሶቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? ወይም በፍም ላይ የሚሄድ፥ እግሮቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው? ወደ ጐልማሳ ሚስት የሚገባም እንዲሁ ነው፤ የሚነካትም ሁሉ አይነጻም። የሚሰርቅ ሌባ ቢያዝ የሚደንቅ አይደለም፥ የተራበች ነፍሱን ሊያጠግብ ይሰርቃልና፤ ቢያዝም ሰባት እጥፍ ይከፍላል፥ ነፍሱንም ያድን ዘንድ ገንዘቡን ሁሉ ይሰጣል። አመንዝራ ግን በአእምሮው ጉድለት፥ ነፍሱ የሚጠፋበትን ጥፋት ይሠራል። ቍስልንና ውርደትን ያገኛል፥ ስድቡም ለዘለዓለም አይደመሰስም። ባሏ ቅንዐትንና ቍጣን የተመላ ነውና፥ በፍርድ ቀን አይራራለትም። የጠብ ካሣ በምንም አይለወጥም፥ በገንዘብ ብዛትም አይታረቀውም።