በምንም አትጨነቁ፤ ነገር ግን በሁሉ ነገር ጸልዩ ማልዱም፤ እያመሰገናችሁም ልመናችሁን ለእግዚአብሔር ግለጡ። ሁሉ የሚገኝባት፥ ከልቡናና ከአሳብ ሁሉ በላይ የምትሆን የእግዚአብሔር ሰላም በኢየሱስ ክርስቶስ ልባችሁንና አሳባችሁን ታጽናው። አሁንም ወንድሞቻችን ሆይ፥ እውነትን ሁሉ፥ ቅንነትንም ሁሉ፥ ጽድቅንም ሁሉ፥ ንጽሕናንም ሁሉ፥ ፍቅርንና ስምምነትንም ሁሉ፥ በጎነትም ቢሆን፥ ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን ሁሉ አስቡ። ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን፥ የሰማችሁትንና ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ፤ የሰላም አምላክም ከሁላችሁ ጋር ይሆናል። በጌታችን እጅግ ደስ አለኝ፤ ቢሳናችሁ እንኳ አሁንም እንደምታስቡልኝ፥ ከዱሮ ጀምሮ ለእኔ ችግር ታስቡ፥ ትተጉም ነበርና። ይህንም የምል ስለ አጣሁ አይደለም፤ ያለኝ እንደሚበቃኝ አውቃለሁና። እኔ ችግሩንም፥ ምቾቱንም እችላለሁ፤ ራቡንም፥ ጥጋቡንም፥ ማዘኑንም፥ ደስታውንም፥ ሁሉን በሁሉ ለምጀዋለሁ፤ በሚያስችለኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ነገር ግን በመከራዬ ጊዜ ተባባሪዎች መሆናችሁ መልካም አደረጋችሁ። እናንተ የፊልጵስዩስ ሰዎች፤ በመጀመሪያው ትምህርት ከመቄዶንያ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትም ቢሆን፥ በመቀበል ከእኔ ጋር እንዳልተባበሩ እናንተ ታውቃላችሁ። በተሰሎንቄም ሳለሁ ደግሞ፥ አንድ ጊዜና ሁለት ጊዜ ለችግሬ ላካችሁልኝ። ይህንም የማነሣሣው ስጦታችሁን ፈልጌ አይደለም፤ በእናንተ ላይ የጽድቅ ፍሬ ይበዛ ዘንድ ፈልጌ ነው እንጂ። ነገር ግን ሁሉ አለኝ፤ ይበዛልኝማል፤ የመዓዛ ሽታና የተወደደ መሥዋዕት የሚሆነውን፥ ለእግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን ስጦታችሁን ከአፍሮዲጡ ተቀብዬ አሟልቻለሁ። ፈጣሪዬ እንደ ባለጸግነቱ መጠን፥ በክብር በኢየሱስ ክርስቶስ የምትሹትን ሁሉ ይፈጽምላችኋል። ለአባታችን ለእግዚአብሔር ለዘለዓለሙ ምስጋና ይሁን አሜን። በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳንን ሁሉ ሰላም በሉ፤ በእኔ ዘንድ ያሉ ወንድሞቻችንም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ቅዱሳንም ሁሉ፥ ይልቁንም ከቄሣር ቤተ ሰብእ የሆኑ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን። በሮሜ ተጽፋ በጢሞቴዎስና በአፍሮዲጡ እጅ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች የተላከች መልእክት ተፈጸመች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን አሜን።
ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4 ያንብቡ
ያዳምጡ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4:6-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች