ወደ ፊል​ሞና 1:4-18

ወደ ፊል​ሞና 1:4-18 አማ2000

በጌታ በኢየሱስ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ ዘንድ ስላለህ ስለ ፍቅርህና ስለ እምነትህ ሰምቼ፥ በጸሎቴ እያሳሰብሁ ሁልጊዜ አምላኬን አመሰግናለሁ፤ የእምነትህም ኅብረት፥ በእኛ ዘንድ ያለውን በጎ ነገር ሁሉ በማወቅ፥ ለክርስቶስ ኢየሱስ ፍሬ እንዲያፈራ እለምናለሁ፤ የቅዱሳን ልብ በአንተ ሥራ ስለ ዐረፈ፥ ወንድሜ ሆይ! በፍቅርህ ብዙ ደስታንና መጽናናትን አግኝቼአለሁና። ስለዚህ የሚገባውን አዝህ ዘንድ በክርስቶስ ምንም እንኳ ብዙ ድፍረት ቢኖረኝ፥ ይልቁንም እንደዚህ የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ሽማግሌው፥ አሁንም ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ እስረኛ የሆንሁ፥ ስለ ፍቅር እለምናለሁ። አስቀድሞ ስላልጠቀመህ፥ አሁን ግን ለእኔም ለአንተም ስለሚጠቅም በእስራቴ ስለ ወለድሁት ስለ ልጄ ስለ አናሲሞስ እለምንሃለሁ። እርሱን እልከዋለሁ፤ አንተም ልቤ እንደሚሆን ተቀበለው። እኔስ በወንጌል እስራት ስለ አንተ እንዲያገለግለኝ ለራሴ ላስቀረው እፈቅድ ነበር፤ ነገር ግን በጎነትህ በፈቃድህ እንጂ በግድ እንዳይሆን፥ ሳልማከርህ ምንም እንኳ ላደርግ አልወደድሁም። ተቀብለህ ለዘላለም እንድትይዘው ስለዚህ ምናልባት ለጊዜው ተለይቶሃልና፤ ከእንግዲህ ወዲህ እንደ ባሪያ አይሆንም፤ ነገር ግን ለእኔ በተለየ የተወደደ ወንድም ከሆነ፥ ለአንተማ ይልቅ በሥጋውም በጌታም ዘንድ ከባሪያ የሚሻል የተወደደ ወንድም እንዴት አይሆንም? እንግዲህ እንደ ባልንጀራ ብትቈጥረኝ፥ እንደ እኔ አድርገህ ተቀበለው። በአንዳች ነገር የበደለህ ቢኖር ግን ወይም ብድር ያለበት እንደሆነ፥ ይህን በእኔ ላይ ቍጠር፤