መጽሐፈ ነህምያ 6:1-9
መጽሐፈ ነህምያ 6:1-9 አማ2000
እንዲህም ሆነ፤ ቅጥሩን እንደ ሠራሁ፥ ከፍራሹም አንዳች እንዳልቀረበት ሰንባላጥና ጦቢያ ዓረባዊውም ጌሳም የቀሩትም ጠላቶቻችን ሰሙ፤ ነገር ግን እስከዚያ ጊዜ ድረስ በበሮቹ ውስጥ ሳንቃዎቹን አላቆምሁም ነበር። ሰንባላጥና ጌሳም፥ “መጥተህ በኦኖ ቈላ ውስጥ ባሉት መንደሮች እንገናኝ” ብለው ላኩብኝ፤ ነገር ግን ክፉ ያደርጉብኝ ዘንድ ይመክሩ ነበር። እኔም እንዲህ ስል መልእክተኞችን ላክሁባቸው፥ “እኔ ታላቅ ሥራ እሠራለሁ፤ እወርድም ዘንድ አይቻለኝም። ስለምን ወደ እናንተ በመምጣቴና በመውረዴ ሥራው ይታጐላል? ሥራውን እንደ ፈጸምሁ እመጣለሁ።” እንዲህም ቃል አራት ጊዜ ላኩብኝ፤ እኔም እንደ ፊተኛው ቃል መለስሁላቸው። ሰንባላጥም እንደ ፊተኛው ብላቴናውን አምስተኛ ጊዜ ላከብኝ፤ በእጁም ውስጥ እንዲህ የሚል ግልጥ ደብዳቤ ነበረ፦ “አንተና አይሁድ ዓመፃ እንድታስቡ፥ ስለዚህም ቅጥሩን እንድትሠራ፥ ንጉሣቸውም ትሆን ዘንድ እንድትወድድ በአሕዛብ ዘንድ ተሰምቶአል። ደግሞም፦ ንጉሥ በይሁዳ አለ ብለው ስለ አንተ በኢየሩሳሌም ይናገሩ ዘንድ ነቢያትን አቁመሃል፤ አሁንም ለንጉሡ ይህን ቃል ያወሩለታል፤ እንግዲህ መጥተህ በአንድነት እንማከር።” እኔም፥ “አንተ ከልብህ ፈጥረኸዋል እንጂ እንደ ተናገርኸው ነገር አይደለም” ብዬ ላክሁበት። እነርሱም ሁሉ ሥራው እንዳይፈጸም፥ “እጃቸው ይደክማል” ብለው አስፈራሩን፤ ስለዚህም እጆችን አበረታሁ።

