የማርቆስ ወንጌል 2:3-12
የማርቆስ ወንጌል 2:3-12 አማ2000
አራት ሰዎችም የተሸከሙትን ሽባ አመጡለት። ስለ ሕዝቡም ብዛት ወደ እርሱ ማቅረብ ቢያቅታቸው እርሱ ያለበትን የቤቱን ጣራ አነሡ፤ ነድለውም ሽባው የተኛበትን አልጋ አወረዱ። ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን “አንተ ልጅ! ኀጢአትህ ተሰረየችልህ፤” አለው። ከጻፎችም አንዳንዶቹ በዚያ ተቀምጠው ነበር በልባቸውም “ይህ ሰው ስለ ምን እንደዚህ ያለ ስድብ ይናገራል? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኀጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል፤” ብለው አሰቡ። ወዲያውም ኢየሱስ በልባቸው እንዲህ እንዳሰቡ በመንፈስ አውቆ እንዲህ አላቸው “በልባችሁ ይህን ስለ ምን ታስባላችሁ? ሽባውን ‘ኀጢአትህ ተሰረየችልህ፤’ ከማለት ወይስ ‘ተነሣ አልጋህንም ተሸከምና ሂድ፤’ ከማለት ማናቸው ይቀላል? ነገር ግን ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን ሊያስተሰርይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፤” ሽባውን “አንተን እልሃለሁ፥ ተነሣ፤ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ፤” አለው። ተነሥቶም ወዲያው አልጋውን ተሸክሞ በሁሉ ፊት ወጣ፤ ስለዚህም ሰዎች ሁሉ ተገረሙና “እንዲህ ያለ ከቶ አላየንም፤” ብለው እግዚአብሔርን አከበሩ።


