እርሱም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዐይኖቹን አንሥቶ እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ ድሆች፥ ብፁዓን ናችሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት የእናንተ ናትና። ዛሬ የምትራቡ፥ ብፁዓን ናችሁ፤ ትጠግባላችሁና፤ ዛሬ የምታለቅሱ፥ ብፁዓን ናችሁ፤ ትስቃላችሁና። ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ቢጠሉአችሁ፥ ከሰው ለይተው ቢአሳድዱአችሁ፥ ቢሰድቡአችሁ፥ ክፉ ስምም ቢአወጡላችሁ ብፁዓን ናችሁ። ያንጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ በደስታም ዝለሉ፤ ዋጋችሁ በሰማይ ብዙ ነውና፤ አባቶቻቸውም ነቢያትን እንዲሁ አድርገዋቸው ነበርና። ነገር ግን እናንተ ባለጠጎች፥ ወዮላችሁ፥ ደስታችሁን ጨርሳችኋልና። ዛሬ ለምትጠግቡ፥ ወዮላችሁ፥ ትራባላችሁና፤ ዛሬ ለምትስቁም ወዮላችሁ፥ ታዝናላችሁና፤ ታለቅሳላችሁምና። ሰዎች ሁሉ ስለ እናንተ መልካሙን ነገር ቢናገሩላችሁ ወዮላችሁ፥ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲህ ያደርጉ ነበርና። “ለምትሰሙኝ ለእናንተ ግን እንዲህ እላችኋለሁ፦ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ። የሚረግሙአችሁን መርቁአቸው፤ ለሚበድሉአችሁም ጸልዩላቸው። ጕንጭህን ለሚመታህም ሁለተኛይቱን ስጠው፤ መጐናጸፊያህን ለሚወስድም ቀሚስህን ደግሞ አትከልክለው። ለሚለምንህም ሁሉ ስጥ፤ ገንዘብህን የሚወስደውንም እንዲመልስ አትጠይቀው። ሰዎች ሊያደርጉላችሁ እንደምትወዱትም እንዲሁ እናንተ አድርጉላቸው። የሚወድዱአችሁን ብቻ ብትወዱማ እንግዲህ ዋጋችሁ ምንድን ነው? ይህንስ ኃጥኣንም ያደርጋሉ፤ የሚወድዳቸውንም ይወድዳሉ። በጎ ለሚያደርጉላችሁ በጎ ብታደርጉ እንግዲህ ዋጋችሁ ምንድን ነው? እንዲህስ ኃጥኣንም ያደርጋሉ። እንዲከፍላችሁ ተስፋ ለምታደርጉት ብታበድሩ እንግዲህ ዋጋችሁ ምንድን ነው? ኃጥኣንም በአበደሩት ልክ ይከፍሉአቸው ዘንድ ለኃጥኣን ያበድራሉና። አሁንም ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ መልካምም አድርጉላቸው፤ እንዲመልሱላችሁ ተስፋ ሳታደርጉ አበድሩ፤ ዋጋችሁም ብዙ ይሆናል፤ የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ለበጎዎችና ለክፉዎች ቸር ነውና። ሰማያዊ አባታችሁ የሚራራ እንደ ሆነ እናንተም የምትራሩ ሁኑ።
የሉቃስ ወንጌል 6 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 6
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 6:20-36
7 ቀናት
ኢየሱስ እንዴት እንድኖር ነው የሚፈልገው?
8 ቀናት
ኢየሱስ ስለራሱ ማን ብሎ ይላል?
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች