ጌታችን ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስን ተመልቶ ከዮርዳኖስ ተመለሰ፤ መንፈስም ወደ ምድረ በዳ ወሰደው። አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ከዲያብሎስ ተፈተነ፥ በእነዚያም ቀኖች ምንም አልበላም፤ እነዚያም ቀኖች ከተፈጸሙ በኋላ ተራበ። ዲያብሎስም፥ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህስ ይህ ድንጋይ እንጀራ ይሁን በል” አለው። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ነው እንጂ በእንጀራ ብቻ አይደለም የሚል ተጽፎአል” አለው። ዲያብሎስም ወደ ረዥም ተራራ አወጣው፤ የዓለምን መንግሥታትም ሁሉ በቅፅበት አሳየው። ዲያብሎስም እንዲህ አለው፥ “ይህን ሁሉ ግዛት፥ ይህንም ክብር ለአንተ እሰጥሃለሁ፤ ለእኔ ተሰጥቶአልና፤ ለወደድሁትም እሰጠዋለሁና። ስለዚህ አንተ በፊቴ ብትሰግድልኝ ይህ ሁሉ ለአንተ ይሁንልህ።” ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ሰይጣን ከኋላዬ ሂድ ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ልትሰግድ፥ እርሱንም ብቻ ልታመልክ ተጽፎአል” አለው። ወደ ኢየሩሳሌምም ወስዶ በቤተ መቅደሱ የማዕዘን ጫፍ ላይ አቆመው፤ እንዲህም አለው፥ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህስ አንተ ራስህ ወደ ታች መር ብለህ ውረድ። በመንገድህ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክትን ስለ አንተ ያዝዛቸዋል፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰነካከል በእጃቸው ያነሡሃል” ተብሎ ተጽፎአልና። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ፥ “ፈጣሪህ እግዚአብሔርን አትፈታተነው” ተብሎአል አለው። ዲያብሎስም በዚህ ሁሉ እርሱን መፈታተኑን ከፈጸመ በኋላ እስከ ጊዜው ከእርሱ ተለየ። ጌታችን ኢየሱስም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተመልሶ ወደ ገሊላ ሄደ፤ ዝናውም በሀገሩ ሁሉ ተሰማ። በየምኵራባቸውም ሁሉ ያስተምራቸው ነበር፤ ትምህርቱንም ያደንቁ ነበር፤ ሁሉም ያመሰግኑት ነበር። ወደ አደገበት ወደ ናዝሬትም ሄደ፤ በሰንበት ቀንም እንዳስለመደ ወደ ምኵራብ ገባ፤ ሊያነብም ተነሣ። የነቢዩን የኢሳይያስንም መጽሐፍ ሰጡት፤ መጽሐፉንም በገለጠ ጊዜ እንዲህ የሚል የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ። “የእግዚአብሔር መንፈስ በላዬ ነው፤ ስለዚህ ቀብቶ ለድሆች የምሥራችን እነግራቸው ዘንድ፥ ለተማረኩትም ነጻነትን እሰብክላቸው ዘንድ፥ ያዘኑትንም ደስ አሰኛቸው ዘንድ፥ ዕውሮችም ያዩ ዘንድ፥ የተገፉትንም አድናቸው ዘንድ፥ የታሰሩትንም እፈታቸው ዘንድ፥ የቈሰሉትንም አድናቸው ዘንድ፥ የተመረጠችውንም የእግዚአብሔርን ዓመት እሰብክ ዘንድ ላከኝ።” መጽሐፉንም አጥፎ ለተላላኪው ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኲራብም የነበሩት ሁሉ ዐይናቸውን አትኲረው ተመለከቱት። እርሱም፥ “የዚህ የመጽሐፍ ነገር ዛሬ በጆሮአችሁ ደረሰ፤ ተፈጸመም” ይላቸው ጀመር። ሁሉም የንግግሩን መከናወን መሰከሩለት፤ የአንደበቱንም ቅልጥፍና እያደነቁ፥ “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን?” ይሉ ነበር።
የሉቃስ ወንጌል 4 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 4
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 4:1-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች