የሉቃስ ወንጌል 1:8-23
የሉቃስ ወንጌል 1:8-23 አማ2000
እርሱም በእግዚአብሔር ፊት በተራው የክህነትን ሥራ በሚሠራበት ጊዜ፥ ካህናት እንደሚያደርጉት የሚያጥንበት ጊዜ ደረሰ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ገባ። ዕጣን በሚያጥንበት ጊዜም ሕዝቡ በሙሉ በውጭ ይጸልዩ ነበር። የእግዚአብሔር መልአክም በዕጣን መሠውያው በስተቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ ፍርሀትም ረዓድም ወረደበት። መልአኩም እንዲህ አለው፥ “ዘካርያስ ሆይ፥ አትፍራ፤ ጸሎትህ በእግዚአብሔር ፊት ተሰምቶአልና፤ ሚስትህ ኤልሣቤጥም ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅንም ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። ደስታና ሐሤትም ይሆንልሃል፤ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። እርሱ በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ይሆናልና የወይን ጠጅና የሚያሰክርም መጠጥ ሁሉ አይጠጣም፤ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮም መንፈስ ቅዱስ ይመላበታል። ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ይመልሳቸዋል። እርሱም የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የከሓድያንንም ዐሳብ ወደ ጻድቃን ዕውቀት ይመልስ ዘንድ፥ ሕዝብንም ለእግዚአብሔር የተዘጋጀ ያደርግ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኀይል በፊቱ ይሄዳል።” ዘካርያስም የእግዚአብሔርን መልአክ እንዲህ አለው፥ “ይህ እንደሚሆን በምን አውቃለሁ? እነሆ፥ እኔ አርጅችአለሁ፤ የሚስቴም ዘመንዋ አልፏል።” መልአኩም መልሶ እንዲህ አለው፥ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ ይህንም እነግርህና አበሥርህ ዘንድ ወደ አንተ ተልኬአለሁ። አሁንም በጊዜው የሚሆነውንና የሚፈጸመውን ነገሬን አላመንኽኝምና ይህ እስኪሆን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ፤ መናገርም ይሳንሃል።” ሕዝቡ ግን ዘካርያስን ይጠብቁት ነበር፤ በቤተ መቅደስ ውስጥ ዘግይቶ ነበርና እጅግ ተደነቁ። ወደ እነርሱ ወደ ውጭ በወጣ ጊዜም እነርሱን ማነጋገር ተሳነው፤ በቤተ መቅደስም የተገለጠለት እንዳለ ዐወቁ፤ እንዲሁም ዲዳ ሆኖ በእጁ እያመለከታቸው ኖረ። ከዚህም በኋላ የማገልገሉ ወራት በተፈጸመ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ።



