ኢያሱም የእስራኤልን ነገድ ሁሉ ወደ ሴሎ ሰበሰበ፤ የእስራኤልንም ሽማግሌዎች፥ አለቆቻቸውንም፥ ጸሓፊዎቻቸውንም፥ ፈራጆቻቸውንም ጠራቸው። በእግዚአብሔርም ፊት አቆማቸው። ኢያሱም ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፥ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘አባቶቻችሁ፥ የአብርሃምና የናኮር አባት ታራ፥ አስቀድመው በወንዝ ማዶ ተቀመጡ፤ ሌሎችንም አማልክት አመለኩ። አባታችሁንም አብርሃምን ከወንዝ ማዶ ወስጄ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፤ ዘሩንም አበዛሁ፤ ይስሐቅንም ሰጠሁት። ለይስሐቅም ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁት፤ ለዔሳውም የሴይርን ተራራ ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤ የያዕቆብም ልጆች ወደ ግብፅ ወረዱ፤ በዚያም ታላቅ ሕዝብ ሆኑ፤ በዙም፤ በረቱም፤ ግብፃውያንም መከራ አጸኑባቸው። ሙሴንና አሮንንም ላክሁ፤ በእነርሱም ላይ ስላደረጉት ነገር ግብፃውያንን ቀሠፍኋቸው፤ ከዚያም በኋላ አባቶቻችሁን ከግብፅ አወጣኋቸው፤ ወደ ባሕሩም ገባችሁ፤ ግብፃውያንም አባቶቻችሁን በሰረገሎችና በፈረሶች እስከ ኤርትራ ባሕር ድረስ ተከተሉአቸው። ወደ እግዚአብሔርም በጮሃችሁ ጊዜ በእናንተና በግብፃውያን መካከል ደመናንና ጭጋግን አደረግሁ፤ ባሕሩንም መለስሁባቸው፤ አሰጠማቸውም፤ ዐይኖቻችሁም በግብፅ ያደረግሁትን አዩ፤ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ ተቀመጣችሁ። በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ተቀመጡት ወደ አሞሬዎናውያን ምድርም ወሰድኋችሁ፤ ከእናንተም ጋር ተዋጉ፤ ሙሴም ተዋጋቸው፤ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋችሁ፤ ምድራቸውንም ወረሳችሁ፤ ከፊታችሁም አጠፋኋቸው። የሞዓብም ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ ተነሥቶ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ፤ እንዲረግማችሁም የቢዖርን ልጅ በለዓምን ልኮ አስጠራው። እኔ ግን ላጠፋችሁ አልወደድሁም፤ መባረክንም ባረክኋችሁ፤ ከእጁም አዳንኋችሁ፤ ዮርዳኖስንም ተሻገራችሁ፤ ወደ ኢያሪኮም መጣችሁ፤ የኢያሪኮም ሰዎች፥ አሞሬዎናዊው፥ ፌርዜዎናዊው፥ ከነዓናዊው፥ ኬጤዎናዊው፥ ጌርጌሴዎናዊው፥ ኤዌዎናዊው፥ ኢያቡሴዎናዊው ተዋጉአችሁ፥ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋቸው። በፊታችሁም ተርብ ሰደድሁ፤ በሰይፍህም፥ በቀስትህም ሳይሆን ዐሥራ ሁለቱን የአሞሬዎናውያንን ነገሥታት ከፊታችሁ አሳደድኋቸው። ያልደከማችሁበትንም ምድር፥ ያልሠራችኋቸውንም ከተሞች ሰጠኋችሁ፤ ተቀመጣችሁባቸውም፤ ካልተከላችኋቸውም ከወይንና ከወይራ በላችሁ።’ “አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩት፤ በእውነትና በቅንነትም አምልኩት፤ አባቶቻችሁም በወንዝ ማዶ፥ በግብፅም ውስጥ ያመለኩአቸውን ሌሎች አማልክት ከእናንተ አርቁ፤ እግዚአብሔርንም አምልኩ። እግዚአብሔርን ታመልኩ ዘንድ ባትወድዱ ግን፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያመለኩአቸውን አማልክት፥ ወይም በምድራቸው ያላችሁባቸውን የአሞሬዎናውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ፥ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ እርሱ ቅዱስ ነውና።” ሕዝቡም መልሰው እንዲህ አሉ፥ “እግዚአብሔርን ትተን ሌሎች አማልክትን ማምለክ ከእኛ ይራቅ፤ እኛንና አባቶቻችንን ከባርነት ቤት ከግብፅ ምድር ያወጣን፥ በዐይናችንም ፊት እነዚያን ታላላቅ ተአምራት ያደረገ፥ በሄድንባትም መንገድ ሁሉ፥ ባለፍንባቸውም አሕዛብ ሁሉ መካከል የጠበቀን፥ እርሱ አምላካችን እግዚአብሔር ነውና። እግዚአብሔር አሕዛብን ሁሉ፥ በምድሪቱም የተቀመጡትን አሞሬዎናውያንን ከፊታችን አሳደደ፤ ስለዚህ እርሱ አምላካችን ነውና እኛ እግዚአብሔርን እናመልካለን።” ኢያሱም ሕዝቡን፥ “እርሱ ቅዱስ አምላክ ነውና፥ እርሱም ቀናተኛ አምላክ ነውና እግዚአብሔርን ማምለክ አትችሉም፤ ብታስቀኑት መተላለፋችሁንና ኀጢአታችሁን ይቅር አይልም። እግዚአብሔርን ትታችሁ ሌሎችን አማልክት ብታመልኩ፥ መልካምን ባደረገላችሁ ፋንታ ተመልሶ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፤ ያጠፋችሁማል” አላቸው። ሕዝቡም ኢያሱን፥ “እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን” አሉት። ኢያሱም ሕዝቡን፥ “እንድታመልኩት እናንተ እግዚአብሔርን እንደ መረጣችሁ በራሳችሁ ላይ ምስክሮች ናችሁ” አላቸው፤ እነርሱም፥ “ምስክሮች ነን” አሉ። እርሱም፥ “አሁን እንግዲህ በእናንተ ዘንድ ያሉትን ሌሎች አማልክት አርቁ፤ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር አቅኑ” አላቸው። ሕዝቡም ኢያሱን፥ “አምላካችንን እግዚአብሔርን እናመልካለን፤ ቃሉንም እንሰማለን” አሉት። በዚያም ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ በሴሎም በእስራኤል አምላክ ድንኳን ፊት ሕግንና ፍርድን ሰጣቸው።
መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 24 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 24:1-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች