እንዲህም ሆነ፤ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር የሙሴን አገልጋይ የነዌን ልጅ ኢያሱን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “አገልጋዬ ሙሴ ሞቶአል፤ አሁንም አንተና ይህ ሕዝብ ሁሉ ተነሥታችሁ ለእስራኤል ልጆች ወደምሰጣቸው ምድር ይህን ዮርዳኖስን ተሻገሩ። ለሙሴ እንደ ነገርሁት የእግራችሁ ጫማ የሚረግጠውን ቦታ ሁሉ ለእናንተ ሰጥቼአለሁ። ከሊባኖስ ፊት ለፊት ምድረ በዳ ጀምሮ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ የኬጤዎናውያን ምድር ሁሉ እስከ ፀሐይ መግቢያ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ወሰናችሁ ይሆናል። በሕይወትህ ዘመን ሁሉ የሚቋቋምህ የለም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ አልጥልህም፥ ቸልም አልልህም። ለአባቶቻቸው እሰጣቸው ዘንድ የማልሁላቸውን ምድር ለዚህ ሕዝብ ታወርሳለህና ጽና፥ በርታ። አገልጋዬ ሙሴ እንደ አዘዘህ ሕግን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ ጽና፤ እጅግም በርታ፤ ሁሉን እንዴት እንደምትሠራ ታውቅ ዘንድ ከእርሱ ወደ ቀኝ ወደ ግራም አትበል። የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፤ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አንብበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል፤ አስተዋይም ትሆናለህ። እነሆ አዝዝሃለሁ፤ በምትሄድበት ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ጽና፥ በርታ፤ አትፍራ፥ አትደንግጥም።” ኢያሱም የሕዝቡን ጻፎች እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ “በሰፈሩ መካከል ዕለፉ፥ ሕዝቡንም፦ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ ወደሚሰጣችሁ ምድር እስከ ሦስት ቀን ይህን ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ልትወርሱአት ትገቡባታላችሁና ስንቃችሁን አዘጋጁ ብላችሁ እዘዙአቸው።”
መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 1 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 1:1-11
6 ቀናት
በዚህ የ6 ቀን ጥናት ውስጥ ፍርሃት፣ ግራ መጋባትና ጭንቀትን ለማስወገድ በሕይወታችን ውስጥ የእግዚአብሔር መኖር ምን ያህል ማድረግ እንደሚችል እናያለን። ከእግዚአብሔር ጋር ጊዜ በማሳለፍና ከቃሉ በመማር እነዚህን ተግዳሮቶች እንዴት ማሸነፍ እንደምንችል፣ ትኩረታችንን እንዴት እንደምናስተካክልና አስተሳሰባችንን እንደምንለውጥ እናያለን።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች