አውስጢድ በሚባል ሀገር ስሙ ኢዮብ የተባለ አንድ ሰው ነበረ፤ ያም ሰው ቅን፥ ንጹሕና ጻድቅ፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፉ ሥራም ሁሉ የራቀ ነበር። ሰባትም ወንዶች፥ ሦስትም ሴቶች ልጆች ነበሩት። ከብቶቹም፦ ሰባት ሺህ በጎች፥ ሦስት ሺህ ግመሎች፥ አምስት መቶም ጥማድ በሬ፥ አምስት መቶም እንስት አህዮች ነበሩ፤ እጅግ ብዙም አገልጋዮች ነበሩት፤ ሥራውም በምድር ላይ ታላቅ ነበረ፤ ያም ሰው በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ገናና ነበረ። ወንዶች ልጆቹም ሄደው በየተራ በእያንዳንዳቸው ቤት ግብዣ ያደርጉ ነበር፤ ሦስቱ እኅቶቻቸውንም ከእነርሱ ጋር ይወስዱአቸው ነበር፤ ከእነርሱም ጋር ይበሉና ይጠጡ ነበር። የግብዣውም ቀኖች በተፈጸሙ ጊዜ ኢዮብ ይልክና ይቀድሳቸው ነበር፤ በማለዳም ገሥግሦ፦ ስለ ልጆቹ በቍጥራቸው መሥዋዕት ያቀርብ ነበር፤ አንድ ወይፈን ስለ ነፍሳቸው የኀጢአት መሥዋዕት ያቀርብ ነበር፤ ኢዮብ፥ “ምናልባት ልጆቼ በልባቸው በእግዚአብሔር ላይ ክፉ ነገር ያስቡ ይሆናል” ይል ነበርና። ከዕለታት አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፤ የእግዚአብሔር መላእክት በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ፤ ሰይጣንም ደግሞ ከእነርሱ ጋር መጣ። እግዚአብሔርም ሰይጣንን፥ “ከወዴት መጣህ?” አለው። ሰይጣንም፥ “ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ ከሰማይ በታችም ተመላለስሁና መጣሁ።” ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ። እግዚአብሔርም ሰይጣንን አለው፥ “በባሪያዬ በኢዮብ ላይ የምታስበው ነገር እንዳይኖር ተጠንቀቅ! በምድር ላይ እንደ እርሱ ቅን፥ ንጹሕና ጻድቅ፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፉ ሥራም ሁሉ የራቀ ሰው የለምና።” ሰይጣንም በእግዚአብሔር ፊት እንዲህ ብሎ መለሰ፥ “በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚያመልከው በከንቱ ነውን? አንተ ቤቱን በውስጥም በውጭም፥ በዙሪያው ያለውንም ሁሉ አልሞላህለትምን? የእጁንም ሥራ ባርከህለታል፥ ከብቱንም በምድር ላይ አብዝተህለታል። ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳስስ፤ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል።” እግዚአብሔርም ሰይጣንን፥ “እነሆ፥ ለእርሱ ያለውን ሁሉ በእጅህ ሰጠሁህ፥ ነገር ግን በእርሱ ላይ እጅህን አትዘርጋ” አለው። ሰይጣንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ።
መጽሐፈ ኢዮብ 1 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢዮብ 1:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች