ራት ከሚበሉበት ተነሥቶ ልብሱን አኖረና ማበሻ ጨርቅ አንሥቶ ወገቡን ታጠቀ። በኵስኵስቱም ውኃ ቀድቶ የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጥብ ጀመር፤ በዚያ በታጠቀው ማበሻ ጨርቅም አበሰ። ወደ ስምዖን ጴጥሮስም ደረሰ፤ እርሱም፥ “አቤቱ፥ አንተ እግሬን ታጥበኛለህን?” አለው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “እኔ የምሠራውን አንተ ዛሬ አታውቅም፤ ኋላ ግን ታስተውለዋለህ” ብሎ መለሰለት። ጴጥሮስም፥ “መቼም ቢሆን አንተ እግሬን አታጥበኝም” አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም፥ “እውነት እውነት እልሃለሁ፤ እኔ እግርህን ካላጠብሁህ ከእኔ ጋር ዕድል ፋንታ የለህም” ብሎ መለሰለት። ስምዖን ጴጥሮስም፥ “አቤቱ፥ እንኪያስ የምታጥበኝ እጆችንና ራሴንም እንጂ እግሮችን ብቻ አይደለም፤” አለው። ጌታችን ኢየሱስም፥ “ፈጽሞ የታጠበ ከእግሩ በቀር ሊታጠብ አያስፈልገውም፤ ሁለንተናው ንጹሕ ነውና፤ እናንተማ ንጹሓን ናችሁ፤ ነገር ግን ሁላችሁ አይደላችሁም” አለው። ጌታችን ኢየሱስም አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና ስለዚህ “ሁላችሁ ንጹሓን አይደላችሁም” አለ። እግራቸውንም ካጠባቸው በኋላ ልብሱን አንሥቶ ለበሰና እንደ ገና ከእነርሱ ጋር ተቀመጠ፤ እንዲህም አላቸው፥ “ያደረግሁላችሁን ዐወቃችሁን? እናንተ ‘መምህራችን፥ ጌታችንም’ ትሉኛላችሁ፤ መልካም ትላላችሁ፤ እኔ እንዲሁ ነኝና። እንግዲህ እኔ መምህራችሁና ጌታችሁ ስሆን እግራችሁን ካጠብኋችሁ እናንተም እንዲሁ የባልጀሮቻችሁን እግር ልታጥቡ ይገባችኋል። እኔ እንደ አደረግሁላችሁ እናንተም ልታደርጉ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና።
የዮሐንስ ወንጌል 13 ያንብቡ
ያዳምጡ የዮሐንስ ወንጌል 13
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 13:4-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች