የማርያምና የእኅቷ የማርታ መንደር በሚሆን በቢታንያ ስሙ አልዓዛር የሚባል የታመመ አንድ ሰው ነበር። ማርያም ግን ጌታችንን ሽቱ የቀባችው፥ እግሩንም በጠጕርዋ ያሸችው ናት፤ ወንድምዋ አልዓዛርም ታሞ ነበር። እኅቶቹም፥ “ጌታችን ሆይ፥ እነሆ፥ የምትወደው ታሞአል” ብለው ወደ ጌታችን ኢየሱስ ላኩ። ጌታችን ኢየሱስም ሰምቶ እንዲህ አለ፥ “ይህ ደዌ በእርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይከብር ዘንድ ስለ እግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት አይደለም።” ጌታችን ኢየሱስም ማርታንና እኅቷን ማርያምን፥ አልዓዛርንም ይወዳቸው ነበር። እንደ ታመመ በሰማ ጊዜM በነበረበት ቦታ ሁለት ቀን ቈየ። ከዚህም በኋላ፥ ደቀ መዛሙርቱን፥ “ኑ፥ ወደ ይሁዳ ሀገር ደግሞ እንሂድ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም፥ “መምህር ሆይ፥ አይሁድ ሊወግሩህ ይሹ አልነበረምን? ዛሬ ደግሞ አንተ ወደዚያ ልትሄድ ትሻለህን?” አሉት። ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “ቀኑ ዐሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን? በቀን የሚሄድ አይሰናከልም፤ የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና። በሌሊት የሚሄድ ግን ይሰነካከላል፤ በውስጡ የሚያየው ብርሃን የለምና።” ይህንም ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው፤ ከዚህም በኋላ፥ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ላነቃው እሄዳለሁ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም፥ “አቤቱ፥ ከተኛስ ይነቃል፤ ይድናልም” አሉት። ጌታችን ኢየሱስም ስለ ሞቱ ተናገረ፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ መተኛት መስሎአቸው ነበር። ከዚህ በኋላም ጌታችን ኢየሱስ ገልጦ እንዲህ አላቸው፥ “አልዓዛር ሞተ። ታምኑም ዘንድ እኔ በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ኑ፥ ወደ እርሱ እንሂድ።” ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስም፥ ባልንጀሮቹን ደቀ መዛሙርት፥ “እኛም ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እንሂድ” አላቸው። ጌታችን ኢየሱስም ወደ ቢታንያ ሄደ፤ ከዚያም በደረሰ ጊዜ ከተቀበረ አራት ቀን ሆኖት አገኘው። ቢታንያም ለኢየሩሳሌም ዐሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ቅርብ ነበረች። ከአይሁድም ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርያምና ወደ ማርታ የሄዱ ብዙዎች ነበሩ። ማርታም ጌታችን ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ ወጥታ ተቀበለችው፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። ማርታም ጌታችን ኢየሱስን እንዲህ አለችው፥ “ጌታዬ ሆይ፥ በዚህ ኖረህ ቢሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር። አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ።” ጌታችን ኢየሱስም፥ “ወንድምሽስ ይነሣል” አላት። ማርታም፥ “ሙታን በሚነሡባት በኋለኛዪቱ ቀን እንደሚነሣ አውቃለሁ” አለችው። ጌታችን ኢየሱስም አላት፥ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞትም ይነሣል። ሕያው የሆነ የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም፤ ይህንስ ታምኛለሽን?” እርስዋም፥ “አዎን፥ ጌታዬ ሆይ፥ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ” አለችው። ይህንም ብላ ሄደች፤ እኅቷን ማርያምንም ቀስ ብላ ጠራችና፥ “እነሆ፥ መምህራችን መጥቶ ይጠራሻል” አለቻት። እርስዋም ይህን በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች፤ ወደ እርሱም ሄደች። ጌታችን ኢየሱስም ማርታ በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደር አልገባም ነበር። ሊያጽናኑአት መጥተው በቤት ከእርስዋ ጋር የነበሩ አይሁድም ፈጥና ተነሥታ እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ በዚያ ለወንድምዋ ልታለቅስ ወደ መቃብሩ የምትሄድ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያምም ጌታችን ኢየሱስ ወደ አለበት ስፍራ ደረሰችና በአየችው ጊዜ ከእግሩ በታች ሰግዳ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ በዚህ ኑረህ ቢሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር” አለችው።
የዮሐንስ ወንጌል 11 ያንብቡ
ያዳምጡ የዮሐንስ ወንጌል 11
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 11:1-32
9 ቀናት
እያንዳንዳቸው እየሱስ ክርስቶስ የህያው የእግዛብሔር ልጅ መሆኑን መልካም የምስራች ዜናን ያበስሩ ነበር። ይህ አጭር ቪዲዮ የኢሱስ ክርስቶስ የእያንዳንዱን ቀን ቁልፍ ተአምራትን በምሳሌ ይገልፃል።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች